ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, April 1, 2020

በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ምዕመናን በአብያተ ክርስቲያናት እና መስጂዶች የማይሰበሰቡ ከሆነ መንግስታዊ ራድዮ እና ቴሌቭዥን ጣቢያዎች ለሃይማኖቶቹ የአየር ሰዓት መመደብ አለባቸው።



ጉዳያችን ሚድያ፣ኮሚኒኬሽን እና ምክር አገልግሎት 
Gudayachn Multimedia, Communication and Consultant

  • ይህንን ክፉ ጊዜ ካለምንም መንፈሳዊ ዕሴት  ለሺህ ዓመታት ፈጣሪውን የሚያውቅ ሕዝብን እንዲሁ መተው አይቻልም


ከሺህ ዓመታት ከፈጣሪው ጋር ሲገናኝ የኖረ ሕዝብ በድንገት ከእዚህ ሳምንት ጀምሮ በኮሮና ወረርሽኝ ሳብያ ማንኛውም ምዕመን ወደ መስጂድም ሆነ ወደ አብያተክርስቲያናት እንዳይሄድ መመርያ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ እና ከከፍተኛው የእስልማና ምክርቤት ውሳኔዎች ተወስነዋል።

ውሳኔዎቹ  ለሕዝብ ጤንነት ተብለው የተወሰኑ ቢሆኑም የሚያስከትሉት መንፈሳውም ሆነ ስነ ልቦናዊ ተፅዕኖ ግን ቀላል ነው ማለት አይደለም።ምዕመኑ ከሞራላዊውም ሆነ ከመንፈሳዊው ዓለም በድንገት ሲቆራረጡ እንደ ሕዝብ የሚያስከትለው ዘርፈ ብዙ ጉዳት ይኖረዋል።ከሚኖሩት ጉዳቶች ውስጥ በስነ ልቦና መድቀቅ፣ የመንፈሳዊ ሕይወት ዝለት እና የተስፋ ቢስነት ስሜቶች በቀዳሚነት ተጠቃሽ ናቸው።ስለሆነም ምዕመናኑ ወደ መስጅድም ሆነ አብያተክርስቲያናት እንዳይሄዱ ከወጣው መመርያ ጎን መሰራት ያለበት ሥራ አለ።ይሄውም ቢያንስ በአካል ሊገኝ ያልቻለ መንፈሳዊ አገልግሎት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲገኝ ማድረግ የመንግስት ኃላፊነት ነው።በኢትዮጵያ አንፃር አብዛኛው ሕዝብ ለቴክኖሎጂ መሣርያዎች ዕድል የለውም።ለምሳሌ አብዛኛው ሕዝብ የኮምፑተር ባለቤት አይደለም።ተንቀሳቃሽ ስልክ ሽፋን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ግማሹን ያህል ገና አላዳረሰም።በመሆኑም ተመራጩ መንገድ ራድዮ እና ቴሌቭዥን ይሆናል ማለት ነው።

ከመስጂድ እና አብያተክርስቲያናት የታቀበው ሕዝብ አገልግሎቱን በራድዮ እና በቴሌቭዥን በጊዜያዊነት እንዲያገኝ ማድረግ ይገባል 

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በሕዝቡ ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉትን የስነ ልቦና መድቀቅ፣ የመንፈሳዊ ሕይወት ዝለት እና የተስፋ ቢስነት ስሜቶች ሁሉ የሚያመጡትን ጉዳቶች ለማጥፋት ባይቻል ጉዳታቸውን ለመቀነስ እንደ መነሻነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ራድዮ እና ቴሌቭዥን ጣብያዎች በሚከተሉት መርሐግብሮች መሰረት የቀጥታ ስርጭት መጀመሩ አስፈላጊ ነው።ይሄውም -

  • ይሄውም በየሳምንቱ ዓርብ ከቀኑ 5:30 እስከ 7ሰዓት ከአንዋር መስጊድ የቀጥታ የጁማ መርሐግብር በኢትዮጵያ ራድዮ እና ቴሌቭዥን ማስተላለፍ ይቻላል።
  • በየሳምንቱ ዕሁድ ከማለዳው 11 ሰዓት እስከ ረፋዱ 3 ሰዓት ድረስ ደግሞ የኪዳን ጸሎት፣የቅዳሴ ጸሎት እና ትምሕርተ ወንጌል በቀጥታ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እና ራድዮ መተላለፍ ይችላል።
እዚህ ላይ ለምን በራድዮ? ቴሌቭዥን አይበቃም ወይ? ብሎ የሚያስብ ይኖራል።ሆኖም ቴሌቭዥን የሌለው ኢትዮጵያዊ  ራድዮ የማግኘት  ዕድል ስለሚኖረው እና በተለይ በገጠር እና ገጠር ቀመስ ከተሞች ራድዮ የመድረስ ዕድሉ  ከፍ ያለ ስለሆነ ነው። በሌላ በኩል በአሁኑ ጊዜ በርካታ የግል ቴሌቭዥኖች ለምን የማስተላለፍ ስራውን አይሰሩም? የሚል ሃሳብም ሊነሳ  ይችላል።ሆኖም ግን አብዛኞቹ የግል ቴሌቭዥኞች በሳተላይት ብቻ ተደራሽ መሆናቸው አሁንም ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ተደራሽ አለመሆናቸው የራሱ የሆነ ችግር ያስከትላል።

ባጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግስት ብሔራዊ ራድዮ እና ቴሌቭዥኖቹን ለእዚህ የተቀደሰ ተግባር ማዋሉ ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው። በመላው ዓለም ያሉ መገናኛ ብዙሃን በዓረቡ ዓለም ዓርብ ዕለት፣በክርስቲያኑ ዓለም ደግሞ ዕሁድ ሰንበትን ተከትለው መንፈሳዊ መርሐግብሮች አሏቸው።እንደ ኢትዮጵያ ያለች የሁለቱም ዕምነቶች አገር ለሆነች ደግሞ ሁለቱም መርሐግብሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ በብሔራዊ ራድዮ እና ቴሌቭዥን ሊቀርቡ ይገባል። ይህንን ክፉ ጊዜ ካለምንም መንፈሳዊ ዕሴት  ለሺህ ዓመታት ፈጣሪውን የሚያውቅ ሕዝብን እንዲሁ መተው አይቻልምና።

ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።