ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, April 24, 2020

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን አስረኛ ዓመቱን እያከበረ ነው።የኢሳት ቦርድ አስረኛ ዓመቱን ምክንያት በማስመልከት መግለጫ አውጥቷል።ሙሉ መግለጫውን ያንብቡ።



የዛሬ አሥር  ዓመት በሶስት የዓለማችን ታላላቅ ከተሞች ቢሮዎች ከፍቶ ስራውን የጀመረው ኢሳት፣በኢትዮያ የሚድያ ታሪክ ውስጥ በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር፣በጉዳዮች ላይ የጋራ ግንዛቤ እንዲወስዱ በማድረግ እና ትክክለኛ መረጃ በመስጠት እና መረጃውም በውጭ እና በአገር ውስጥ እስከ ትንሿ የገጠር መንደር ድረስ በራድዮ እና በሳተላይት በመድረስ ታላቅ ገድል የፈፀመው ኢሳት አስረኛ ዓመቱን እያከበረ ነው።ከእዚህ በታች የኢሳትን አስረኛ ዓመት በማስመለከት የኢሳት ቦርድ ያወጣው መግለጫ ይመልከቱ።
====================================
  የኢትዮጵያሳተላይትቴሌቪዥን


__________________www.ethsat.com__________________
Holland : Washington DC : Addis Abeba

   

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ራድዮ  (ኢሳት) የተመሰረተበትን 10ኛ  ዓመት አስመልክቶ ከኢሳት ቦርድ የተሰጠ መግለጫ

የዛሬ አስር ዓመት የነበረውን የኢትዮጵያ ተጨባጭ እውነት መለስ ብለን ስናስብ ሀገራችን መፈናፈኛ በሌለው አፈና የተዘጋችበትና ሕዝባችን ምንም ዓይነት መረጃ እንዳያገኝ ዙሪያ ገባው የተደፈነበት የድቅድቅ ጨለማ ወቅት ነበር። ሕዝብን ከመረጃ በመነጠል አደንቁሮ ለመግዛት የተዘረጋውን የአፈና መረብ ለመበጣጠስና ያለመረጃ ፍሰት የሕዝብ ነጻነት ሊመጣ  እንደማይችል በተረዱ ቆራጥ የሕዝብ ወገንተኞች ጥረት የኢትዮጵያዊያን ሁሉ የጋራ ድምጽ ለመሆን  ኢሳት ሊወለድ ችሏል። የኢሳት መመስረት ለመረጃ አልባው ሕዝባችን ትልቅ ብስራት የነበረውን ያህል ድንቁርናንና አፈናን እንደ አይነተኛ የመግዢያ ዘዴ ለሚጠቀሙት ጨቋኞች ከፍተኛ መርዶ ነበር። በመሆኑም አፋኙ ገዢ ቡድን ስርጭቱን በማፈን፣ በዲፕሎማሲ፣ በገንዘብ ኃይል፣ በውስጥ ቡርቦራና በሌሎችም መንገዶች ተቋሙን ገና በጠዋቱ የማዘጋት የሞት ሽረት ዘመቻ የከፈተ ቢሆንም ሕዝባችን ነጻ መረጃ ማግኘት አለበት ብለው የተነሱት የሕዝብ ወገኖችና ከጀርባ በደጀንነት የተሰለፈው ደጋፊ ተባብሮ ተቋሙ በጠላቶች ዘንድ በተዘመተበት ሁኔታ ሳይወድቅ እነሆ አስር ዓመታትን መዝለቅ ችሏል። ኢሳት ከተመሠረተ በኋላ በአንድ በኩል ሰቆቃዊ በሆነ የመስዋእትነት መንገድ መረጃዎችን እየሰበሰበ ለሕዝብ በማድረስ፣  በሌላ በኩልም ከአፈና ሥርዓቱ ጋር ያደርግ የነበረው ግብግብ ፈታኝ የሚባል ብቻ ሳይሆን የሚገፋ በማይመስልበት በዚያ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ በሠራው ያልተቋረጠ የሕዝብ ወገንተኝነት ሥራ ሕዝባችን እንዲደራጅ፣ ለነጻነቱ እንዲታገልና መብቱን እንዲጠይቅ ብሎም እንዲያስከብር ከፍተኛ የማንቃት ሥራ  ለረጅም ጊዜ በብቸኝነት  ሠርቷል። 

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከዳር ላደረገው የአልገዛም ባይነት ትግል እና ተያይዞ ለተገኘው ሀገራዊ ለውጥ ኢሳት በመረጃ አቅራቢነትና አሰራጭነት በግንባር ቀደምነት ያደረገው አስተዋጾ ሁሉም የሚመሰክረው ሀቅ ነው። ኢሳት የጭቁኑ ሕዝባችን ድምጽ መሆን ብቻም ሳይሆን ሌሎች ሚዲያዎችም ፈለጉን ተከትለው እንዲከፈቱና እንዲስፋፉ በኢትዮጵያ ሚዲያ ታሪክ የፋና ወጊነት ሚናም የተጫወተ ነው። ኢሳት ከጽንሱ ጀምሮ ዓላማውን በሁለት ዙር ከፍሎ ነው የተንቀሳቀስውም። ኢሳትና ደጋፊዎቹ በመጀመሪያው ዙር ዓልመው የተገበሩት የወያኔ መራሹን አገዛዝ ከሕዝቡ ጫንቃ ማስወገድ ከሞላ ጎደል በስኬት ተገባዷል ማለት ይቻላል።

የሚቀጥለውና ሁለተኛው ዙር የኢሳትና የደጋፊዎቹ ሥራ በኢትዮጵያና በአካባቢዋ ወደፊት ተራማጅ፣ ዲሞክራቲክ፣ የበለጸገና  ፍትሐዊ ሕብረተሰብን ለመገንባት በሚደረገው ጉዞ ተቀዳሚ የመረጃና የዕውቀት ምንጭ ሆኖ የመገኘት የረጂም ጊዜ ራዕይ ላይ የተመሰረተ ነው። ከራዕዩ ለመድረስም በኢትዮጵያችን ንቁና ብሩህ የሆነ ዜጋን ማፍራትን ግድ ይላል። ኢሳት በተሰማራበት የሚዲያ ማምረትና ማከፋፈል ሥራ አማካኝነት፤

  • በባህል ብዛሃነትና በእጅጉ በካበተ ታሪካዊ ማንነት ላይ የተመሠረተ፣
  • በሀገሩና በዓለም ጉዳይ ላይ በበቂ መረጃ ያለው፣
  • በሀገሩ ህብረተሰባዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ሙሉ ተሳትፎ የሚያደርግ፣
  • ለዲሞክራሲያዊ እሴቶችና መርሆች የጸና አቋም ያለው ዜጋ ማፍራትና ማበራከትን እንደዋና  የሥራው ዓላማና ተልዕኮ አድርጎ ሥራ ጀምሯል።
 እነዚህን ጥልቅ ማህበራዊ ለውጦች እውን ለማድረግ  በሚዲያ በኩል የሚያስፈልጉትን ግብአቶች ቀስበቀስ ለማሟላት ኢሳት ከአሁን ጀምሮ በውስጥ አደረጃጀት፣ በዘመናዊ ማነጅመንት፣ በፕሮፌሽናል ጋዜጠኝነትና በልዩ ልዩ የፕሮግራም ይዘቶች ፈጠራና ስርጭት ክህሎት የሚያስፈልጉትን የሰውና የቁሳቁስ ዓይነቶች የማግኘት ተግዳራቶች ተገንዝቦ መሄድ እንዳለበት ያውቃል። በአሁኑ ወቅት የኢሳት ቦርድና የኢሳት ልዩ ልዩ የሥራ ዘርፎች ኢሳትን ወደዚህ ብቃት የሚሸጋግሩትን ተግባሮች እያከናወኑ ይገኛል። 
በመሆኑም በዚህ መልክ ዛሬ በጠንካራ መደላድል ላይ የምንተክለው ኢሳት ከትውልድ ትውልድ በአርአያነት የሚያገለግል የሕዝብ ተቋም እንደሚሆን እንተማመናለን።
ዛሬ የኢሳትን አስረኛ ዓመት በምናስብበት ወቅት ዓለምን የገጠመው የኮሮና ወረርሽኝ በሀገራችን የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ሕዝባችን ከተገቢው ምንጭ የመረጃ አቅርቦት እንዲያገኝና ግንዛቤ እንዲሰፋ የሚዲያ  ሚናውን በተገቢው ለመወጣትና ሕዝቡን ለማገልገል ያለመታከት እየሠራ ይገኛል። 
በመጨረሻም ከፍ ባለ አጽኖት የምናነሳው ታላቅ ቁም ነገር ቢኖር ኢሳት ፈተና ባልተለየው የአስር ዓመት ጉዞው ወቅት በሀገር ውስጥ መረጃ ከማቀበል አንስቶ በጋዜጠኝነት፣ በካሜራና ቴክኒክ፣ በአስተዳደር ብዙዎች ተዘዝሮ የማያልቅ ዋጋ ከፍለዋል። በመላው ዓለም ያሉ ደጋፊዎች በዚህ ሁሉ ጊዜ የጀርባ አጥንት ሆነው ተቋሙን ለዛሬ አብቅተዋል። በዚሁ አጋጣሚ ሁላችሁንም እንኳን ለኢሳት 10ኛ ዓመት ምስረታ አደረሳችሁ እያልን ያለእናንተ ድጋፍ ኢሳት አስር ዓመት ሊዘልቅ የሚችልበት አቅም አልነበረውምና  ላደረጋችሁት ታሪክ የማይረሳው አስተዋጽኦ በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርብላችኋለን። 
ስናጠቃልልም የኢሳት ራዕይ የጋራ ሀገራችንንና ሕዝባችን ነው። የምንጓዘው መንገድ ከመጣንበት ይረዝማል። ሀገራችን ስጋትም ተስፋም የተፋጠጡባት ናት። በዚህ ዓይነት ሀገር ፈተና ውስጥ ባለችበት ወቅት እንደኢሳት አይነት ስለሁላችንም ሀላፊነት የሚሰማው ሚዲያ የግድ ይላል። ነገ ለምናልማት ኢትዮጵያም ጠንካራ ሀገራዊ የጋራ ራዕይ ያለው ሚዲያ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግድ ነው። ኢሳት ሀገራዊ የሚዲያ ሀላፊነቱን የሚወጣ ጠንካራ ተቋም እንዲሆን በሙሉ ልብ እየሠራን መሆኑን እያረጋገጥን ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ኢሳትን በመደገፍ ረገድ እንደትናንቱ ሁሉ ዛሬም አብራችሁን እንድትቆሙ ጥሪ እናደርጋለን።

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!! 
ኢሳት የኢትዮጵያ ሕዝብ አንደበት፣ ዓይንና ጆሮ ሆኖ ይቀጥላል!!
የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ራድዮ (ኢሳት) ቦርድ            




ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments: