ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, April 5, 2020

በወረርሽኙ ስጋትም ውስጥ ሆነን ከአዲስ አበባ የምስራች ተሰምቷል።

ጉዳያችን ሚድያ፣ኮሚኒኬሽን እና ምክር አገልግሎት 
Gudayachn Multimedia, Communication and Consultant
=================

የሐምሌ ደመና እና ደማቁ የመብረቅ ብርሃን 

አስረኛ ክፍል እያለሁ በጣም የምናደንቀው የእንግሊዝኛ መምህር ነበር።ይሄው መምህራችን በአንድ ወቅት የጠቀሳትን የህንዶች አባባል አስታውሳታለሁ። ''በሐምሌ ጥቁር ደመና ውስጥ ብልጭታ መብረቅ አይጠፋም'' ነበር ያለው።አባባሉ በብዙ የመከራ ጊዜ ውስጥ ሁሉም ነገር መከራ ነው አይባልም።ከመከራው ውስጥ የሚወጣ መልካም ነገር ፈፅሞ አይጠፋም ለማለት ነው።እንደ መምህራችን አገላለጥ የሐምሌ ድቅድቅ ጨለማ አስፈሪ ጥቁር ሰማይ ቢታይም በመሃል ላይ ሳይታሰብ ብልጭ የሚለው ደማቅ የመብረቅ ብልጭታ መኖሩን ለመግለጥ ህንዶች የሚጠቀሙበት አባባል ነው።ይህንን ከነገረኝ በኃላ ሐምሌ በመጣ ቁጥር ጥቁር ሰማይ ስመለከት ይህንን አባባል አስታውስ ነበር።ዛሬም በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ውስጥ ሆነን አንድ መልካም ተስፋ ፈንጣቂ መንገድ አገሪቱ እየሄደች እንደሆነ ተሰምቷል።በሌላ አነጋገር በኮሮና ወረርሽኝ ሳብያ በሞት የስጋት ጥላ ውስጥም ሆነንም ከአዲስ አበባ የምስራች ተሰምቷል። 

ጉዳዩ ለአንዳንዶች ቀለል አድርገው ሊያዩት ይችላሉ።ጉዳዩ ግን ኢትዮጵያ ከ1966ቱ የየካቲት አብዮት ወዲህ ለሚገጥማት ችግር ሁሉ በአንዱ እና ዓይነተኛ  የመፍትሄ መንገድነት ተጠቅማ የማታውቀው፣ኢትዮጵያ ግን ከስሪቷ እስከ መላ ዘመኗ ሁሉ ስትጠቀምበት የነበረው መፍትሄ ነበር።ይሄውም ከተፈጥሮን በጉልበት እንቆጣጠራለን ወደ ተፈጥሮን እናለማለን ተፈጥሮን የፈጠረ አምላክንም እንለምናለን ወደሚል ወሳኝ ምዕራፍ ከዛሬ ሰኞ መጋቢት 28/2012 ዓም ጀምሮ መሸጋገሯ ማሳያ ምልክት ታይቷል።

በእዚህ መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት እንደመንግስት በባለስልጣናቱ፣የአገሪቱ ዋና ዋና መገናኛ ብዙሃን እንደ አገሪቱ አንደበትነታቸው  የፈጣሪን አምላክነት የሚዘክሩበት የእየቀን መርሃግብር ተይዟል።ስለሆነም የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ላይ እንደገለጠው   -

1ኛ) ሰኞ መጋቢት 28/2012 ዓም ከምሽቱ 3 ሰዓት ጀምሮ በሶስት የተመረጡ ቦታዎች የሃይማኖት አባቶች እና ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት የፀሎት ማስጀመርያ መርሃ ግብር ይጀመራል መርሃ ግብሩ  በኢትዮጵያ ያሉ አራቱ ዋና ዋና ቴሌቭዝኞች ማለትም ኢቲቪ፣ፋና፣ዋልታ እና አዲስ ቲቪ በቀጥታ ያስተላልፉታል።

2ኛ) የፀሎት እና የሃይማኖት አባቶች የትምህርት መርሃግብር ከሰኞ መጋቢት 28/2012 ዓም ጀምሮ በእየቀኑ በሚወጣው መርሃግብር መሰረት ለአንድ ወር ያህል የሚቀጥል ሲሆን መርሃግብሩን በሙሉ ከምሽቱ 3 ሰዓት እስከ 4 ሰዓት ድረስ ኢቲቪ፣ፋና፣ዋልታ እና አዲስ ቲቪ በቀጥታ ያስተላልፉታል።


3ኛ) የጸሎት እና የትምህርት መርሃግብሩ ዋና  ዋና ዓላማዎች 

  ሀ)  ምእመናን ለእውነተኛ ንስሐ እንዲነሱ ለማድረግ እና 
  ለ) ምእመናን መንፈሳዊ ሕይወታቸውን በማጠናከር ዓለምአቀፍ ወረርሽኝ በፈጣሪ ፍቃድ እንዲነሳ ሁሉም በየእምነቱ በፀሎት እንዲበረታ  እና መንፈሳዊ እና ስነልቦናዊ ጥንካሬ ለመስጠት መሆኑ ተጠቅሷል።


ይህ ለኢትዮጵያ ምን ማለት ነው?

ይህ ለኢትዮጵያ ታላቅ ደስታ ነው።ምናልባት አንዳንዶች የሃይማኖታዊውን ጉዳይ ዋጋ ለማይሰጠው፣ምናልባትም ''በግራ ግንፍ'' አስተሳሰብ ውስጥ ለተዘፈቀ ሰው ጉዳዩ ትርጉም ላይሰጠው ይችላል።የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን፣የኢትዮጵያ የቤተመንግስት ሰዎች ኢትዮጵያ ለመጣባት ፈተና ሕዝብ በእየእምነቱ ይፀልይ ብለው ሲንበረከኩ ማየት እና መስማት በራሱ ኢትዮጵያ ከ46 ዓመታት በኃላ የመጀመርያ ተግባር ነው።ኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቀችው በእግዚአብሔር ፊት ተንበርክካ ነው።የኢትዮጵያ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን የእግዚአብሔርን ነገር በቀጥታ ሲያስተላልፉ አሁንም ከ46 ዓመታት በኃላ  ይህ የመጀመርያ መጀመርያ ነው።ስለሆነም ኢትዮጵያ ወሳኝ የአስተሳሰብ ለውጥ መኖሩን የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን  የትውልድ ሽግግር ሂደትም ነው።ሽግግሩ ከስር የጀመረ ለመሆኑ አንዱ ማሳያ አድርጎ መውሰድም ይቻላል።

ጅማሮው መርሳት የሌለበት ጉዳይ  

ይህ መልካም ጅማሮ ለአንድ ወር እንደሚቆይ ነው የተነገረው።ይህ በራሱ ጥሩ ነገር ሆኖ፣ነገር ግን ከአንድ ወር በኃላ ሁኔታው ከተሻሻለ ለችግር ጊዜ ብቻ አልቅሰን በኃላ ነገር ዓለሙ እንዳይረሳ ጅማሮው በቀጣይ ከኃይማኖታዊው ጉዳይ አልፎ የህዝብ ሞራላዊ እና ስነልቦናዊ አቅም በሚገነባ መልኩ መቀጠል አለበት። ስለሆነም የሚከተሉት ተግባራት ከግንዛቤ ውስጥ ቢገቡ መልካም ነው።እነርሱም -

1) ዓርብ እኩለ ቀን ለሙስሊሞች የጁማ መርሃግብር የቀጥታ የቴሌቭዥን እና ራድዮ ስርጭት ቢኖር ፣

2) እሁድ ማለዳ ከ11:30 ጀምሮ የኪዳን ጸሎት፣ፀሎተ ቅዳሴ እና ትምህርተ ወንጌል እስከ ረፋዱ 4 ሰዓት ድረስ የቀጥታ ራድዮ እና ቴሌቭዥን ስርጭት ቢኖር፣(ዛሬ በአዲስ ቲቪ የተጀመረው መልካም ጅምር ቢሆንም ከአዲስ አበባ ባለፈ እስከ ዳር አገር አይደርስም ይህ ደግሞ ቀረጥ ከፋዩን ሕዝብ እኩል ማገልገል ያለባቸው መገናኛ ብዙሃንን አቅማቸውን ይወስነዋል)፣

3) ስርጭቶቹን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ (ካለ ሳተላይት ዲሽ ጭምር መከታተል እንዲችል) አብዛኛውን የኢትዮጵያ ክፍል የሚሸፍኑ ብሔራዊ ራድዮ እና ቴሌቭዥን እንዲያስተላልፉ ቢደረግ።እዚህ ላይ ራድዮ በአዲስ አበባ ካለ እንበል አንድ የቀን ሰራተኛ እስከ ሊስትሮ፣በገጠርም እስከ ገበሬው ድረስ የመድረስ አቅም ስላለው የሳተላይት ቴሌቭዝኖችን ብቻ ማዳረሱ አብዛኛውን ሕዝብ እንዳያጣ ያሰጋል። 

4) ወደፊትም ይህ አገልግሎት ቢያንስ በሳምንት በሚሰጡ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች እንዲቀጥል መንግስት ሁሉንም የኢትዮጵያ ክፍል የሚሸፍን ቻናል የአየር ሰዓት በመስጠት መጪው ትውልድ እግዚአብሔርን የሚፈራ እንዲሆን የሚሰሩ ስራዎችን ከአሁኑ መልክ ባለው መንገድ ማቀድ አለበት።ይህ ካልሆነ ወረርሽኙ ሲነሳ ብቻ ወደፈጣሪ የምንንበረከክ ወረርሽኙ ሲቀል ግን  የምንተወው ፕሮጀክት እንዳይመስል መጠንቀቅ ይገባል። ምክንያቱም በምድር ላይ ስንኖር የነፍስ ጉዳይ አለ።በኢትዮጵያ ነፍስ ወደፈጣሪዋ እንደምትጠራ የሚጠራጠር ሕዝብ የለም።የነፍሱ ጉዳይ የተያዘለት ሕዝብ ነው በራስ መተማመን መንፈስ ለአገሩም ሆነ ለዓለምም የሚተርፍ ሥራ የሚሰራው።

ለማጠቃለል ኢትዮጵያ ከአርባ ስድስት ዓመት በኃላ ለመጀመርያ ጊዜ ብሔራዊ ቴሌቪዥኖቿ የፈጣሪን ነገር ሊናገሩ፣የሃይማኖት አባቶቿ በይፋ ሕዝብ ሊመክሩ ነው።ይህ ኢትዮጵያ ለግማሽ ክፍለዘመን ለቀረበ ዓመታት በማያምኑ መሪዎች ተተብትባ ህዝቡ የሚሄድበት እና መንግስት የሚሄድበት መንገድ ተለያይቶ ኖሯል።አሁን ወደ የሰውነት ማዕረግ እየተመለስን ነው።ወደ ሰውነት ስንመለስ ኮሮና ቫይረስ አይደለም ሌላ ምድራዊ ፈተናም የመሻገር አቅማችን ብቻ ሳይሆን ለዓለም የመትረፍ አቅማችን በቅርቡ የሚታይበት ጊዜ እንደደረሰ አመላካች ሂደት ነው።በዘመኔ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ስለ እግዚአብሔር ሲነገርበት ማየት የምናፍቀው አንዱ ጉዳይ ነበር።ለእዚህም እግዚአብሔር ይመስገን።እግዚአብሔር ደግሞ ዝም አይልም።ይሰማናል።''ጆሮን የተከለው አይሰማምን? ዓይንን የሠራው አያይምን?'' መዝሙር 94፣9

ቅያሜው ይቅርና አምላክ ሆይ ታረቀን በዘማሪ ይልማ ኃይሉ 






ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።