ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, December 24, 2020

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓቢይ አህመድ የጎሳ ፖለቲካን ለማገድ ከሕገ መንግሥቱም አንፃር ያለውን ቀዳዳ በሙሉ ተጠቅመው በተግባር ላይ የሚያውሉበት ወርቃማ ጊዜ አሁን ነው።






ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓቢይ አሕመድ 

  • ኢትዮጵያ ከእዚህ በላይ የጎሳ ፖለቲካ የመሸከም አቅም የላትም።በአሁኑ ሰዓት  የጎሳ ፌድራሊዝምን ለማገድ ሀገራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታም ይፈቅድላታል።

ኢትዮጵያ የሕዝቧን ባሕል፣ታሪክ እና ማንነትን ያማከለ የመንግስት ስርዓት ከመመስረት ይልቅ ተለማምዳው የማታውቀው  የጎሳ ፖለቲካ ታውጆባት ወደ ጥፋት እንደሚወስዳት እያወቀች ዛሬ ላይ ደርሳለች።የጎሳ ፖለቲካውን በህወሓት ተፅዕኖ ስር በሚገኘው  በኢህአዴግ ስብስብ ላለፉት ሠላሳ ዓመታት ያህል ታውጆ ኢትዮጵያን ለመበጣጠስ የደረሰ ብዙ መከራ በሕዝቧ ላይ አስከትሎ ከዛሬ ደርሷል።

የጎሳ ፖለቲካው በዋናነት የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደ ሕዝብ፣አንድ ዜጋን እንደዜጋ የማያውቀው ህገ መንግስት ዋና ማጠንጠኛው ነው።ህገ መንግስት መግቢያው ሲጀምር 
''  እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች፡በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገታችን እንዲፋጠን፣ የራሳችንን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን፣...''
በሚሉ ዓረፍተ ነገሮች ይጀምራል።ይህ ማለት ህገ መንግስቱ ከመነሻው ለኢትዮጵያዊነት በወልም ሆነ በግል እውቅና አይሰጥም።

የጎሳ ፌድራሊዝም ማለት በራሱ የፌድራል አስተዳደር ብቸኛ መንገድ ማለት አይደለም።ጎሳን መሰረት ያደረገ ፌድራሊዝም አንዱ መገለጫው ጎሳን መሰረት ያደረገ የክልሎች አከላለል አንዱ መነሻው ነው።የጎሳ ፖለቲካ እና የጎሳ ፌደራሊዝም በኢትዮጵያ ስላስከተለው ጥፋት የተለየ ጥናት ማድረግ የሚጠይቅ አይደለም።ከእዚህ ሳምንቱ የመተከል ጭፍጨፋ እስከ ሐረር እና አርሲ፣ከሻሸመኔ እስከ ማይካድራ የደረሱትን ጥፋቶች ብቻ መጥቀስ ይበቃል።አሁን ጥያቄው የጎሳ ፖለቲካንም ሆነ የጎሳ ፌዴራሊዝምን ኢትዮጵያ ከእዚህ በኃላ ልትሸከምበት የምትችለው ትከሻ አላት ወይ? የሚለው ነው።

በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ ጎሳ ፖለቲካ እና ለጎሳ ፌድራሊዝም ጠበቃ የሚቆም የሀገር ውስጥ ወይንም የውጭ አካል አለ? 

በሀገር ውስጥ የጎሳ ፖለቲካ ዋና አቀንቃኝ የነበረው የቀድሞው የፅንፈኛው ህወሓት በዋና ሞተርነት ስያንቀሳቅሰው ሌሎች ላለፉት አርባ ዓመታት በላይ በየጎሳቸው ሲያቀነቅኑ የነበሩ በዋናነት ከኦሮሞ፣ኡጋዴን፣ሲዳማ እና በቅርብ ደግሞ ከዓማራ አጋዦች አላጣም።ሆኖም ግን በኢትዮጵያ ሕዝብ ማኅበራዊ፣ታሪካዊ እና ፖለቲካዊ ታሪክ አንፃር ያልተለመደ እና ወደ ህዝቡ ለመስረፅ ከሃያ አመታት በላይ ፈጅቶበታል። ይህም ሆኖ ግን አሁንም በሕዝብ ውስጥ ሰርፆአል ማለት የሚቻልበት ደረጃ አይደለም።ይልቁንም ዘመን በሄደ ቁጥር ከህዝብ እየተነጠለ የጥቂት ጥቅመኞች ስብስቦች ዙርያ እየቀረ የመጣ እና በተቀረው ሕዝብ ዘንድ ግን እጅግ የሚጠላ እና ለሞት እና ለግጭት የሚዳርገው ዋነኛ ጠላቱ ሆኗል።ስለሆነም በሀገር ውስጥ ለጎሳ ፖለቲካ እና ለጎሳ ፈድራሊዝም ዘብ የሚቆሙ አካላት ከሕወሓት መደምሰስ በኃላ የቀሩት አቀንቃኞቹ በክልል ደረጃ በኦሮምያ፣በዓማራ እና በቤንሻንጉል ፅንፍ በያዙ አካሎች ዙርያ ተኮልኩሎ እና ተነጥሎ ብቻውን መንምኖ ቆሟል።

የኢትዮጵያን የጎሳ ፖለቲካ እና ይህንኑ መሰረት አድርጎ የተመሰረተው የክልሎች አመሰረታተት በውጭ አካላትም ሆነ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድም አድናቆት አላገኘም።በእርግጥ በኢትዮጵያ ጠላቶች በኩል ኢትዮጵያን ይበትናል ከሚል ምኞት ህወሓትን ሲያደንቁ እና ሲያበረታቱ ታይተዋል።ከእዚህ በተለየ የአፍሪካ ሀገሮች የኢትዮጵያን አካሄድ በፍርሃት ሲመለከቱት ኖረዋል።ለእዚህም ምክንያቱ የኢትዮጵያ አካሄድ ወደ ሀገራቸው እንዳይመጣ ከመፍራት የመነጨ ነው።የቀረው ዓለም ግን ቢያንስ የጎሳ ፖለቲካን አላደነቀም።ይህ ማለት ኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካዋን ሙሉ በሙሉ ብታግድ በተለይ በእዚህ ህወሓት በተወገደበት ጊዜ እና ሕዝቡም በጎጥ ልዩነት የሚነሱ ግድያዎች ባንገሸገሹት ጊዜ ከኢትዮጵያ መንግስት የጎሳ ፖለቲካን የሚያግድበትን አንዳች ዓይነት መንገድ መቀየስ እና ተግባራዊ ማድረግ አለበት።

የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም አከላለል አንዱ እና ዋናው ችግር ጎሳን መሰረት ማድረጉ ነው።ይህ ደግሞ ክልሎች የተካለሉበት መንገድ አስተዳደራዊ አመችነቱን ሳይሆን ጎሳን እና ቋንቋን መሰረት ያደረጉ ናቸው።በኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀፅ 48 ቁጥር 1 ላይ ''ክልሎች በመካከላቸው የሚነሳ አለመግባባት በተመለከተ የፌድሬሽን ምክር ቤት የህዝብ አሰፋፈርና ፍላጎት መሰረት በማድረግ ይወስናል'' ይላል።ይህ ማለት ግጭት ሳይፈጠር የህዝብ አሰፋፈርና ፍላጎትን መሰረት የማያደርግ እና ጎሳን መሰረት የሚያደርግ።ክልሎቹ ሲጋጩ ግን ፈድሬሽን ምክር በት የህዝብ አሰፋፈርና ፍላጎት መሰረት ያደርጋል ማለቱ በራሱ ግራ የሚያጋባ ነው።ክልሎች በሕዝቡ ፍላጎት መሰረት ለመከለል መጋጨት ያለባቸው ይመስላል።

የጎሳ ፖለቲካ እና ጎሳን መሰረት ያደረገው ፖለቲካ ለማስተካከል አንዱ የሚነሳው ጉዳይ የሕገ መንግስቱ መሻሻል ነው።ሕገ መንግስቱ አንቀጽ 105 ሕገ መንግሥቱን ስለማሻሻል የሚከተሉትን ነጥቦች ያስቀምጣል።

1 በዚህ ሕገ መንግሥት ምዕራፍ ሦስት የተዘረዘሩት መብቶችና ነጻነቶች በሙሉ፣ይህ አንቀጽ፣ እንዲሁም አንቀጽ 104 ሊሻሻሉ የሚችሉት በሚከተለው አኳሁአን ብቻ ይሆናል፡፡ 

ሀ/ ሁሉም የክልል ምክር ቤቶች የቀረበውን ማሻሻያ በድምጽ ብልጫ ሲያጸድቁት፣ 
ለ/ የፌዴራሉ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያጸድቀው፣ እና 
ሐ/ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ ማሻሻያውን ሲያጸድቀው ነው፡፡ 

2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 ከተዘረዘሩት ውጭ ያሉት የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ሊሻሻሉ የሚችሉት በሚከተለው አኳኊን ብቻ ይሆናል፤ 
ሀ/ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በጋራ ስብሰባ በሁለት ሦስተኛ ድምጽ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያጸድቁት፣ እና 
ለ/ ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎቸ ምክር ቤቶች ውስጥ የሁለት ሦስተኛ ክልሎች ምክር ቤቶች በድምጽ ብልጫ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያጸድቁት ነው፡፡ ይላል።

ለማጠቃለል ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት  የጎሳ ፌድራሊዝምን ለማገድ ሀገራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታም ይፈቅድላታል።በሀገር ውስጥ የጎሳ ጠበቃው እና ትርምስ ለመፍጠር በብዙ ወንጀሎች የጠነከረው የፅንፈኛው የህወሓት ቡድን በኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት መደምሰሱ፣በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ የጎሳ ፖለቲካ የመሰደዱ፣የመገደሉ፣የእርስ በርስ ግጭት እና አጠቃላይ መጪውን ጊዜ የሚያጨልም ብቻ ሳይሆን ወደ አደገኛ የጥፋት መንገድ የሚወስድ መሆኑን ከምንጊዜውም በላይ በተግባር ያረጋገጠበት መሆኑ፣የአፍሪካ ሀገሮች በተለይ ከሳሃራ በታች ያሉ ሀገሮች የኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካ ወደ ሀገራቸው የውስጥ የጎሳ ቁርሾ ተምሳሌት እንዳይሆን ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ጥያቄ ይዞ እንዳይመጣ በስጋት ሲያዩት የነበረ መሆኑ እና የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በመተከል ሰሞኑን የተፈፀመው እልቂት ተከትሎ ኢትዮጵያ በጎሳ ፖለቲካ ላይ የምትወስደው እርምጃ ተደማጭ ነቱን ይጨምረዋል ብቻ ሳይሆን እርምጃውን ለመውቀስ ሊያነሱት የሚችሉት የሞራል ጥያቄ ሊኖር አይችልም።ስለሆነም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ የጎሳ ፖለቲካን ለማገድ ከሕገ መንግሥቱም አንፃር ያለውን ቀዳዳ በሙሉ ተጠቅመው በተግባር ላይ የሚያውሉበት ወርቃማ ጊዜ አሁን ነው።
===========================
ማስታወቂያ 
============
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ የሚችሉበት አዲስ ቴክኖሎጂ ጉዳያችን ማስተዋወቅ ጀምራለች።
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ - 


No comments:

Beynouna Village - Ethiopia (Video) ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሃራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)

Beynouna Village - Ethiopia (Video) ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሐራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)