ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, May 12, 2021

ሱዳን ለሩስያ የባህር ኃይል ወደብ ለመስጠት የተስማማችውን ውል መሰረዝ ለአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ምን ዓይነት በረከት እና እርግማን ያመጣል?

የሩስያ መርከብ (ፎቶ ታስ ዜና አገልግሎት)

>> የአሜሪካ ኢትዮጵያን በትግራይ ጉዳይ የመጎንተል ሥራ በቅርቡ ወደ መቃብር ይወርዳል።

ጉዳያችን/Gudayachn 


ሱዳን እና ሩስያ የሩስያ ባህር ኃይል ጣብያ በሱዳን ወደብ ላይ የጦር ሰፈር እንዲያገኝ ለመጪዎቹ 25 ዓመታት የሚቆይ ውል መዋዋላቸው የተሰማው ባለፈው ታህሳስ ወር መጀመርያ ሳምንት ላይ ነበር።ስምምነቱ ሩስያ የጦር መርከቦቿን በወደቡ ላይ ከማስፈር ባለፈ የመርከብ ጥገና ስራም የምትሰራበት እንደሚሆን ተጠቅሶ፣የኒኩለር ተሸካሚ መርከቦችን ማሳረፍ የጨመረ ዕድል ለሩስያ ሲሰጣት፣ሱዳን በምላሹ ነፃ የጦር መሳርያዎችን ከሩስያ የማግኘት ዕድል እንደሚከፍት ነው የተነገረው።የሩስያ በሱዳን የባህር ዳር ላይ ቦታ ማግኘት የአፍሪካ መግቢያ በር እንደሚሆናት ታስቦ ነበር።በሌላ በኩል የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ሀገሮች (ናቶ) ወደ ደቡብ የሚያደርገውን መስፋፋት ለመግታት የታሰበ የሩስያ አካሄድ ነው በማለት የተነተኑም ነበሩ።

የሩስያ በሱዳን ወደብ ላይ ቦታ ማግኘቷ በዋናነት የቆጠቆጣት አሜሪካ ነበረች።አሜሪካ ከሱዳን ጋር ያላትን ግንኙነት በቶሎ ከማሻሻል አንስቶ ሱዳንን ከአሸባሪ መዝገብ እንድትሰረዝ እና የዓለም ባንክ ገንዘብም ለወቅታዊ ችግሮቿ እንዲሸፍኑ ተሰጥቷታል። አሜሪካ ሩስያ በሶርያ ያላትን መሰረት ማጠናከሯ እንደትልቅ ስጋት የምታየው ሲሆን ወደ ሱዳን ያደረገችውን ግስጋሴ በሱዳን የውስጥ ጉዳይ በመግባት እና በማባበል ውሉ እንዲሰረዝ ያደረገችው አሜሪካ ነች እየተባለች ትታማለች።

የሩስያ ዜና አገልግሎት ''ታስ'' ከሳምንት በፊት እንደዘገበው ስምምነቱ አንድ ዓመት ሳይሆነው ለማቆም መሞከር ሁለቱም ወገኖች አንዳንዳቸው ለአንዳቸው በማሳወቅ ሳይስማሙበት ሊሆን እንደማይችል ከፍተኛ የሩስያ ባለስልጣን እንደገለጡለት ነው ያስታወቀው።ባለሥልጣኑ ይህንን ይበሉ እንጂ ውሉ መሰረዙን ግን የመካከለኛ ምስራቅ መገናኛ አውታሮች እና የሩስያ ዜና አገልግሎትም ገልጧል።

ጉድዩ ለአፍሪካ ቀንድ ይዞት የሚመጣው በረከት እና እርግማን ምንድነው? የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ነው። ሩስያ ፊቷን ወደ አፍሪካ እንደ ቻይና እና ምዕራባውያን ማዙሯ የአደባባይ ምስጢር ነው።ለእዚህም የሩስያ አፍሪካ ግንኙነት ላይ ያተኮረ ጉባኤ ከአንድ ዓመት በፊት በሩስያ ከተደረገ በኃላ ቀጣይ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው ጉባኤ በአፍሪካ እንደሚደረግ መነገሩ ያታወቃል።ጉባኤውን ለማዘጋጀት ኢትዮጵያ ፈቃደኛ መሆኗን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር  እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ ደመቀ መኮንን አማካይነት መግለጧ ይታወሳል።አማርኛ አቀላጥፈው የሚናገሩት በኢትዮጵያ የሩስያ አምባሳደር ኤቭገኒ ተረኪን ሩስያ የኢትዮጵያ አጋር ሀገር መሆኗን ባገኙት አጋጣሚ ሲገልጡ ተሰምተዋል።ሩስያ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ጉዳይ አስታኮ የጠራቸውን ስብሰባዎች በሙሉ በመቃወም ማክሸፍ ከቻሉት ሀገሮች ውስጥ ግንባር ቀደሟ ነች።ከእዚህ በኃላ ነው የተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያከብር እና በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ መግባት ተገቢ አለመሆኑን አፅንኦት የሚሰጥ መግለጫ ያወጣው። 

የአፍሪካ ቀንድ በሁሉም የዓለም ኃያላን ዘንድ መጪው ቁልፍ የበለጠ ስልታዊ ብቻ ሳይሆን ግዙፍ ምጣኔ ሀብት ይዞ ይወጣል ተብሎ የሚታሰበው እና ለአንዳንዶች ''የሚፈራው'' ጠቅላይ ዓቢይ ወደ ስልጣን እንደመጡ ያቀነቀኑት የኤርትራ፣ኢትዮጵያ እና ሱማሌ የምጣኔ ሀብት ጥምረት ሃሳብ ነው።ይህ ሃሳብ ግዙፍ የገበያ ማዕከል ብቻ ሳይሆን ይዞ የሚመጣው የቀይ ባህርን በተሻለ ጉልበት የመቆጣጠር ኃይል ለሶስቱ ሀገሮች ይሰጣል።ስለሆነም የሩስያ ቀጣይ መንገድ በኤርትራ የባህር ኃይል መሰረት የማግኘት ዕድል ከገጠማት እና ኢትዮጵያ የባህር ኃይሏን እንደጀመረችው ማደራጀት ከቻለች በአካባቢው ላይ ተፅኖ መፍጠር የሚፈልጉ ኃያላን ጥቅማቸው የሚነካ አድርገው ያዩታል።ስለሆነም ሩስያ እና ቻይና ከሚጠቀሙ የአፍሪካ ቀንድ ቢበታተን የሚመርጡ የሉም ማለት አይቻልም።የሶስቱ ሀገሮች የምጣኔ ሐብት ጥምረት ግን ለሦስቱም ሀገሮች ከፍተኛ ጥቅም ይዞ መምጣቱ አያጠራጥርም።በተለይ  በአንፃሩ የተሻለ የሰው ኃይልም ሆነ የምጣኔ አደረጃጀት ያላት ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥላ የምታጠላበት ጥምረት እንደሚሆን ነው የሚታመነው። ስለሆነም ሶስቱ ሀገሮች በሩስያ እና በአሜሪካ አንፃር የሚጫወቱት ጫወታ ከሀገሮቹ ዘላቂ ጥቅም አንፃር በደንብ አጥንተው የሚገቡበት መሆን አለበት ማለት ነው።

የሩስያ ከሱዳን የባህር ኃይል ማረፍያ አለማግኘት ማለት አማራጭ ቦታ የላትም ማለት አይደለም።በኢትዮጵያ አግባቢነት በኤርትራ የማግኘት ዕድል አሁንም አላት።ይህ እንዳይሆን አሜሪካ ኢትዮጵያን የማትለምንበት መንገድ አይኖርም።በእርግጥ ከመለመን በፊት አሜሪካ በትግራይ ጉዳይ አሳባ ብዙ የማወክ ሙከራ በኢትዮጵያ ላይ ላለፉት ስድስት ወራት ስታስኬድ ሰንብታለች።በውጤቱ ግን የተሳካ ሆኖ አላገኘችውም።የግብፅ የደህንነት ባለስልጣናት ለአሜሪካ 'የኢትዮጵያን ነገር ተይው ከውስጥ የጀመርነው ፕሮጀክት አለ' እያለች ስታማልል ብትከርምም በቅርቡ ግን ከቤንሻንጉል እስከ መቀሌ ያለው የተንኮል ድር በሙሉ በመበጣጠሱ አሜሪካ ከሰሞኑ የመለሳለስ መልክ ብታሳይም አይገርምም።

አሁን የአሜሪካ ስጋት ሩስያ ከኢትዮጵያ ጋር ከገጠመች በተለይ በኤርትራ ወደብ የባህር ኃይል ከመሰረተች ከሶርያ ቀጥሎ ሩስያ ቁልፍ ማረፍያ እንዳገኘች ትቆትረዋለች ብቻ ሳይሆን ከመካከለኛው ምስራቅ ወደ አፍሪካ የምታደርገው እመርታ ወሳኝ ምዕራፍ እንደሆነ ተረድታዋለች። ይህም ከቀዝቃዛው ጦርነት በኃላ ሩስያ እንደገና ወደ አፍሪካ አንፃር አንሰራራች ማለት ነው።ስለሆነም የሱዳን ውል ማፍረስ ለኢትዮጵያ ይዞ የሚመጣው አንዱ በረከት አሜሪካ ኢትዮጵያን በትግራይ ጉዳይ መጎንተሏን ታቆማለች ወይንም ታቀዘቅዛለች።በመቀጠልም ሰሞኑን እያሳየች እንዳለው የዓባይ ግድብ አንፃር ኢትዮጵያ የራሷን የተፈጥሮ ሀብት የማልማት መብት አላት የሚለውን አረፍተነገር በመደጋገም ታፈገፍጋለች።ኢትዮጵያ ይህንን የሩስያን ጉዳይ ከኤርትራ ጋር ተመካክራ እንደ ታላቅ ወንድም እያስፈራራች ምርጫውን እና የውሃ ሙሌቷን ከጨረሰች ቀሪውን ውሳኔዋን ከመስከረም አደይ አበባ መፈንዳት ጋር ቀስ ብላ ቡና ፉት እያለች መወሰን ትችላለች።

ለማጠቃለል የአሜሪካ በትግራይ ጉዳይ ኢትዮጵያን የመጎንተል ሂደት በቅርቡ ወደ መቃብር በእዚሁ በሩስያ ጉዳይ እንደሚያበቃ ግን ከወዲሁ መገመት ይቻላል።ይህ ማለት አንዳንድ በሎቢ የቀወሱ ሴናተሮች እና ጋዜጠኞች ዝም ይላሉ ማለት አይደለም። ዋናዎቹ የውጭ ፖሊሲ አውጪዎች ግን አንዳች እርምጃ ሊወስዱ አይችሉም ቢያንስ ለመጪዎቹ አራት ወራት።ሌላው ቀርቶ የአውሮፓ ህብረት አዲስ የሳተላይት መሳርያ ካላስገባሁ፣የምርጫ ውጤቱን እኔ ቀድሜ የመናገር መብት ካላገኘሁ እያለ ትንሽ  ጠገብ ብሎ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ሃሳቡ ተቀይሮ ባላችሁት መሰረት ለምርጫው ታዛቢ እልካለሁ ማለቱ ሁሉ የኢትዮጵያ ቦታ መልሶ መሬት እየቆነጠጠ መሆኑን ብቻ ሳይሆን የሚያሳየው አፍሪካ ቀንድ ላይ ያለው መራኮት ኢትዮጵያን ከሁሉ በላይ አስፈላጊ መሆኗንም ጭምር ነው።ይህ እንግዲህ በመላው አፍሪካ ላይ ያላትን ተፅኖ የመፍጠር አቅም ሳናነሳ ነው።ኢትዮጵያውያን ግን አሁን ማተኮር የሚገባው ግዙፍ እርዳታ በተለይ በቤተ እምነቶች አንፃር ለትግራይ እና በልዩ ልዩ ስፍራ አደጋ እና ጥቃት ለደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን የእርዳታ ሀብት ማሰባሰብ እና መርዳት ነው።የኢትዮጵያ ቁስል ይሽራል።ከትግራት እስከ መተከል፣ከአጣዬ እስከ ወለጋ የተጎዱትን የመርዳቱ ተግባር ግን መቀጠል አለበት።
=======================////=============

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...