ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, March 11, 2019

አዲስ አበባ በራሷ ፍልስፍና ነች።ፍልስፍናዋን የመጠበቅ ታላቅ ሀገራዊ እና ታሪካዊ አደራ ተጥሎባታል።

የአዲስ አበባ ጉግል ካርታ እኤአ 2019 ዓም 

ጉዳያችን / Gudayachn 
መጋቢት 3/2011 ዓም (ማርች 12/2019 ዓም)
==================================
በእዚህ ፅሁፍ ስር  የሚከተሉት ርዕሶች ይገኛሉ። 
አዲስ አበባ ማን ነች?
አዲስ አበባ የኢትዮጵያ መርገም እና መርገም ያረፈባት የኢትዮጵያ አሻራ
አዲስ አበባ በበቀል በትር ስር 
አዲስ አበባ ፍልስፍና ነች  እና 
- ቪድዮ (ከቦሌ እስከ ፒያሳ አራዳ እና ከጀሞ እስከ ፒያሳ አራዳ የአውራ ጎዳና ጉብኝቶች)
=================================
አዲስ አበባ ማን ነች?

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፊት ድረ ገፅ ላይ አዲስ አበባን ሲገልጣት እንዲህ የሚለው ፅሁፍ በቀዳሚነት ሰፍሯል።    
''አዲስ አበባ ተብላ የተሠየመችው እቴጌ ጣይቱ ኅዳር ፲፬ ቀን ፲፰፻፸፱ ዓ/ም ፍልውሃ ፊል-ፊል ወደሚልበት መስክ ወርደው ሳሉ ከዚህ በፊት አይተዋት የማያውቋት አንዲት ልዩ አበባ አይተው ስለማረከቻቸው ቦታውን ‹‹አዲስ አበባ!›› አሉ ይባላል። አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ስትሆን በተጨማሪ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ እንዲሁም የብዙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቅርንጫፎችና ሌሎችም የዓለም የዲፕሎማቲክ ልዑካን መሰብሰቢያ ከተማ ናት። ራስ-ገዝ አስተዳደር ስላላት የከተማና የክልል ማዕረግ ይዛ ትገኛለች። አብዛኞቹን የሀገሩ ቋንቋዎች የሚናገሩ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች የሚኖሩባት ከተማ ናት። ከባሕር ጠለል በ2500 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው ከተማ ነች።'' ይላል።


 ፖላንዳውያኑ የታሪክ ፀሐፊዎች አንድርዜይ እና ማንቴል ኒየችኮ ''የኢትዮጵያ ታሪክ ከመጀመርያው እስከ አሁን ዘመን'' በሚል በፖላንድኛ የፃፉትና በኃላ ወደጀርመንኛ በተተረጎመው መፅሐፍ ላይ አዲስ አበባ ቀደም ብላ በ13ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ ጀምሮ የኢትዮጵያ ነገስታት መቀመጫነት ትታወቅ እንደነበር ይገልጣሉ። በዓለማየሁ አበበ አማካይነት  ከጀርመንኛ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ በ2003 ዓም ባለ 592 ገፅ ሆኖ ታትሟል።በእዚሁ መፅሐፍ ውስጥ በገፅ 367 ላይ አዲስ አበባ ቀድማም ከሰባት መቶ ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ነገስታት መቀመጫ እንደነበረች እንዲህ በማለት ገልጠውታል። እንዲህ ይነበባል : -
‘’ አዲሱ የምንሊክ መቀመጫ የሆነው ስፍራ (አዲስ አበባ) ከ13ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ ጀምሮ የኢትዮጵያ ነገስታት ይቀመጡበት በነበረው ቀበሌ ውስጥ የሚገኝ መሆኑ ሊጠቀስ ይገባል’’

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ መርገም እና በረከት ያረፈባት የኢትዮጵያ አሻራ 
አዲስ አበባ ከላይ ከተሰጡት ገለጣዎች በላይ ነች። አዲስ አበባ የኢትዮጵያን መርገምንም ሆነ ፀጋ ሁለቱም እንደክረምት እና በጋ የተፈራረቁባት ከተማ ነች።አዲስ አበባ ፋሺሽት ጣልያን በሶስት ቀናት ውስጥ ከሠላሳ ሺህ በላይ የሆኑ ነዋሪዎቿን በአካፋ እና በዶማ የተጨፈጨፉባት ከተማ ነች።አዲስ አበባ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣት እና ጎልማሳ ነዋሪዎቿን በቀይ ሽብር በመሐል አስፋልት የተዘረሩባት ነች።አዲስ አበባ ታንክ በጎዳናዋ እየተሽከረከረ ''ኢትዮጵያ ትቅደም ካለምንም ደም'' ሲባል ፀሐይ ወጣ ብላ ጨፍራለች።አዲስ አበባ መሬት አርሳ አዝመራ አዝምራ ባታጭድም የካቲት 25።1967 ''መሬት ላራሹ'' ሲታወጅ ሆ! ብላ ወጥታ ዘምራለች።

አዲስ አበባ በታሕሳስ/1953 ዓም እና በግንቦት 8/1981 ዓም የጦር ሰራዊቱ በመንግሥታቱ ላይ ስያምፅ አብራ አምጣለች።አመፁን ያስነሱ የጦር መኮንኖች በንጉሱም ሆነ በኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ሲገደሉ አብራ አምጣለች።አዲስ አበባ በዩንቨርስቲዋ ምሁራን አማካይነት የለውጥ መርሕ ጠንስሳ ወደ ሕዝብ አስርፃ፣መላው ኢትዮጵያጵያን ቀስቅሳ የለውጥ ሐዋርያ ሆናለች።አዲስ አበባ መሬት ላራሹ! ብላ ስታስተጋባ ስለ ዳር ሀገር ብቻ ሳይሆን ስለ አምቦ፣ቢሸፍቱ፣ሰላሌ፣ወለጋ፣ባሌ እና ሐረር ገበሬ ሁሉ የመሬት ባለቤትነት ብላ እንጂ ዘር እና ጎሳ ቆጥራ አይደለም።

አዲስ አበባ በ1997 ዓም በኢትዮጵያ ታሪክ ዓይነተኛ መልክ አለው የተባለውን ምርጫ በግንባር ቀደምትነት በመምራት ህወሓት/ኢህአዴግ መራሹን መንግስት ስልጡን በሆነ የምርጫ ካርድ በመዘረር ዓለምን ያስደነቀ እና የአውሮፓ ኅብረት ወክለው ለምርጫው ታዛቢነት የመጡትን ፖርቹጋላዊ ወ/ሮ አና ጎሚዝን በቁጭት ያንገበገበች፣ከምርጫው አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ሚያዝያ 30/1997 ዓም ሚልዮን ነዋሪዎቿን ይዛ አደባባይ ወጥታ ስለ ሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ ትግል ፈር የቀደደች አሁንም አዲስ አበባ ነች።አዲስ አበባ በእዚህ በ1997 ዓም ምርጫ የሰጠችውን ድምፅ አቶ መለስ እና ስርዓታቸው ሲክዷት ልጆቿን ይዛ አደባባይ ወጥታ ተቃውማለች።በእዚህም የስርዓቱ ኃይል ከ193 በላይ ልጆቿን በአውራ ጎዳናዎቿ ላይ ከተረሸኑባት ገና አስራ አምስት ዓመት አልሞላትም።

አዲስ አበባ በበቀል በትር ስር 
አዲስ አበባ የነቃ፣የተጋ እና የበቃ የፖለቲካ፣ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሐብታዊ አቅም እንዳላት የተረዳው የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት የጅራፍ እሾሁን ማስወንጨፍ የጀመረው አርባ የሚሆኑ የዩንቨርስቲ መምህሮቿን ካለምንም ምክንያት በማባረር ነበር።ከመምህራኑ ውስጥ በፋሺሽት ጣልያን አባታቸው የተገደሉባቸው ፕሮፌሰር አስራትን ጨምሮ በርካታ ምሁራን ከስራ ውጭ ተደረጉ።

በመቀጠል ከተማዋ ቀድማ በማታውቀው ደረጃ በሽሻ፣ጫት ቤት እና ሞራለ ቢስ በሆኑ የዳንስ ቤቶች እንድትወረር ስልታዊ ጥቃት ተደረገባት።በተለይ የጫት እና ሽሻ ቤቶች ሆን ተብለው ከትምህርት ቤቶች ጀርባ ሲከፈቱ ቀበሌዎች እና ክፍለ ከተሞች እያወቁ ምንም አይነት እርምጃ ሳይወስዱ እንዲመለከቱ ተደረጉ።ይህ የማደንዘዝ ሥራ በተለይ በሚያስደነግጥ  ደረጃ ቁጥሩ ያደገው ከ1997 ዓም ምርጫ በኃላ ነው።በ1997 ዓም ምርጫ ተከትሎ አቶ መለስ ከስርዓታቸው ጋር ቂም ይዘውባታል።ስለሆነም ከተማዋን ከፖለቲካዊ ሕይወቷ ለመነጠል ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም።ከእነኝህ የተንኮል ስራዎች ውስጥ አንዱ አዲስ አበባን ከኦሮምያ ክልል ጋር የማጋጨት ተንኮል ነበር።

በተለይ ቅንጅት አዲስ አበባ ሊረከብ ነው ሲባል የኦሮምያ ክልል ፅህፈት ቤቱን ወደ አዲስ አበባ እንዲያዞር ህወሓት ኦህዴድን አዘዘው።ኦህዴድ የቢሮ ዕቅዎቹን እና ሠራተኞቹን ይዞ ወደ አዲስ አበባ መጣ።አዳማ (ናዝሬት) የነበረው የኦህዴድ መስርያቤት ሰራተኞቹ በተለይ ከውሳኔው ድንገተኛነት የተነሳ አዲስ አበባ ቤት ለመከራየት ትልቅ ውክብያ ውስጥ ገብተው ነበር። ውክብያው በእዚህ አላበቃም ቀድሞም ቅንጅትን ከኦህዴድ ጋር የሚያጋጭ መስሎት የጠነሰሰው ስለነበር አዲስ አበባ በባለ አደራ አስተዳደር ላይ ስትወድቅ ኦህዴድ ተመልሶ እንዲወጣ ታዘዘ።በሺህ  የሚቆጠሩ የኦህዴድ ልዩ ልዩ ቢሮ ሰራተኞች ተመልሰው  ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መልሰው በአዳማ (ናዝሬት) ቤት ለመከራየት ሌላ ውክብያ ውስጥ ገቡ።

አዲስ አበባ ፍልስፍና ነች 
ጉዳያችን አዲስ አበባ ፍልስፍና ነች ያለችው ዛሬ አይደለም። ከሦስት ዓመታት በፊት ''አዲስ አበባ ፍልስፍና ነች። ለፍልስፍናዋ ትዋደቃለች'' በሚል ፅሁፍ ስር ይህንኑ ሐሳብ በህወሓት/ኢህአዴግ ዘመንም ገልጣ ነበር።የአዲስ አበባን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያላትን አቅጣጫ የመስጠት አቅም ማንም ሊያጣጥል አይችልም።በ1983 ዓም በአዲስ አበባ አራት ኪሎ ተቀምሞ በኢትዮጵያ ገጠሮች ገበሬውን ይዞ አዲስ አበባ የገባው ለውጥ የረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቀያሽ አዲስ አበባ ሳትገባው እና እርሷም ሳይገባት ሐያ ሰባት ዓመታት ብታሳልፍም አዲስ አበባ ዛሬም ንቁ ነች።አዲስ አበባ ባለፉት ሐያሰባት ዓመታትም ጉልህ የለውጥ ሐዋርያ ከአብራክዋ የውጡ ነበሩ።አንዱዓለም አራጌ፣እስክንድር ነጋ፣የዞን 9 እንቅስቃሴ፣ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ቡልቻ ደመቅሳ፣ብሩቱካን ሜደቅሳ፣ሲሳይ አጌና፣ርዕዮት ዓለሙ እና ሌሎችም ስርዓቱን በሰላማዊ ትግል ሐያሰባቱንም ዓመታት ወጥረው ለለውጥ ከሰሩ አዲስ አበቤዎች ውስጥ ናቸው።

አዲስ አበባ ፍልስፍና ነች።አዲስ አበባ በ1935 ዓም ጣልያን ከሀገራችን ተባርሮ ከወጣ እና የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከኦሜድላ በመቀጠል በከፍተኛ ብሔራዊ ስነ ስርዓት ተመልሶ ከተሰቀለ ጀምሮ አዲስ ዘመን ጋዜጣን ነፃነት በመጣበት ዓመት ማተም ጀምራ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደ ላቀ ደረጃ ያሻገረ እና የሚያሻግር ፍልስፍና ባለቤት ነች።የአዲስ አበባ ፍልስፍና የኢትዮጵያውያን ፍልስፍና ነው።የአዲስ አበባ ፍልስፍና የዘር ቀለም፣የጎሳ ድንበር የለውም።አዲስ አበባ ከሰሜናዊ እስከ ደቡባዊ እና ከምስራቃዊ እስከ ምዕራባዊ  ክፍሏ ከዶርዜ እስከ ከምባታ፣ከዓማራ እስከ ሐማሴን ኤርትራ፣ ከትግራይ አድዋ እስከ ሶዶ ጉራጌ፣ከሐረሪ እስከ ኦሮሞ፣ከአፋር እስከ ቤንሻንጉል ያሉ ኢትዮጵያውያንን ኢትዮጵያዊ በሚል አንድ ስሜት አሳፍራ ያኖረች ከተማ ነች።ይህ ሕብረ ብሔራዊ ነገር ግን ኢትዮጵያዊ ፍልስፍናዋ በወረቀት ላይ ብቻ ሳይሆን በመኖር እና የአኗኗር ዘይቤውንም በማሳየት ያስመሰከረች ነች።አዲስ አበባ ውስጥ አንዱ ብሔር ከሌላው ጋር ተጋጨ የሚል ዜና ተሰምቶ አይታወቅም።ይህ የአዲስ አበቤ የአብሮ የመኖር ፍልስፍና እንዲሁ የመጣ ሳይሆን የመጣ እንግዳዋን አስተምራ የመደመር ችሎታዋ ውጤት ነው።

አዲስ አበባ ኢትዮጵያዊ አድርጎ የመኖር ፍልስፍናዋ የመሳብ ኃይል ያለው እጅግ ከባድ ነው።አስራ ሰባት ዓመት በጫካ እና በረሃ ከርሞ የመጣ የህወሓት/ኢህአዴግ ሰራዊት ፀጉሩን አጎፍሮ እና ያደፈ ልብሱን አጥቦ በቤተ መንግስቱ አጥር ላይ አስጥቶ እና ''በረባሶ'' ጫማውን አድርጎ ሲመጣ፣ ልብሱን ቀይራ፣ሽፍን ጫማ አጫምታ፣ኮሮላ የጃፓን መኪና አስይዛ እና የከተማ መንገዶች ምልክቶች አስተምራ ወደ አዲስ አበቤ ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና አጥምቃ ቦሌ እና ጃክሮስ ሰፈር አኑራ ሰው ያደረገች ነች አዲስ አበባ።አዲስ አበባ የለውጥ ሐዋርያ እንደመሆኗ ሁሉ ከ1997 ዓም በኃላ በስርዓቱ ላይ ለመነሳት ተቸግራ የቆየችበት መሰረታዊ ምክንያት ነበራት።ይሄውም በህወሓት ተንኮል እና የተሳሳተ ትውልድ በመፈጠሩም ጭምር የኢትዮጵያ ፖለቲካ በጎሳ በመከፋፈሉ አዲስ አበባ ሁኔታዎችን በአንክሮ ከመከታተል ባለፈ የጎላ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ተቸግራለች።ፍልስፍናዋ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ሜዳው ጎሳዊ ሲሆን ለአዲስ አበባ አይመቻትም።የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያነሳ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ስመጣ ቀድማ ከፊት በመሰለፍ ግን አዲስ አበባ ነበረች።አዲስ አበባ በሚልዮን የሚቆጠር ልጆቿን ይዛ በመስቀል አደባባይ የተሰለፈች አዲስ አበባ ከኢትዮጵያዊ ፍልስፍናዋ ጋር ነበር።

የአዲስ አበባ ዘር አልባ እና ጎሳ አልባ ፍልስፍናዋ ለአሁኗ ኢትዮጵያ በእጅጉ ያስፈልጋታል።ኢትዮጵያን የማያውቁ የተወለዱበትን አካባቢ ብቻ ዓለም የሚመስላቸው የዋሃንን ኢትዮጵያ ምን ያህል ሰፊ እንደሆነች እና የሁሉም መሆኗን ለማሳወቅ የአዲስ አበባ ፍልስፍና ያስፈልጋቸዋል።የአዲስ አበባ ፍልስፍና ጎሳ አልባ ብቻ አይደለም።ይቅር ባይ እና ዓለም አቀፋዊ እሳቤንም የተላበሰ ነው።አዲስ አበባ ይቅር ስትል ፈጣን ነች።በ1997 ዓም ከአንድ መቶ ዘጠና ሶስት በላይ ልጆቿን የገደሉባት አቶ መለስ በሶስት ዓመት ውስጥ የኢትዮጵያ ሚሊንየም በሚሊንየም አዳራሽ ሲከበር የሀገር ልብስ አልብሳ በሱዳን ዘፈን አብራ የተጫወተች የትናንቱን ፈጥኖ የመርሳት ፍልስፍና ባለቤትም ነች አዲስ አበባ።አዲስ አበባ ስሟን ክዶ ''ፊንፊኔ'' እያለ የሚጠራትን ሲፈልግ እጁን ትንፋሽ እንዳጠረው ሕፃን እያወራጨ ''አዲስ አበባ በቀለበት ውስጥ አድርገን ማፈን እንችል ነበር'' እያለ ከአራት ሚልዮን በላይ ሕዝብን ሳህን ላይ እንደዘረገፈው ቆሎ የሚያየውን ጃዋር መሐመድ አዲስ አበባ ሲመጣ ድንጋይ ሳትወረውር፣የሁሉም ሃሳብ ይደመጥ ብላ እያየች እንዳላየች፣እየሰማች እንዳልሰማች ያሳለፈች ነች አዲስ አበባ ብቻ ነች። ይህ ብቻ አይደለም አዲስ አበባ የፅንፍ መስመሩ የወጣ እንደሆነ በትርክቱ የምታውቀው የኦነግ አመራር በባሌ ሳይሆን በቦሌ ሲመጣ አዲስ አበባ ኦነግን ለመቀበል ከሩቅ ገጠር ቦታዎች የመጡ ኢትዮጵያውያንን መንገድ ላይ ምግብ ደርድራ፣የሚጠጣ አዘጋጅታ ለእንግዶቹ ኢትዮያዊ ፍልስፍናዋን ያሳየች ከተማ ነች።ለእዚህ ደግነቷ ቡራዩ ላይ ሕፃናቷ ሳይቀሩ ቢታረዱባትም  አዲስ አበባ በቶሎ የተጎዱትን አክማ፣የሞቱትን ቀብራ፣እንባዋን አበሳ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ሕይወትን አስቀጠለችው።

ከላይ የተጠቀሰው የአዲስ አበባ ቻይነት፣ታጋሽነት፣ኢትዮጵያዊ ደማሪነት እና ይቅር ባይ ፍልስፍናዋ ግን ገደብ የለውም ማለት አይደለም።ሁሉን ስለፍቅር ብታደርገውም በህልውናዋ ላይ የተረት ተረት ትርክት ይዞ ዱላ እና ገጀራ ይዞ ለሚፎክር ግራ ገብ ግን ቦታ የላትም።መጋቢት 1/2011 ዓም በሺህ የሚቆጠር የአዲስ አበባ ነዋሪ ወጣት በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አስተባባሪነት በባልደራስ ሆቴል በተጠራው ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ የተገኘው ሕዝብ ዋነኛ ብሶቱ የመሰረታዊ ኢትዮጵያዊ ፍልስፍናው መደፈር ነው።መደፈር ብቻ አይደለም።መኖር አትችልም፣እናስወጣሃለን፣ የሚሉ ስለ ትናንት ያላጠኑ እና ያላነበቡ፣ስለነገ ርዕይ ማስቀመጥ ያልቻሉ በአንድ የመንጋ አስተሳሰብ የሚመሩ ሲዝቱበት የማይነካውን ቀይ መስመር እንዳለፉ አመነበት። ስለሆነም የረጅም ጊዜ ፍልስፍናዋን ይዞ ተነሳች።

ባጠቃላይ አዲስ አበባ በአስራ ዘጠነኛው ክ/ዘመን መጨረሻ ለዓድዋ ዘማች ስንቅ ሰንቃ፣ታቦት አስይዛ ቸር ግቡ ብላ ንጉሷን የሸኘች፣በሐያኛው ክ/ዘመን መጀመርያ በፋሽሽቶች ከሠላሳ ሺህ በላይ ልጆቿን በመገበር የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ገፈት ቀማሽ የሆነች እና በእዚሁ ክፍለ ዘመን ውስጥ በኢትዮጵያ የነበረው ፖለቲካዊ፣ማኅበራዊ እና ምጣናዊ ሐብታዊ ቅርፅ በመስጠት እና ለማም ከፋ አዳዲስ ሃሳቦችን ከዓለም አቀፍ ለውጥ ጋር በተናበበ መልኩ በማፍለቅ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ የለውጥ ፍልስፍና ማዕከል ሆናለች።ይህ ፍልስፍናዋ መሰረታዊ መርሁ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት እና ጎሳ አልባ ዕሳቤ ነው።አሁን አዲስ አበባ ይህንን ፍልስፍናዋን በልዩ ክብር የመጠበቅ እና በጎሳ ፖለቲካ ለተጎዳችውን ኢትዮጵያ የማስተማር ዘመቻ ከአዲስ አበባ ይጠበቃል።አዲስ አበባ በዙርያዋ ያለውን የተሳሳተ አስተሳሰብ እና ትርክት በጥቂት ፅንፈኞች እንዲይዝ የተደረገውን ወገን ወደ በጎ ዕሳቤ እንዲመጣ የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥቶ ኢትዮጵያዊ ቤተኘነቱን እንዲያፀና በፍቅር የማስተማር ስራዋን በዕቅድ እና በመርህ ላይ በተመሰረተ መንገድ ማካሄድ ይገባታል።ይህ ማለት ግን ገጀራ ይዞ ለመምጣት ለሚያስብ በታኝ ፅንፈኛ ጋዜጠኛ እስክንድር እንዳለው ''ግፍ መስራትን እንጂ ግፈኛን አንፈራም'' ከማለት ሌላ አማራጭ የላትም።የአዲስ አበባ ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ይለምልም! 
================================////=======================
አዲስ አበባ ከቦሌ እስከ አራዳ ፒያሳ የአውራ ጎዳና ጉብኝት (ቪድዮ) 

አዲስ አበባ ከጀሞ እስከ ፒያሳ አራዳ  የአውራ ጎዳና ጉብኝት (ቪድዮ) 


ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...