ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, April 27, 2020

እናመሰግናለን! እንልመድ።ጉዳያችን አራት የኢትዮጵያ ሰዎችን ዛሬ ልታመሰግን ትወዳለች።

የኛ ማኅበረሰብ አንዱ ችግር መልካም ላደረገ እናመሰግናለን ከማለት ይልቅ ትንሽ ስህተት ለማግኘት ብዙ የሚደክም  መሆኑ ነው።ይህ ደግሞ ከቤተሰብም የማመስገን ባሕል አለመውረስም ጭምር ነው።እቤት ውስጥ ሲመሰጋገኑ እያዩ አለማደግ በራሱ ይዞ የመጣው ችግር አለ።አባት ልጁን ካመሰገነ የበለጠ እንዳይሰራ አኮራዋለሁ ብሎ ያስባል፣እናትም ልጇን ማድነቅ እና መመስገን ያዘናጋዋል ብላ ታስባለች።ይህ ሁሉ ወደ ባሕላችን እየገባ ነው። የማኅበራዊ ሚድያውም ከባሕላችን ውጪ አይደለም።የኛው ነፀብራቅ ነው።እስኪ ማመስገን እንልመድ።
የሚለፉትን ማመስገን ጤናማነት ነው።

ከእዚህ በታች የምትመለከቷቸውን እንደናሙና ነው ያቀረብኩት።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ሊመሰገኑ ይገባል



በእዚህ በኮሮና ወረርሽኝ ዘመን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ነገ ስንት አስከሬን ይቆጠር ይሆን? ነገ ከቀውስ ኢትዮጵያን እንዴት ማውጣት ይቻላል? እያሉ ሌት ከቀን መጨነቅ ምን ማለት እንደሆነ ካልገባን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይን እንዴት ማመስገን እንችላለን? በእርሱ ቦታ ስንት ጉዳዮች እንቅልፍ አሳጥተው እንዲሰራ እያደረጉት መሆኑን ካልገመትን እንዴት ማመስገን እንችላለን።ይህንን ካላሰብን ነው ጥቃቅን ነገር እየፈለግን ባልተጨነቀ እና ግዴለሽ አዕምሮ ውስጥ ሆነን የፈለግነውን እየፃፍን አሉታዊ ነገር ስናደምቅ የምንውለው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የጎደለባትን በየአገሩ እየደወሉ መጠየቅ፣የአገር ውስጥ የዕለት ከዕለት ጉዳይ መከታተል፣በየክልሎች ያለው ጉራማይሌ የስልጣን ጥማት እና የፅንፍ ኃይሎች ተንኮል ሁሉ ጋር መሟገት ምን ያህል እረፍት ነሺ ሥራ መሆኑ ካልገባን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማመስገን አንችልም።

ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ወሳኝ ጊዜ ላይ ኮሮና ሲከሰት የነበረ ዕቅድ በሙሉ ሰርዞ ወይንም አቆይቶ አዲስ የአደጋ ጊዜ ዕቅድ አውጥቶ መምራት ምን ያህል አቅም የሚጠይቅ ሥራ መሆኑ ካልገባን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩን የማናመሰግነው።ስለሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩን እናመሰግናለን።

የጤና ጥበቃ ሚንስትሯ  ዶ/ር ሊያ ታደሰ ሊመሰገኑ ይገባል


በኮሮና ዘመን የጤና ሚኒስትር መሆን ምን ማለት እንደሆነ የሚሰማን የታመሙ ሰዎች ቁጥር ለመንገር ወደ ሚድያ ላይ መውጣት እና ሕዝቡን ማርዳት ምን ያህል አስጨናቂ ጉዳይ እንደሆነ ሲገባን ነው።ነገ ምን ያህል አስከሬን እንደሚያመጣ ያልታወቀ በሽታ ጉዳይ በሴት ስሜት ቀን ከሌሊት በማሰብ እና የመምራቱ ኃላፊነትም እራስ ላይ መውደቅ ምን ማለት እንደሆነ ከተረዳን ብቻ ነው።

የኮሮና ወረርሽኝ የተያዙ ቁጥር፣የዳኑ እና ያገግሙ ሁኔታ ሌሊቱን ሪፖርቱን እየጠበቁ ማደር አንዳንዴም ሌሊት ተነስቶ ሪፖርት መፃፍ ከቤተሰብ ኃላፊነት ጋር ምን ማለት እንደሆነ ሲገባን ነው የጤና ሚኒስትሯን የምናመሰግነው።ስራው የሞራል ጥንካሬ፣ትጋት እና የአደጋ ጊዜ የአስተዳደር ብቃት ሁሉ ይጠይቃል።ስለሆነም የጤና ሚኒስትሯን እናመሰግናለን።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ  አቶ ተወልደ  ሊመሰገኑ ይገባል


አቶ ተወልደን የማውቃቸው (እርሳቸው ላያውቁኝ ይችላሉ) ከሃያ ሶስት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ የገበያ ክፍል ውስጥ ባልሳሳት የዲፓርትመንት ክፍል ኃላፊ ሆነው ነው።እኔ አየር መንገድ ውስጥ ያለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞች አገልግሎት ላይ ሲመጡ እና ስናገለግላቸው አውቃቸዋለሁ።አገልግሎቱ እስኪያልቅ ድረስ ካውንተሩ ላይ ትንሽ ቆም ብለው የሚያወሩን የበሰሉ ንግግሮች አሁንም ድረስ አስታውሳለሁ።ትልቅ ዲስፕሊን ያላቸው፣ትሑት እና በወቅቱ ለእኛ ተራ የባንኩ ሰራተኞች ሳይቀር አክብሮት ያላቸው ናቸው።

እሳቸውን በሚያውቁ ሰዎችም እንደምረዳው ለእምነት እና ለሞራል ዋጋ የሚሰጡ፣ዕምነት የግል ቢሆንም አንዳንዶቻችን በእርሳቸው ቦታ ያለ ሰው ብዙ ጉዞ፣ግብዣ የሚያስተናገድ ሰው አይችልም የምንለውን በእምነታቸው  በፈቃድ እንጂ የማይገደዱበት ''የፅጌ ፆም'' በመባል የሚታወቀውን የክርስቶስን የስደት ወራት ፆም ሳይቀር የሚፆሙ፣በበርካታ ስብሰባዎች ላይ እና ዓለም አቀፍ ጉዞዎች ውስጥ ይህ የግል ዕምነታቸው የማይጣረስባቸው ግለሰብ ናቸው። ይህንን ስብዕና በሥራ ሂደት በተሰሩ የስራዎች ሂደት እያስታከኩ  ያላደረጉትን እንዳደረጉ አድርጎ ማብጠልጠት ግለሰብን ብቻ ሳይሆን አገር ይጎዳል።

በእርግጥ በአመራር ወቅት ኃይለኛ ናቸው የሚሉ ይኖራሉ።ይህንን አንድ ጊዜ ተጠይቀው የመለሱት ሚዛን ይደፋል። ''የአየር መንገድ ሥራ እንደ ወታደር ሥራ ነው። ትንሽ ካዛነፍክ ብዙ ነገር ይበላሻል ስለሆነም በሥራ አመራር ላይ ጠጠር የምለው ለእዚህ ነው።ይህም ሆኖ ግን በውሳኔ ላይ በቡድን ነው የምንወስነው።ብዙ ክርክሮች ተደርገው ነው ውሳኔዎች የሚሰጡት'' ነበር ያሉት።ይህንን አባባላቸውን በሸገር ራድዮ ምናልባት አንድ ዓመት ባልሆነው ጊዜ ውስጥ ተላልፏል።

እኝህ ሰው አሁን በቀውስ ላይ ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራ አስኪያጅ ናቸው።በብዙ ፈተና ላይ የሚገኘው አየር መንገድ በእዚህ ጊዜ ከሌላው ዓለም አየር መንገዶች በተለየ በካርጎ ንግዱ እንዲጠነክር እየሰሩ ነው።በቀውስ ውስጥ አየር መንገድ መምራት ምን ማለት እንደሆነ ካልገባን አናመሰግናቸውም።ስራው አየር መንገዱን ከቀውስ አስተዳደር አውጥቶ ወደ ነበረበት የመመለስ ትልቅ ሥራ ነው።ስለሆነም አቶ ተወልደን እናመሰግናቸዋለን።

ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የውሃ፣መስኖ እና ኢነርጂ ሚንስትርን እናመሰግናቸዋለን


በኢትዮጵያ በውሃ ቴክኖሎጂ እና ተያያዥ ሙያዎች አሉ ከተባሉ ምሁራን ውስጥ ናቸው።በዓባይ ግድብ ዙርያ ብዙ ምክረ ሃሳቦች ከመስጠት አልፈው የአካባቢው ከውሃ ጋር በተያያዘ ያለውን ጅኦፖለቲካ ጉዳይ ላይ ልምድ አላቸው።ኢትዮጵያ ከግብፅ እና ሱዳን ጋር ባደረገችው ድርድር ሚናቸው ቀላል አይደለም።የፖሊሲ አውጪዎች እንዴት ማሰብ እንዳለባቸው ቅርፅ የመስጠት ሚና እንዳላቸው ይነገራል።ከሁሉም በላይ በጠንካራ የኢትዮጵያዊነት ስሜት በግድቡ ዙርያ የሚያሳዩት ቁርጥ ሃሳብ ያስመሰግናቸዋል።''ግድቡ የእኔ ነው!'' የሚለው አባባላቸው ዛሬም ብዙዎች ጆሮ ላይ ይጮሃል።

እኚህ ሰው በዓባይ ግድብ ድርድር ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሂደቱን በማጥናት ብዙ ሌሊቶች ካለእንቅልፍ እንዳሳለፉ መገመት ቀላል ነው።ምሁርነት ማኅበራዊ ሚድያ ላይ ተቀምጦ መሪዎችን ከመስደብ እና ከመተቸት ያላለፈ ሥራ በሚሰራበት ዘመን ዶ/ር ኢንጅነር ስለሺን አለማመስገን አይቻልም።ስለሆነም እናመሰግናቸዋለን።

ባጠቃላይ በርካቶች ያላመሰገንናቸው የህዝብ አገልጋዮች አሉ።ከላይ የተጠቀሱት ግንባር ቀደም ከሆኑት ውስጥ ተነሱ እንጂ ብዙዎች ሊመሰገኑ የሚገባቸው አሉ።ማመስገን መልመድ ጤናማነት ነው።ለመንቀፍ ብቻ መሮጥ ደግሞ የመታመም ምክንያት ነው።ባለማመስገናችን መልካም የሰሩትን እናጣለን።በማመስገናችን ለበለጠ ሥራ እናተጋቸዋለን።

ጉዳያችን ሚድያ፣ኮሚኒኬሽን እና ምክር አገልግሎት 
Gudayachn Multimedia, Communication and Consultant
ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...