በቅርቡ የተመሰረተው እና ከከፍተኛ ምሁራን ባለሙያዎች እስከ ገበሬዎች ድረስ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች አባላት እንዳሉት የሚነገረው የእናት ፓርቲ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን አስመልክቶ ሶስት የመፍትሄ ሃሳቦች የያዘ ደብዳቤ ዛሬ ሚያዝያ 2፣2012 ዓም መላኩን ጉዳያችን ተረድታለች።የደብዳቤው ሙሉ ይዘት ከእዚህ በታች ያንብቡ። (ፎቶ ኮፒው በጥራት ካልተነበብልዎት፣ከኮፒው ስር በጥራት የተለጠፈውን ያንብቡ)
===========================
ለክቡር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ
ጉዳዩ፡- ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችንን ተጠቅመን ከመጣብን መዓት እንውጣ
የኖብል ኮሮና ቫይረስ(CoVID-19)በይፋ መገኘቱ ከተገለፀበት ዕለት ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቍጥር ቀስ በቀስ እያሻቀበ ሄዶ 1.5 ሚሊዮን ደርሷል፤ የሟቾችም ቍጥር ከ80 ሺህ አልፏል፡፡ በሀገራችንም የታማሚዎች ቍጥር ከ50 እንዳለፈ ታውቋል፡፡ ማኅበረሰባችን ወደ ጤና ተቋማት ሄዶ የመመርመር ባህሉ በሽታ በእጅጉ ሲፀናበት ብቻ መሆኑና የምርመራ ማእከላት አነስተኛ ከመሆናቸው የተነሳ የተመረመረው ሰው ቍጥር አነስተኛ በመሆኑ በቫይረሱ የተያዘው ሰው ቍጥር በኦፊሴል ከሚነገረው ከፍ ሊል እንደሚችል መገመት አዳጋች አይደለም፡፡ ካለን የምጣኔ ሀብት እድገት፣ አነስተኛ የሐኪሞች ቍጥር፣ ውስን የመመርመሪያ መሣሪያ ላይ የጠነከረ ማኅበራዊ መስተጋብር ሲጨመርበት የችግሩ ስፋት
የኖብል ኮሮና ቫይረስ(CoVID-19)በይፋ መገኘቱ ከተገለፀበት ዕለት ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቍጥር ቀስ በቀስ እያሻቀበ ሄዶ 1.5 ሚሊዮን ደርሷል፤ የሟቾችም ቍጥር ከ80 ሺህ አልፏል፡፡ በሀገራችንም የታማሚዎች ቍጥር ከ50 እንዳለፈ ታውቋል፡፡ ማኅበረሰባችን ወደ ጤና ተቋማት ሄዶ የመመርመር ባህሉ በሽታ በእጅጉ ሲፀናበት ብቻ መሆኑና የምርመራ ማእከላት አነስተኛ ከመሆናቸው የተነሳ የተመረመረው ሰው ቍጥር አነስተኛ በመሆኑ በቫይረሱ የተያዘው ሰው ቍጥር በኦፊሴል ከሚነገረው ከፍ ሊል እንደሚችል መገመት አዳጋች አይደለም፡፡ ካለን የምጣኔ ሀብት እድገት፣ አነስተኛ የሐኪሞች ቍጥር፣ ውስን የመመርመሪያ መሣሪያ ላይ የጠነከረ ማኅበራዊ መስተጋብር ሲጨመርበት የችግሩ ስፋት
ያስጨንቃል፡፡
አሁን በጤናችን በኩል የመጣ ጠላት ጋር ጦርነት ውስጥ ነን፡፡ መሽነፍ ደግሞ የኢትዮጵያውያን ባህል አይደለም፣ ሥነልቡናችንም አይፈቅድም። ይህ ከሆነ መጪው ትውልድ ይታዘበናል፤ ታሪክም ይፈርድብናል፡፡ በዚህ ረገድ ሌሎች ሀገራት ይህን ጦርነት ከመቆጣጠር አኳያ የዘየዱትን መላ መመልከት ተገቢ ሲሆን የወረርሽኙ መነሻ የሆነችው ቻይና፣ በኋላም ጃፖን እንዴት አድርገው ወረርሽኙ በተከሰተበት ግዛት እንዲገደብ ብሎም በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ እንዳደረጉ ትምህርት መውሰድ ያሻል፡፡
ወረርሽን ከአፍሪካ አህጉር አንጻር ሲታይ እጅግ ፈታኝ መሆኑ አሌ አይባልም። የአኗኗር ዘይቤ፣ የማኅበረሰብ ቁርኝት፣ የጤና ሽፋን፣ የሐኪምና ታማሚ ምጣኔ፣ የሕክምና መሣሪያ እጥረት ባለበት ሁኔታ ምን ያህል አደጋ ሊሆን እንደሚችል መረዳት መረዳት አያዳግትም። በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እኛ አፍሪካውያን በአጠቃላይ እና ኢትዮጵያውያን በተናጠል የምንኮራባቸው ለሌሉቹም አህጉራት ተምሳሌት ሊሆኑ የሚችሉ የማኅበረሰብ እሴቶች አሉን፡፡ ለምሳሌ ደቦ፣ እድር፣ ድርጎ፣ ኡቡንቱ፣ ... የመሳሰሉ እምቅ እሴቶች ማኅበረሰቡ ከሚመጡበት ማንኛውም ችግርና አደጋ በመተሳሰብ፣ በመረዳዳት፣ በአንድነት ለአንድ የጋራ ዓላማ የሚቆምበት ዘመን ጠገብ መሣሪያዎቹ ናቸው፡፡
አህጉራችንም ሆነ ሀገራችን ከገጠማቸው ችግር ለመውጣት የመንግስት ድርሻ ከፍ ያለ መሆኑ ቢታወቅም እነዚህን እሴቶች በአግባቡ መጠቀም የገጠመንን ፈተና ለመወጣት የምናደርገውን ጥረት በእጅጉ ይረዳል፡፡ ወረርሽኙ ከዚህ ቢሰፋ የሚያስከትላቸው አሉታዊ ተጽዕኖዎች እንደ የቤት ኪራይ መጨመር፣ የገበያ ዋጋ መናር፣ የደሞዝ መቋረጥ፣ የቤት መልቀቅ፣ የሚላስ የሚቀመስ ማጣት ሆነ ሌሎች ተያያዥ ችግሮች በኢትዮጵያዊ እሴቶቻችን የሚፈቱ ጉዳዮች ናቸው፡፡ የማኅበረሰባችን ችግር በማኅበረሰባችን መፍትሔ ያገኛል የሚለው እሳቤ ዘለቄታዊ መፍትሔ ከማምጣቱ ባሻገር ማኅበረሰቡ ጉዳዩን በባለቤትነት እንዲይዘው ያደርጋል ብለን እናምናለን፡፡ ለዚህም፡
በመጀመሪያ ወረርሽኙ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዳይስፋፋና ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን የበሽታውን ሥርጭት ባለበት መገደብ ያሻል፡፡ ከዚህ አኳያ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚተገበር በባለሙያዎች የተጠናና ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በውል ያገናዘበ እንቅስቃሴን የመገደብ ሥራ /Declaring Total Lock-down/ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆን ግን የማኅበረሰቡን የመኖር ሕልውና ማገናዘብ አለበት እንላለን፡፡ወደተግባር ሲገባም ከእጅ ወደአፍ ኑሮ የሚገፋው ማኅበረሰብ በእጅጉ ይጎዳል፡፡ በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችን በተግባር ማዋል ለመጫው እጅጉን ይጠቅማል፡፡ በዕለት ምግብ እርዳታ ለማለፍ የሚገደዱ ዜጎች ቍጥር በየቀበሌው በአስቸኳይ በስልክ እንዲመዘገብ ወይንም ጎረቤቱ እንዲያስመዘግበው ማድረግ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ገደቡ በሚጸናበት ጊዜ ሁሉ የአንድን ሰው የዕለት ምግብ ፍጆታ በየዕለቱ መሸፈን የሚችለውን የኅብረተሰብ ክፍል እንዲሁ መመዝገብ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሥራ ሕዝቡ የዕለት ምግብ ፍጆታ በማበርከት በየቀኑ መትጋትን ሲጠይቅ መንግሥት የራሱን ተሽከርካሪዎች ጨምሮ በጎ ፈቃደኛ ባለመኪናዎችንና ሌሎች ማጓጓዣ ስልቶችን በማስተባበር የዕለት ምግብ እርዳታው ከለጋሾች ወደሚፈለግበት ማድረስን መደበኛ ሥራ ማድረግ ይጠይቃል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ዘመናዊውን ሕክምና ከሀገር በቀሉ የዳበረ የሕክምና ጥበብ ጋር በማጣመር መፍትሔ መሻት ነው፡፡ እንደእኛ ዓይነት ነባር እውቀትና በባህል ሕክምና ለሺህ ዓመታት ሲሠራበት ለኖረ ማኅበረሰብ የጊዜውን ትሩፋት መጠበቅ እንዳለ ሆኖ እገረ መንገዱን ነባሩን እውቀትና አዋቂዎች መዝገብ ገለጥ ገለጥ ማድረግ ለነገ የሚባል አይደለም፡፡ አዳፍነነው ስለኖርን ይህ እንኳን መንገዱ ረጅም ነው ቢባል ከየባህሉና መልክዓ ምድሩ የሚበቅሉ ለእንዲህ ዓይነት ወረርሽኝ መታገያ አቅም የሚሆኑ አዝርእትን አፈላልጎ የትግሉ አካል ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ በዚሁ አጋጣሚ የባህል ሕክምና ሕግና ሥርዓት ተበጅቶለት ከዘመናዊው ሳይንስ ጋር ተቀናጅቶ የሌላው ወገን ይሁንታ እንዳለ ሆኖ ሲያዋጣን ግን በፍጥነት መጠቀሙ አስፈላጊ ነው፡፡
ሦስተኛው ይህ ጊዜ ሲያልፍ /Post Corona/ የምንሆነው ከአሁኑ መታሰብ አለበት፡፡ የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት፣ የአልሚው ሁኔታ፣ የማኅበረሰቡ ሥነልቡና፣ የአምራች ኃይሉ የመሥራት ፍላጎት፣ የሸማቹ ፍርሃት፣ የተማሪው የመማር ዝግጁነት፣ ዳግም ማኅበራዊ ቅርርብ፣... ወዘተ በተጎዳ ሥነልቡናና እንደአዲስ በሚጀመር አኳኋን ነው የሚመለሱት፡፡ ይህም የችግሩ አካል እንደሚሆን አድርጎ ማሰብና ከወዲሁ ትልቅ ሥራ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ ለዚህም የሃይማኖት ተቋማት የሰውን ሥነልቡና ከፍ በማድረግና ባለበት ሁኔታ ከፈጣሪው ጋር በማገናኘት የሚወጡት ሚና ቀላል አይሆንምና የተጀመረው ሀገር አቀፍ ጸሎት መልካም ሆኖ አሁንም የፖኬጁ አካል የሚሆኑ ቀሪ መርሐ ግበሮች (በክርስትናው ቅዳሴ፣ የሰንበታት አምልኮዎች፣ የሰሙነ ሕማማት ክዋኔዎች፣ በእስልምናው እንደ ጁምዐ ሰላት፣ የረመዳን ጾም ክዋኔዎች) በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የቀጥታ ሥርጭት ሽፋን እንዲያገኙ ማድርግ አስፈላጊ ነው፡፡ በሌላ በኩል የሥነልቡና አዋቂዎች፣ የፍልስፍና ምሑራን፣ ተደማጭ ኢትዮጵያውያን ጊዜና ሁኔታው ተመቻችቶላቸው ወደመድረኩ እንዲመጡ፣ ጉዳይ ተኮር ሥራ እንዲሠሩ ማድረግ ጊዜው የሚጠይቀው ነው፡፡ የምጣኔ ሀብት ምሑራን፣ በችግር ጊዜ መውጫ ሀሳብ ያላቸውን እነአባ መላን ይዞ ነገ የሚሆነውን በትክክል በመተንበይና መውጫ መንገዱንም በመተለም የምጥ ስሩን ማሳጠር አለብን፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር
ይህን የመጣብንን ታላቅ ፈተና ለመሻገር መላ ማበጀት በእርስዎና በዙሪያዎ ባሉ ባለሥልጣኖች ጫንቃ ላይ ብቻ እንዳልወደቀ ፖርቲያችን ጠንቅቆ ይረዳል፡፡ እንዲያውም እኛን ጨምሮ ብዙ ከፊት ተሰልፈው የአቅማቸውን በማድረግ የጦርነቱ ፊታውራሪ መሆን የሚችሉ ወጣቶች ስላሉ ሊኮሩ፣ ሊጠቀሙባቸው እንደሚችሉ ስንነግርዎት በደስታና ቃል በመግባት ጭምር ነው፡፡ ሆኖም በታሪክ አጋጣሚ የዚህች ውድ ሀገራችን አመራር በእርስዎ እጅ በወደቀበት በአሁኑ ወቅት ዛሬ ለብዙዎች መዳን ወይም እልቂት ነገ ስምዎ በወርቅ ቀለም ሊፃፍ ወይንም የታሪክ ተወቃሽ ሊያደርግዎ የሚያስችል ሥራ የሚሠሩበት ጊዜ ነው፡፡ ስለሆነም የሕዝባችንን የዳበረ እሴት ተጠቅመን ሀገራችን ከተጋረጠባት ጦርነት በድል ተሻግራ ብሩህ ነገን የምታይ እንድትሆን ሁሉም ሓላፊነቱን እንዲወጣና አስፈላጊው እርምጃ በአስቸኳይ እንዲወሰድ ባለብን የዜግነት ግዴታና እንደ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ እናሳስባለን፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይጠብቅ
ኃይለኢየሱስ ሙሉቀን (ዶ/ር)
ፕሬዚዳንት
.
ግልባጭ :
- ለሁሉም መገናኛ ብዙኃን አካላት ባሉበት
No comments:
Post a Comment