ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, December 24, 2020

የኢትዮጵያ ''የዱላ እና ካሮት'' ፖሊሲ ሱዳንን ከጎረቤት ጋር እንዴት እንደሚኖር ሳያስተምራት አይቀርም።ኢትዮጵያ ዛሬ ሱዳንን በሚገባት መንገድ አናግራታለች!



ጉዳያችን አጭር ልዩ ዘገባ /Gudayachn

ሱዳን እና ግብፅ  በህወሓት መደምሰስ የሆነ የተደበላለቀ እና የተደናበረ ስሜት ውስጥ ገብተዋል።ሱዳን እና ግብፅ ብቻ ሳይሆኑ በኢትዮጵያ ላይ የነበራቸውን እኩይ ዓላማ ለማስፈፀመ የሚያልሙ ኃይሎች ሁሉ አብረው ''እንባ እንባ ይለኛል'' ዓይነት ስሜት ውስጥ ገብተዋል።በመጀመርያ ኢትዮጵያ አበቃላት እያሉ ይናገሩ የነበሩ ሁሉ የሕግ ማስከበሩ ተግባር ከሰብዓዊ ከፍተኛ ጥፋት በራቀ መልኩ ሲጠናቀቅ እራሳቸው ገብተው ሊያቦኩ የሸሚዛቸው እጅጌ ሲሰበስቡ መመልከት አስገራሚ ሆኗል።

ይህ በእንዲህ እያለ ሱዳን ከግብፅ ጋር ወታደራዊ ልምምድ በሰሜናዊ ካርቱም ግዛት በህዳር ወር መጨረሻ ጀምሮ ሲያደርጉ ነበር።የወታደራዊ ልምምዱ ዓላማ ግልጥ ባይሆንም በዋናነት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ላይ ያነጣጠረ ለመሆኑ ግን አያጠራጥርም።የሱዳን እና የግብፅ ፖለቲካም ሆነ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ሁሉ በራሱ በሁለት እግሩ ያልቆመ ነገር ግን ከመካከለኛው ምስራቅ የትርምስ የፖለቲካ ኮተቱን በአፍሪካ ላይ ለማራገፍ የሚጥር የተሳከረ የአጉል ጀብደኝነት ሁሉ ውጤት ነው።

ከሰሞኑ ሱዳን የኢትዮጵያን የድንበር ቦታዎች እየጣሰች ጥቃት ስትፈፅም የአካባቢው የሚልሻ እና የፋኖ ኃይል በከባድ የአፀፋ ምት መልሷት ነበር።በመቀጠል ግን የሱዳን ወታደራዊ ኃላፊዎች የተሰማቸውን እፍረት ለመመለስ ተጨማሪ ጦር ከተሽከርካሪዎች ጋር  ወደ ቦታው ላኩ።ከፍተኛ አመራሮችም ወደ ድንበሩ ወርደው እስከ ሶስት ቀኖች የሚቆይ ቆይታ እያደረጉ  ግፋ በለው ሲሉ ከረሙ።በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩን ለማብረድ በመጀመርያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ጉዳዩ የሁለቱን መንግሥታት እና ሕዝብ የማይወክል እና ሁለቱን ሀገሮች ወደ ግጭት የሚያመራ አይደለም የሚል ማብራርያ በማኅበራዊ ሚድያ ከመልቀቅ ጀምሮ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ  ደመቀ መኮንን የተመራ ከፍተኛ የመንግስት ልዑክ እስከ ትናንት ድረስ በካርቱም ከሱዳን ባለስልጣናት ጋር ውይይት ሲያደርግ ቆይቶ ካለአመርቂ ውጤት ተመልሷል።

እስከ ውይይቱ ድረስ ግን የሱዳን ወታደሮች እስከ 25 ኪሎ ሜትር ድረስ የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው መግባታቸው እና የኢትዮጵያውያን ባለሀብቶችን ንብረት ማውደማቸው ተሰምቷል።ከሱዳን ጋር ትናንት በተደረገው ውይይት የውጭ ጉዳይ ምኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የተደረገው ውይይት የመጀመርያ ደረጃ እና ዝርዝሩ በቀጣይ የሚደረግ ነው የሁለቱ ሀገሮችን ወደ ግጭት መግባት ላይ የሚሰሩ ሀገሮች አሉ በማለት የተናገሩ ሲሆን፣በሌላ በኩል ግን ሌሎች መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ ሱዳን ከአላስፈላጊ የግጭት ሂደቶች እንድትታቀብ አስጠንቅቃለች በማለት ዘግበዋል።

በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ ማስጠንቀቅያ ተራ ንግግር አለመሆኑን ሱዳኖች  የተረዱት ይመስላል።ካርቱምን ከማሳሰቢያ ጋር ለቆ የወጣው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አዲስ አበባ እንደገባ ሱዳንን በሚገባት መንገድ እያናገራት ነው።ይህንን ደግሞ ራሷ ሱዳን አምናለች።ሱዳን ትሪቡን ስሜን አትጥቀሱ አለኝ በማለት የሱዳን ወታደራዊ ባለስልጣን ጠቅሶ ኢትዮጵያ ''ጃባል አቡ ታዩር'' የሚገኘው ጦሯ በኢትዮጵያ ጦር ኃይል በከባድ መሳርያ መደብደቡን አምናለች።ሱዳን ይህንን የምትለው ኢትዮጵያን የፀብጫሪ አድርጎ ለማቅረብ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን የሚሰጡ አሉ።የዛሬው ዘገባ ግን ከእዚህም ያለፈ ነው።ሱዳን በዛሬው የኢትዮጵያን ክንድ የቀመሰችበት መንገድ በአንድ በኩል ብቻ አለመሆኑን ጨምራ ነው የገለጠችው ።ግንባሩ በሁለት በኩል እንደነበር ዜናው ያትታል።ሁለተኛው ግንባር በወዲቃሊ በኩል ያለው ግንባር እንደሆነ የሚያትተው ዜና በሁሉም ግንባሮች በኢትዮጵያ መደበኛ ሰራዊት ጋር ሃገሩን እየተከላከለ ያለው የአማራ ፋኖ እንደሆነ የሱዳኑ ጋዜጣ ሱዳን ትሪቡን ያትታል።

በመጨረሻም ሱዳን ትሪቡን በኢትዮጵያ እና በሱዳን በኩል ያለው ድርድር ዋና ነጥብ።በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ ጥያቄ ሱዳን ወርራ ከያዘችው የኢትዮጵያውያን የእርሻ ቦታዎች ለቃ እንድትወጣ እና ወታደሮቿ ላደረሱት ጥፋት ካሳ እንድትከፍል ሲሆን፣ሱዳን ደግሞ የድንበር መካለሉ አሁኑኑ ይፈፀም ባይ ነች።የኢትዮጵያ እና የሱዳን ድንበር የማቃለል ሥራ ጥናት ከንጉሡ ጊዜ ጀምሮ የነበረ ሲሆን ስራው ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ እና የምድር ላይ ምልክቶች ሙሉ  በሙሉ ለማድረግ  ጊዜ እንደሚጠይቅ እያወቀች ኢትዮጵያ በተወጠረችበት ሰዓት ዛሬውኑ ማለቷ በግርግር እና በችኮላ የማይገባትን መሬት ለመውሰድ እንደሆነ ማንም የሚረዳው ነው።ለማንኛውም የኢትዮጵያ ''የዱላ እና ካሮት'' ፖሊሲ ሱዳንን ከጎረቤት ጋር እንዴት እንደሚኖር ሳያስተምራት አይቀርም።

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...