ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, March 23, 2019

ኢትዮጵያን ከመጪው ቀውስ የምትታደጋት ታላቅ ምሽት በጉጉት እየተጠበቀች ነው።


ጉዳያችን/ Gudayachn
መጋቢት 15/2011 ዓም (ማርች 24/2019 ዓም)

ኢትዮጵያ ጥገናዊ ለውጥ ውስጥ ከገባች ድፍን አንድ ዓመት ሊሞላት አስር ቀናት ብቻ ቀርተዋታል።ሰሞኑን የተለያዩ ሚድያዎች የአንድ ዓመት ጉዞውን በመገምገም እና መጪውን በማመላከት ላይ ያተኮረ ስራዎች ላይ ተጠምደዋል።በእነኝህ ጉዳዮች ላይ ከእዚህ በፊት ብዙ ስላልኩበት እና ብዙዎች ብዙ ስላሉበት እዚህ ላይ በአንድ ዓመት ሂደት ላይ የምለው የለም። ኢትዮጵያ በቀጣይ በሚገጥማት ግልጥ እና የጠራ ሂደት ላይ ግን ብዙ ማለት ይቻላል።  

በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ በአራት አስተሳሰቦች እና ኃይሎች ውስጥ እንዳለች ግልጥ ሆኗል።

የመጀመርያዎቹ  በኢትዮጵያ ላለፉት 27 ዓመታት በህወሓት/ኢህአዴግ የተጫነው የጎሣ ፖለቲካ የሚያቀነቅኑ እና በከረረ መልክ ለማስቀጠል የሚሞክሩ ናቸው።እነኝህ ውስጥ የቀድሞው ህወሓት፣የአሁኑ ኦደፓ፣የኦነግ አንጃዎች  እና በደቡብ ክልል ውስጥ የተደባለቁ አመራሮች ሁሉ ይካተቱበታል።

በሁለተኛ  የሚጠቀሱት እንዲሁ ብሔርተኛ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ነገር ግን በኢትዮጵያ የነበረ መሰረት ማናጋት እና አዲስ ትርክት መፃፍ አያዋጣም የሚሉ እና ፅንፍ የረገጡ ኃይሎች  ሕዝብ አፈናቅለዋል፣ለመጭዋ ኢትዮጵያም አደጋ ናቸው የሚሉ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ መከበር አለበት፣አሁን ያለው ሕገ መንግስት እኛን ያላሳተፈ ነው የሚሉ ናቸው።በእዚህ ውስጥ ዓማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣አዴፓ ውስጥ ያሉ ባለሙያ እና አንዳንድ አመራሮች ሁሉ ይገኙበታል።

ሶስተኛው ተጠቃሾች ደግሞ ላለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያ የገባችበት የጎሳ ፖለቲካም ሆነ አሁን በየትኛውም መልኩ በተለያዩ ቡድኖች እና ፓርቲዎች የሚራመደው የጎሳ ፖለቲካ ኢትዮጵያን የሚያጠፋ እና ወደ ለየለት የእርስ በርስ ጦርነት የሚከት ስለሆነ ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም። ፖለቲካ ብሎ የጎሳ ፖለቲካ ማራመድ ፈፅሞ አይቻልም ምክንያቱም ፖለቲካ በተፈጥሮው ሁሉን አቀፍ እንጂ የእዚህኛው ወገን ነኝ ብለህ ፖለቲካ ልታራምድ አትችልም።የሚል ሲሆን እንደ መፍትሄ የሚያቀርቡት የዜግነት ፖለቲካን ነው።አንድ ሰው ዜጋ በመሆኑ ብቻ ከየት መጣህ ሳይባል እንደ ግለሰብ እና የቡድን መብቱ ሊከበር ይገባል የሚል ሃሳብ ያቀርባሉ።ከእዚህ ሃሳብ ጋር የሚስማሙት እና ዋነኛ ተጠቃሽ በቅርቡ ወደ ፓርቲነት እንደሚቀየር ያስታወቀው የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ነው። 

አራተኛው እና ከላይ ከተጠቀሱት ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች እና አደረጃጀቶች ጋር ልንዘለው የማንችለው እና እራሱን የቻለ ቅርፅ ያልያዘው (ፍኖተ ካርታ ስላልወጣ) የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖለቲካ ዕሳቤ ነው።ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መጋቢት 24/2010 ዓም በመንበረ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሰየሙ በኃላ በመጡበት በቀድሞው ኦህደድ የዛሬው ኦዴፓ (ምርጫ ቦርድ ገና አልመዘግብኩትም መጥቶ ይመዝገብ ብሏል) አስተሳሰብን ሙሉ በሙሉ እያስፈፀሙ ነው ብሎ መናገር አይቻልም።ከእዚህ ያልቅ እርሳቸውም በባዛኛው በኢትዮጵያዊነት ንግግሮች በታጀበ የፖለቲካ ስሪት እንደሚያምኑ የሚገልጥ ግን ሁሉን አቀፍ የሆነ ''መደመር'' በሚል ዕሳቤ ውስጥ የሚያጠነጥን ፖለቲካ ይዘው ወጥተዋል።

ይህ መደመር በተግባር ላለፉት አንድ ዓመታት ሲታይ በርካታ መልኮች እና ፈፃፀሞች እንደታዩበት ዛሬ ላይ ሆኖ መናገር ይቻላል። አንዳንዶች ኢትዮጵያን በሂደት ወደ አንድ የሚያመጣ ነው ሲሉ፣ሌሎች በተግባር  የበለጠ ለፅንፈኛ የኦህዴድ (ኦዴፓ) እና ኦነግ ኃይሎች ቦታ የሚያደላድል ነው በማለት ያወሳሉ።በርግጥ በሁሉም መልክ ለመደምደም ጊዜው ገና ነው።ሆኖም ግን የሕግ የበላይነትን ማስከበር  ላይ በርካታ ግድፈቶች ታይተዋል።እዚህ ላይ ከአስራ አምስት በላይ ባንኮች በኦነግ ስም መዘረፉ፣በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ አሁንም በኦነግ ስም በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች አንፃር የተወሰደው እርምጃ እና ድርጊቱን ለመውቀስ ሳይቀር የዶ/ር ዓቢይ አስተዳደር ያሳየው እጅግ የበዛ መቅለስለስ በብዙ አስተችቶታል። 

ኢትዮጵያን ከመጪው ቀውስ የምትታደጋት ታላቅ ምሽት በጉጉት እየተጠበቀች ነው

ይህ ኢትዮጵያን ከመጪው ቀውስ የምትታደጋት ታላቅ ምሽት በጉጉት እየተጠበቀች ነው  የሚለው  የእዚህ ፅሁፍ ርዕስ የሃሳቡ መነሻም መድረሻም ነው።ጉዳዩ እንዲህ ነው ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ከላይ በተጠቀሱት ኃይሎች አስተሳሰብ ተወጥራ ለምርጫ በሰላም የመድረስ ዕድሏ ፈታኝ ነው።ምርጫው እራሱ በጎሳ እና በኢትዮጵያ የዜግነት ፖለቲካ መሐል ለመምረጥም የማይቻልበት ፍትሓዊ መደላድሉ ከአሁኑ ትንፋሽ ማጠር ይታይበታል።እዚህ ላይ ያለው አማራጭ ምንድን ነው? የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው።መልሱ በአጭሩ ኢትዮጵያ በህወሓት/ኢህአዴግ ወለድም ሆነ በፅንፈኛ የኦነግ ኦዴፓ የጎሳ ፖለቲካ የምትራመድበት አንዳችም መንገድ የላትም። የችግሩ ክብደት አንዲት የዶሮ ላባ ቢጨመር የሚንኮታኮት ቁልል መስሏል።ከሁሉም በላይ የጎሳቸውን በደል ለማሰማት እና ጎሳቸውን ለመቀስቀስ ብቻ አልመው የተነሱ ሚድያዎች ጧት ማታ አዳዲስ ጎሳቸውን የሚቀሰቅስ አጀንዳ እየመዘዙ ባሉበት ወቅት መጪው ምርጫ ይደረጋል ማለት ለፅንፈኞች  ወንበር ለመስጠት እና ኢትዮጵያን አዲስ ትርምስ ውስጥ ለመክተት ካልሆነ በቀር ውጤት የለውም።ገና ተመርጠው ስልጣን ሳይዙ ትዕግስት አጥተው ከአዲስ አበባ ጀምሮ እስከ ወሎ ሁሉ የእኛ ንትርክ ውስጥ የገቡት ኃይሎችም ሆኑ በጎሳ ነፍጥ ሁሉን አንበርክከን እንገዛለን የሚሉት አዳዲስ ምልምል የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች ሁሉም የነገ የኢትዮጵያን ተስፋ የሚያጨልሙ ናቸው።

ስለሆነም ኢትዮጵያ አንድ ከመጪው ቀውስ የምትታደጋት ምሽት ያስፈልጋታል።ይህች ምሽት ቆራጥ፣ኢትዮጵያዊ፣ትውልድ አዳኝ ምሽት ሆና በታሪክ የምትዘከር ምሽት ትሆናለች። በእዚህ ምሽት ላይ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እና ራድዮ የምሽት ሁለት ሰዓት ዜና ላማሰማት ይዘጋጃሉ።በዜናው ላይ ማንኛውም ሰው፣ፓርቲ፣ሚድያ፣ትምህርት ቤት፣ የሃይማኖት ድርጅት፣የንግድ ድርጅት፣ባንክ፣አከላለል ሁሉ በጎሳ እና በብሔር ስም ማድረግ፣ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ ንግግር መናገር፣ጎሳን መሰረት ያደረገ ማናቸውም የጥላቻ ንግግሮች ሁሉ፣ይህ ክልል የእኔ ነው ያኛው የእገሌ ነው ማለት፣ባጠቅላይ ላለፉት 28 ዓመታት ሲሰራበት የነበረው የጎሳ ፖለቲክ በሕግ ታግዷል የሚል ዜና ይሰማል።ይህ ሕልም አይደለም።ብቸኛው የኢትዮጵያን የአሁኑ ችግር የሚፈታ ወሳኝ ውሳኔ ነው።ጉዳዩ ከሕገ መንግስቱ ጋር ወዘተ የሚለውን እንደፈለገ ቅርፅ ስጡት፣ተንትኑት።ኢትዮጵያን መምራት የፈለገ መውሰድ ያለበት ወሳኝ እርምጃ ግን ይህ ነው።እዚህ ላይ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች ከፍተኛ ተቃውሞ ያስነሳሉ፣ኢትዮጵያን ወደ ባሰ ብጥብጥ የምወጽዳት የሚመስላቸው አሉ።ይህ ግን ከተወሰነ መንገጫገጭ ውጪ ኢትዮጵያን አንድ እርምጃ የምያስፈነጥራት፣ አብዛኛውን ሕዝብ በተለይ በጎሳ ምክንያት ስፈናቀል የኖረው የሱማሌ፣የደቡብ፣የዓማራ እና የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ስለሆነ ከፍተኛ ደስታ ይፈጥራል።የንግዱ ማኅበረሰብ እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሳይቀር በከፍተኛ ደረጃ አብሮን የሚቆምበት ትልቅ እና ወሳኝ አጀንዳ ነው። ዕርምጃው በአንድ ጊዜ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆችን ባያከስም ሀገራዊ መብታቸውን ሳይነጠቁ እና ተከብሮ የማሰብያ የፅሞና ጊዜ የሚሰጣቸው ነው።

በመጨረሻም ይህችን ምሽት ማን ይሰራታል? የሚለው ጥያቄ ይነሳል።ዶ/ር ዓቢይ ይህንን ብቸኛ አዋጪ መንገድ ይወስዳሉ? ወይንስ ሁሉንም ለማስደሰት በሚል መሐል ላይ ሆነው ለማጫወት ይሞክራሉ? መልሱ ቀላል ነው።ዶ/ር ዓብይ ነገሮችን ተንትነው እንደሚያወሩት ለኢትዮጵያ አንድነት ከቆሙ ይህችን የምፈልጋትን ምሽት ያምጡ። ይህንን ማድረግ ካላመኑበት ግን የኢትዮጵያ ታሪክ በወርቅ ቀለም ታሪኩን የሚፅፍለት ከጦር  ሰራዊቱም ይምጣ፣ከትግራይ፣ከጎንደርም ይምጣ ከአፋር እና ሱማሌ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊቀበለው ዝግጁ ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ ከ150 ዓመት በኃላ አይደለም አካላቸውን ፀጉራቸውን አክብሮ በሙዜም በዛሬዋ ዕለት ከእንግሊዝ አስመጥቶ በክብር ያስቀመጠላቸው አፄ ቴዎድሮስ ጎንደር መወለዳቸው ሳይሆን ለአንድነቱ በድፍረት በፈንጅ ላይ የመራመድ ያህል ከዘመነ መሳፍንት የገላገሉት ጀግና ስለሆኑ ነው።ዛሬም ምርጫው አንድ ነው።እንደ አሮጌ የሹራብ ክር እየተረተረ የማያልቅ መዘዝ ይዞ ከሚመጣ የጎሳ ፖለቲካ በአንዲት ምሽት አዋጅ መገላገል ነው።ከአዋጁ በፊት ምንም ሥራ የለም እያልኩ አይደለም።ከእዚህ ውጪ ዶ/ር ዓቢይ ለውጡን ወደፊት ማስኬድ ይቸግራቸዋል። ያቺን ምሽት ማንም ያምጣት ማንም በእርግጠኝነት አትቀርም።ጥያቄው ብዙ ሕዝብ ሳያልቅ ያችን ምሽት ማምጣታችሁ ላይቀር መሽኮርመሙ ይብቃ። ኢትዮጵያን ከመጪው ቀውስ የምትታደጋት ታላቅ ምሽት በጉጉት እየተጠበቀች ነው።  


ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments:

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...