ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, December 20, 2020

ወቅቱ ሁሉም ኢትዮጵያን ሊጠነቀቅላት እና ሊጠብቃት የሚገባበት ጊዜ ነው።


  • ኢትዮጵያ እና ሱዳን በድንበር ጉዳይ ላይ ለመወያየት ለመጪው ማክሰኞ መቀጣጠራቸው ተሰምቷል።

ወቅቱ 

በሀገር ውስጥ -

- መንግስት በትግራይ የሕግ ማስከበር ተግባሩን በማገባደድ ላይ ያለበት፣
- የህወሓት ፅንፍ አመራሮች ገና ያልተያዙበት እና እየታደኑ ያለበት፣
- በትግራይ አስፈላጊ ለሆኑ መሰረተ ልማት ወጪዎች የሚያስፈልጉበት፣
- ብልጥግና ፓርቲ በውስጡ ያሉትን የፅንፍ  የጎሳ ኃይሎች በተለይ በኦሮምያ እና ቤንሻንጉል አለመረጋጋት እንዲፈጠር የበለጠ የሚጥሩበት እና በተለይ በኦሮምያ  ያሉ የፅንፍ ኃይሎች የመንግስትን መወጠር እንደ መልካም አጋጣሚ በመቁጠር እንደ አሜባ ለመስፋፋት የሚጥሩበት፣
- በአንፃሩ በፅንፍ ኃይሎች ላይ ለመዝመት እና ሰላሙን ለማስከበር በኦሮምያ በተለይ በወለጋ ህዝቡ ከምንጊዜውም በላይ አምርሮ የተነሳበት፣
- ኢኮኖሚው አነሰም በዛ በአጭር ጊዜ ጦርነት ሳብያ እና በህወሓት እና በርሱ ዙርያ በነበረው መረብ የሚንቀሳቀሱ የንግድ ድርቶች ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ ከመደረጉ አንፃር ለጊዜውም ቢሆን የሚፈጥረው ተፅኖ በስራቸው በያዙት የሰው ኃይል ሳብያ ክፍተት የሚያሳይበት፣
- ኢትዮጵያ ምርጫ ለማድረግ የምትዘጋጅበት፣
- በኮቪድ ምክንያት የተቀዛቀዘው ምጣኔ ሀብት ድጋፍ የሚሻበት እና በቶሎ ለማገገም የቱሪዝሙን ዘርፍ ለማንቀሳቀስ በጉጉት የሚጠበቅበት፣
- የፀጥታ ችግር ለመፍጠር የሚፈልጉ ተረፈ-ጁንታ እና የስልጣን ጥመኞችን ለመጠበቅ መንግስት ለፀጥታው ዘርፍ ዳጎስ ያለ በጀት ለመመደብ የተገደደበት ጊዜ ነው።

ከውጭ 

- የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ-ፖለቲካ ከምንጊዜውም በላይ የጦዘበት፣
- በአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች መሃል ለምሳሌ በኬንያ እና ሱማሌ፣በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ውጥረቶች ከድንበር ጋር በተያያዘ ውጥረቶች የታየበት፣
- በጅቡቲ የውጭ ወታደራዊ ጦር ሰፈሮች  ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ የመጡበት፣
- ሩስያ በያዝነው ሳምንት በአፍሪካ የመጀመርያዋ የሆነው የባህር ኃይል ጦር ሰፈር በሱዳን የመሰረተችበት እና ሶስት መርከቦች ከ 300  ወታደሮች ጋር ያሰፈረችበት፣በእዚህም መሰረት ውሉ እስከ 25 ዓመታት እንደሚቆይ የተነገረበት፣
- ሱዳን የኢትዮጵያ ለም መሬቶችን ለመውረር እና እስካሁን ግቡ ያልታወቀ የጦር ኃይሏን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ያስጠጋችበት፣ 
- ሱዳን የጦር ኃይሏ ሙሉ በሙሉ በአንድ ዕዝ ስር ነው ለማለት የሚያስቸግር  በመሆኑ የህወሓት ተረፈ-ጁንታም ሆነ የጠገበ ነጋዴ በገንዘብ እንደፈለገ የሚመራው ጦር መሆኑ እና የጦሩ ሂደት የሱዳን የውስጥ መከፋፈል ነፀብራቅ መሆኑ የታየበት፣
- የምዕራቡ የዜና ማሰራጫዎች ከምንጊዜውም በላይ የፀረ-ኢትዮጵያ ዜናዎችን በተጋነነ መልኩ እያቀረቡ ያለበት እና የኢትዮጵያን ገፅታ ለማጠልሸት እየጣሩ ያለበት እና 
- የተረፈ-ጁንታ ቡድኖች በውጭ ሀገር የኢትዮጵያን ገፅታ ለማጠልሸት እና የዲፕሎማሲ መስመሯን ለማበላሸት ከፔቲሽን እስከ ስም ማጥፋት  ዘመቻ የተሰማሩበት ጊዜ ነው።

ለኢትዮጵያ መጠንቀቅ እና መጠበቅ የሁሉም ግዴታ ነው

ኢትዮጵያ አሁን የምትገኝበት ወሳኝ ከሆኑ ታሪካዊ ወቅቶች ውስጥ በአንዱ ላይ ነች።በቅርብ ታሪካችን ውስጥ ኢትዮጵያ ሳትጠቀምባቸው ያለፉት ነገር ግን ወደፊት ሊያስፈነጥሯት የሚችሉ ዕድሎች ሲመክኑባት ኖረዋል።የ1967 ዓም  እና የ1983 ዓም ለውጦች መጠለፋቸው እና አስፈላጊውን ለውጥ ሳያመጡ መምለጣቸው እና የ1997 ዓም ምርጫ ውጤት በህወሓት/ኢህአዴግ መካዱ  ኢትዮጵያን ዋጋ አስቀፍሏታል።አሁን ያለውም የለውጥ ሂደት በውጭም ሆነ በውስጥ አደናቃፊ እንዳይሰናከል የሁሉም ትጋት እና ንቃት ያስፈልጋል።በተለይ የአሁኑ የለውጥ ሂደት ላይ የሚደርስ እንቅፋት በቀላሉ በእንቅፋትነት ብቻ ተወስቶ የሚያልፍ ሳይሆን ካልወጣንበት መርዛማ የጎሳ ፖለቲካ አንፃር ለውጭ ተጋላጭነት ስለሚያጋልጥ 
በመንግስት ላይ የሚደረጉ ጥቃቅን ጫናዎች ሀገርን የሚጎዳ መሆኑን በመረዳት መንግስትን ማገዝ ሀገርን ማገዝ መሆኑን መረዳት ያስፈልግል።
በመጨረሻም ይህ በእንዲህ እያለ አሁን ዘግይቶ ከጅቡቲ እንደተሰማው ኢትዮጵያ እና ሱዳን በድንበር ጉዳይ ላይ ለመወያየት ለመጪው ማክሰኞ መቀጣጠራቸው ተሰምቷል።

 =============================

ማስታወቂያ 

============

በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ የሚችሉበት አዲስ ቴክኖሎጂ ጉዳያችን ማስተዋወቅ ጀምራለች።

አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ - 

https://www.fetantopup.com/#gudayachn 


No comments: