ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, May 11, 2021

የክርስትና እና የሙስሊም የእምነት አደረጃጀቶች የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች እንዳይጎትቷቸው መጠንቀቅ አለባቸው።


ጉዳያችን/Gudayachn


ኢትዮጵያ የእምነት ሀገር ነች።ህዝቧ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በፈጠረው አምላክ ያምናል።በችግሩ እና በደስታው ጊዜ ብቻ ሳይሆን በሰላምታው ጊዜም ሳይቀር አምላኩን የሚጠራ ሕዝብ ነው።ይህ ሕዝብ ካለምንም ማጋነን ከየትኛውም የዓለማችን ክፍል በተለየ እና በፀና ደረጃ በብዙ ፈተና ውስጥም ቢሆን ከፈጣሪው ጋር ግንኙነት አለው።በሌላው ሀገር የማናገኘው የሞራል ልዕልና በኢትዮጵያውያን ላይ የሚታየው ሌላ ሳይሆን የሕዝቡ በፈጣሪው ላይ ያለው ዕምነት ነው።በቅርቡ በአዲስ አበባ አስተዳደር ከፍተኛ ባለስልጣን እንደተገለጠው በአዲስ አበባ ብቻ በቀን አንዴ በልተው ለማደር የሚቸገሩ ከአንድ መቶ ሺህ በላይ ሕዝብ አለ።በእዚህ ደረጃ ችግር ላይ ያለ ሕዝብ ግን የእምነት ሕዝብ ስለሆነ አንዱ አንዱን እየረዳ የሚኖር የተቸገረውም በትሕትና እንጂ በነጠቃ የማይኖርባት ሀገር መሆኗን ይህ በራሱ ምስክር ነው።

ይህ በእንዲህ እያለ ይህ ወቅት የኢትዮጵያ የክርስትናም ሆነ የሙስሊም አደረጃጀቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ነቅተው እና ተግተው የሚቆሙበት ጊዜ ነው።በሁለቱም ዕምነቶች ውስጥ አደረጃጀቶቻቸውን ለመክፈል እና የፀብ መድረክ ለማድረግ በተለያዩ የፖለቲካ አካላት ጉተታ ይታያል።ጉተታዎቹ ሦስት ዓላማዎችን ይዟል። እነርሱም -  የእምነት ድርጅቶቹን እርስ በርስ በውስጣቸው ሰላም እንዳያገኙ ማበጣበጥ፣ከመንግስት ጋር ማጋጨት እና አንዱን እምነት ሌላውን እንዲጠራጠር ወሬ መንዛት ናቸው። 

በእስልምናም ሆነ በክርስትና ውስጥ ያሉ የውስጥ ቁርሾዎችን ማባባስ እና አደረጃጀቶቹ ሰላም እንዳይሆኑ በማድረግ ተከታዩ ምዕመንን ሰላም መንሳት እና በውጤቱ ሀገር እንዳይረጋጋ እና ሰላም እንዲጠፋ በማድረግ ርካሽ የፖለቲካ ግብ መምታት ነው።
በእዚህ መሰረት በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ውስጥ የበላይ አመራር መጅሊሱን ሕዝብ እንዳይቀበል የሚቀሰቅስ ቅስቀሳ በማካሄድ የፅንፍ ኃይሉ የበላይ እንዲሆን የማድረግ ሙከራ ነው።

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም ውስጥ ተመሳሳይ ድርጊቶች ይታያሉ።በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሰሞኑን ቅዱስ ፓትርያሪኩ ከአንድ ወር በፊት የተቀዳው እና ወቅታዊ የኢትዮጵያን ሁኔታ የተመለከተ ቪድዮ ሰሞኑን መለቀቁን  የቤተክርስቲያኒቱን መዋቅር እና ድምፅ በትክክል የማይወክሉ የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች እዚህም እዝያም በሚድያ እየቀረቡ በቤተክርስቲያኒቱ ስም ሲናገሩ እየታየ ነው።በተለይ የኢትዮጵያ ሚድያዎች የቤተክርስቲያኒቱን ተዋረድ ሳይጠብቁ ያገኙትን ካህን በቤተክርስቲያኒቱ ስም ማናዘዝ እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው።ቤተክርስቲያኒቱም የህዝብ ግንኙነት በተመለከተ በማዕከላዊነት የምትመራበት አንድ ድምፅ እንዲኖራት እና ማንም ከእዚህ ማዕከላዊ የህዝብ ግንኙነት ውጪ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም የሚናገር አገልጋይ እንዳይኖር ጥብቅ መመርያ ያስፈልጋታል። 

ሌላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም ሆነ የእልምና ተከታዮች በተለያየ ጥግ ሆነው ከመንግስት ጋር እንዲጋጩ የሚሰሩ አሉ። እነኝህ የተለያየ ዓላማ የያዙ ናቸው።በእስልምና ውስጥ እጅግ ፅንፍ የያዘ እና የራሱን መጅሊስ ቆርጥሞ በልቶ እና እውነተኛ አማኙን ከመስጊድ አስወጥቶ በሌሎች ሀገሮች የሚታየው የፅንፍ አስተዳደር በእምነት ስም መለጠፍ የምፈልገው ቡድን በቅድምያ ሙስሊሙ ከመንግስት ጋር እንዲጋጭ ማድረግን እንደዋና ግቡ ወስዶታል።ለእዚህም ያገኘውን  እያሰፋ ነገር ስጎነጉን የሚያድር ነው።ይህንን አብዛኛው ሙስሊም ስላወቀበት አንዳንዴ ተመሳስሎ ሲቆም ይታያል።

በተመሳሳይ መንገድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም ውስጥ በተለይ ላለፉት 27 ዓመታት በሌሎቹ የእምነት አደረጃጀቶች ውስጥ የታየው  ፀሐይ የሞቀው የአንድ ብሔር የበላይነት ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ በመጣው ለውጥም ሆነ በቀድሞው ሥርዓት ላይ በቅርቡ የተወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ ሳይቀር ስላስከፋው ቤተክርስቲያኒቱን ለመከፋፈል በተለይ በውጭ ሀገር አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ እየታየ ነበር።ይሄውም የትግራይ ካሕናትን ከቅዱስ ሲኖዶስ ስር ለመለየት አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ሲያደርጉ ታይተው በትግራይ ካህናት ሳይቀር ከፍተኛ ተቃውሞ ስለገጠመው አድፍጦ መቀመጡ እየታየ ነው። በተለይ የእዚህ ዓይነቱ ቡድን በትግራይ በሚኖሩ አባቶች ቢሰማ የሚደርስበትን ውግዘት የተረዳው ቡድን ቤተክርስቲያኒቱን ለመረበሽ አንዳንድ ያልተሳኩ እና የማይሳኩ ሙከራዎች እያደረገ ነው።

የመጨረሻው በኢትዮጵያ የክርስትና እና የእስልምና አደረጃጀቶች ውስጥ እየታዩ ያሉ ተግዳሮቶች አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ እንዲመለከት ማድረግ ነው።ይህ ደግሞ የሐሰት ወሬዎች በመንዛት ሲሆን በፅንፍ አካሄድ የሚታወቁ የፖለቲካ ድርጅቶች ዋና አቀጣጣዮች ናቸው።ይህ አለመተማመን የመፍጠር ሂደት በተለይ የእምነቶቹን ሊቃውንት ያገለለ በመሆኑ ''መደዴ'' የሆኑ የእምነቱ ተከታዮች ቀድመው በመናገራቸው ወይንም በመሳደባቸው ''እንደመሪ'' እየሆኑ የሚወጡበት ስለሆነ አደገኛ አካሄድ ይታይበታል።

ባጠቃላይ  የክርስትና እና የሙስሊም የእምነት አደረጃጀቶች የተለያዩ የፖለቲካ እና የፅንፍ ኃይሎች ጉተታ ውስጥ እንዳይገቡ  ከመቼውም ጊዜ በላይ የእስልምናም ሆነ የክርስትና አደረጃጀቶች የውስጣዊ ጥንካሪያቸውን፣በልቃውንቶቻቸው እና በሕጎቻቸው ላይ ብቻ በተመሰረተ መንገድ መመራታቸውን በደንብ መፈተሽ አለባቸው። 99% የሚሆን ሕዝብ በፈጣሪው የሚያምን ሕዝብ  ሀገር የእምነት አደረጃጀቷ ጤነኛ ብቻ ሳይሆን ለሀገር እድገትም አዎንታዊ አስተዋፅኦ ያለው እንዲሆን ያለምንም ወገንተኝነት የማገዝ ግዴታ ደግሞ መንግስት አለበት።መንግስት የኢትዮጵያ የእምነት አደረጃጀቶች መጠናከር እና ምእመናኖቻቸውን በሚገባ ማገልገል ማለት ሃገራዊ ሰላም ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን በሰላም የማሸጋገር አንዱ እና ወቅታዊው ወሳኝ ተግባር ነው።ከሁሉም በላይ ወሳኞቹ ግን የክርስትናም ሆነ የእስልምና የውስጥ ጤነኛ፣በፖለቲካ ኃይሎች ያልተዘወረ ግን የእምነት ነፃነቱን የጠበቀ የእምነት አደረጃጀት እንዲኖራቸው ጠንክረው ሲሰሩ ነው። ''እውነት አርነት ያወጣችኋል'' ዮሐንስ 8፣32 እንዲል ታላቅ ሀገር ኢትዮጵያን ነፃ የሚያወጣት፣ እምነቷን ጠብቆ የሚያቆይም እውነት እንጂ የተለያዩ አመለካከቶች ጉተታ እና የእነርሱ ሰለባ መሆን አይደለም።

========================///=============

እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው።"
(ዮሐንስ 8:32)
እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው።"
(ዮሐንስ 8:32)

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።