ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, May 1, 2021

በአዲስ አበባ በቅርቡ ሰልፍ ያስፈልጋል! ለምን? ከፅሁፉ መልሱን ያገኙታል።ሕዝብ ይወያይበት መንግስትም ያስብበት።


ጉዳያችን/Gudayachn 

ኢትዮጵያ በነፃነቷ ከክፍለ ዘመን ወደ ክፍለዘመን የተሻገረች ሀገር ነች።እነኝህ የነፃነት ጉዞዎች እጅግ ውጣ ውረድ በተሞላባቸው የታሪክ ሂደቶች አባቶቻችን እያለፉ ሀገሪቱን ዛሬ ላለንበት ዘመን አሸጋግረውልናል።አሁን ያለንበት የዓለማችን ወቅታዊ ሁኔታ ደግሞ አንድ ዓይነት የሥርዓት ለውጥ ለማድረግ ፍትጊያ ላይ ነው።ከሀያኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ ዓለምን ለመቆጣጠር የቻሉ ከነበሩበት ላለመውረድ የሚጥሩበት፣ተበድለው የነበሩ ከበደላቸው ሰብረው ለመውጣት የሚጥሩበት እና አዳዲስ ኃይሎች ደግሞ ወደፊት የሚመጡበት ጊዜ ነው።በዓለም ታሪክ በሁለተኛውም ሆነ በአንደኛው የዓለም ጦርነት የዓለም ስርዓት እንዲሁ ተቀይሯል።በዘመናችን ከተነሳው የኮቪድ ወረርሽኝ በኃላ የዓለም ስርዓት ፍትጊያ ያጣዋል ማለት አይቻልም።

የእነኝህ ፍትግያዎች አንዷ ሜዳ ደግሞ አፍሪካ ነች።አፍሪካ ከቅኝ ግዛት ብትላቀቀም ከእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ግን ገና አልወጣችም።በመሆኑም አፍሪካውያን ዛሬ የፖለቲካ ነፃነታቸውን ካገኙ ከግማሽ ክፍለዘመን በኃላም በሀብት ላይ ተቀምጠው በድህነት እየማቀቁ ነው። የበለፀጉ ሀገሮች አፍሪቃውያንን ከሚያዋክቡባቸው መንገዶች ውስጥ አንዱ የምርጫ ሂደትን መተቸት ነው።ምርጫ ያላደረጉት ባለማድረጋቸው ሲወቀሱ ያደረጉት ደግሞ ሂደታቸው ይተቻል።ይህ በራሱ ችግር የለውም።ምርጫ አድርጉ ማለት እና ሂደቱ ላይ ሃሳብ መሰጠት ለበጎ ብለን እንውሰደው።ሆኖም ግን እኛ ያላቦካነው ዳቦ አይሆንም ዓይነት መቀባጠር የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ አባዜ ጉዳይ ነው።

ኢትዮጵያ በግንቦት ወር መጨረሻ የምታደርገው ምርጫ በሀገሪቱ ታሪክ በምርጫ ኮሚሽን አደረጃጀትም ሆነ አፈፃፀም እጅግ የተሻለ እና የውስጥ ነቃፊዎች ሳይቀሩ የኮሚሽኑን አደረጃጀት እና አፈፃፀም ለመተቸት ቃላት ያጠራቸው ጊዜ ነው።ምክንያቱም እንከን ለማውጣትም እንከን ማግኘትን ይጠይቃል። አንዳንዶች በህወሓት/ኢህአዴግ ዘመን የምርጫ አጃቢ የነበሩ ዛሬ ሁኔታው ግልጥ እና አስተማማኝ ሲሆን ምርጫው ላይ አንሳተፍም ቢሉም ምክንያታቸው በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት አጥተው ከመሸማቀቅ ባለመሳተፋችን ነው እንጂ እናሸንፍ ነበር እያሉ ከቤት ተቀምጠው መሸለሉ የተሻለ ስለመሰላቸው ነው።ለምሳሌ ፕሮፌሰር መራራ እና ድርጅታቸውን መጥቀስ ይቻላል።ለእነርሱ የተከተሉት መንገድ አዋጪ መስሏቸው ይሆናል።ሆኖም ግን ወክለነዋል የሚሉት ሕዝብ አንቅሮ የሚተፋቸው ጊዜ መሆኑን የፖለቲካ ምሑር የሆኑት አለመረዳታቸው ነው አስገራሚው ነገር።

ኢትዮጵያ መጪውን ምርጫ ልታደርግ በሄደችበት ሂደት ላይ እንቅፋት ይገጥማታል ብለው አድፍጠው የነበሩ አንዳንድ የምዕራብ ሀገር ባለስልጣናት አሁን የምርጫው ሂደት እየሰመረ መሆኑን ሲያውቁ የሚይዙት የሚጨብጡት ተፍቷቸዋል።በመሆኑም ከአሁኑ ምርጫው ዓለም አቀፍ መስፈርት አያሟላም እያሉ መለፈፍ ይዘዋል።ዓለም አቀፍ መስፈርት ማለት እነርሱ ይሁን ሲሉት የሚሆን እነርሱ ሲከለክሉ የሚቀር አድርገው ያስባሉ።ዓለም አቀፍ የምርጫ መስፈርት በሚለው መሰረት ኢትዮጵያ በቅርቡ የምታደርገው ምርጫ  ደረጃውን የጠበቀ ነው።ለዓለም አቀፍ የምርጫ መስፈርት አንዱ መነሻ ሕግ የተባበሩት መንግሥታት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1948 ዓም  ያወጣው ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ ነው።በእዚህ ድንጋጌ ላይ አንዱ እና ዋነኛ መስፈርቱ ምርጫ ሀገሮች በየተወሰነ ጊዜ የማድረጋቸውን አስፈላጊነት ጠቅሶ ምርጫው ሕዝብ በሚስጥር የመስጠቱን ፋይዳ በዋናነት ያነሳል።ይህ ደግሞ በዋናነት የሚያከናውነው የምርጫ ቦርድ አደረጃጀት፣አፈፃፀም እና የእስካሁኑን ሂደት ተረድቶ በምን ያህል የተሻለ ደረጃ ኢትዮጵያ እየሄደች እንዳለ ግልጥ ነው።የሚገርመው አንዳንድ የአሜሪካ ሴናተሮች በሺህ ማይሎች ርቀት ላይ ተቀምጠው የኢትዮጵያን ምርጫ ሊተቹ መሞከራቸው ነው። እንደነርሱ አባባል ከእዚህ በፊት ፕሬዝዳንት ኦባማ አዲስ አበባ ላይ ሱዛን ራይስ አሜሪካ ላይ ሆነው የህወሓት/ኢህአዴግን  የምርጫ ፌዝ ''ዲሞክራሲያዊ'' እያሉ ሲሳለቁ ያልታዘብናቸው ይመስላቸዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሉአላዊነቱ የማይበገር መሆኑን ድምፁን የሚያሰማበት ጊዜ አሁን ነው። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድምፃቸውን አሰምተዋል።አሁን የአዲስ አበባ ሕዝብ ድምፁን የሚያሰማበት ጊዜ የደረሰ ይመስለኛል።በመሆኑም አደባባይ ወጥቶ የማንንም የፖለቲካ ድርጅት ሳይነቅፍ እና ሳያጥላላ ነገር ግን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ አትግቡ የሚል ድምፁን ማሰማት አለበት። ይህ ብቻ አይደለም ግብፅንም ሆነ ሱዳንን በእዚሁ ሰልፍ ማስጠንቀቅ አለበት።ዛሬ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያስተላለፈውን በህወሓት እና ኦነግ ሸኔ ላይ የሽብርተኝነት የውሳኔ ሃሳብ ስልፉ መደገፍ አለበት።ይህ ሰልፍ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ጥቅም አለ።ጥቅሞቹም - የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት ለባዕዳን ያሳይበታል፣የራሱን ሕብረት ዳግም ያረጋግጥበታል፣ለኢትዮጵያ ጠላቶች ማስጠንቀቅያ ይሰጥበታል፣ሌላው የባዕዳንን ተንኮል ላልሰማ ኢትዮጵያዊም በሰልፉ ምክንያት እንዲነቃ ያደርገዋል። ስለሆነም አዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ ወይንም በጃንሜዳ ወይንም ሌላ አመቺ ስፍራ ድምፁን ከፍ አድርጎ ማሰማቱ መልካም ለሚሰሩ የመንግስት ኃላፊዎችም ሕዝብ  ከበጎ ስራቸው ጎን ሁል ጊዜ የሚቆም እንደሆነ የሚያረጋግጡበት አንዱ የሞራል ስንቅም ነው። ሰልፉ ሲደረግ ሁለት አስጊ ጉዳዮች አሉ።እነርሱም ኮቪድ -19 ወረርሽኝ እና ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች የፀጥታ ችግር እንዳይሆኑ የሚሉት ናቸው።ሆኖም ግን የሰልፉ መልዕክት በተለይ በእዚህ ካለው ጥቅም አንፃር እያንዳንዱ ሰው የአፍ  እንዲያደርግ እና እርቀት እንዲጠቅብ በማድረግ እና የፀጥታ ጥበቃውንም በማጠናከር (ወደ ሰልፉ የሚሄዱትን መፈተሽ ጨምሮ) ጥንቃቄ ከተደረገ የሰልፉ የኢትዮጵያውያንን ሕብረት ከማንፀባረቁ አንፃር ጥቅሙ ከፍተኛ ነው።

ለማጠቃለል የአሜሪካን እና አጋሮቿን በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ መግባት የሚቃወም ግዙፍ ሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ ያስፈልጋል።ይህ ሰልፍ አስፈላጊ ነው ያልኩባቸው አምስት ምክንያቶች  -

1) ለአሜሪካ ግልፅ መልዕክት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ያስተላልፋል።መንግስት ሕዝባዊ ድጋፍ የለውም የሚል ግምት ላላት አሜሪካ መልዕክት አለው።

2) በሰልፉ ላይ የዲሞክራቶችን የአፍሪካ ፖሊሲ በግልጥ መቃወም። በእዚህም ጉዳዩ የውጪ ፖሊሲ ክስረት እንደሆነ ለአሜሪካ ሕዝብ እና ምሁራን መልዕክት ያስተላልፋል።

3) አሜሪካኖች አፍሪካን የማጣት ዕድል እንደሚገጥማቸው ግልጥ መልዕክት ስለሚያስተላልፍ በሪፓብሊካን እና ዲሞክራቶች  ፖሊሲ አውጪዎቹ መካከል ቆይቶም ቢሆን አከራካሪ ጉዳይ መፍጠሩ አይቀርም።

4) የአሜሪካን ጣልቃ ገብነት የሚቃወሙ ሀገሮችም ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ ያደርጋል።በአሜሪካ አንፃር ያሉ ሀገሮች የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያሳየውን ተቃውሞ አይተው ከኢትዮጵያ ጎን መቆም ዘለቄታዊ ጥቅም መሆኑን እንዲያስቡ ያደርጋል።

5) ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለራሱም የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት በምን ያህል ደረጃ አደጋ መሆኑን ያሳስባል።የአሜሪካ የጣልቃ ገብነት አደጋ በምን ያህል አደጋ እንዳለው በኢትዮጵያ ከገጠር እስከ ከተማ እኩል ተረድቶታል ማለት አይቻልም።ይህ ሰልፍ ግን የጉዳዩን አደገኛነት ለራሱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማሳሰብያ ይሰጣል።

ኢትዮጵያን ፈጣሪ በጥባቆቱ ልጆቿ በተጋድሏቸው ተጠብቃ ለዘላለም ትኑር!

No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...