ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, March 6, 2019

በዓማራ እና በትግራይ መሐል ሕዝብ የጠራው ጦርነት የለም! የድርጅቶች ግጭት የሕዝብ ግጭት አይደለም።


ጉዳያችን / GUDAYACHN 
የካቲት 28/2011 ዓም (ማርች 7/2019 ዓም)

  • ሕዝቡን በጎሳ ከፋፍላችሁ በማጫረስ ጎልምሳችሁ እና አርጅታችሁ፣ ዛሬም ደም ለማፋሰስ የምትጣደፉ የዕርግማን ትውልድ አካሎች ሆይ! ይልቅ የዕርጅና ዘመናችሁን የመፀፀቻ እና የንስሐ ዘመን አድርጉት።

ህወሓት ከሻብያ ጋር ገጥማ እንዳ ስላሴ ላይ ሦስተኛውን ክፍለ ጦር ስታጠቃ እና መቀሌን ስትይዝ ከኢሕአፓ የወጡት የእነታምራት ላይኔ ቡድን በኢሕዴን ስር መኖሩ የበለጠ ወደ ወሎ እና ጎንደር ለመሻገር እንደሚረዳት አመነችበት።ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከአንዱ ክፍለ ሀገር ወደ ሌላው ስትሄድ እንደ መንገድ ዳር ሱቅ የብሔር ድርጅቶች እየፈለፈለች አዲስ አበባ ደረሰች።የፈለፈለቻቸው የብሔር ድርጅቶች ግን ዛሬ አድገው እራሷኑ የሚገዳደር አቅም ገንብተው ህወሓትን አሽቀነጠሯት።

ህወሓት ከአዲስ አበባ በከፍተኛ የሙስና ቅሌት እና ሰብአዊ ጥፋት መቀሌ ከከተተች በኃላ የገጠማት ሁለተኛው ተግዳሮት  የእራሱ የትግራይ ሕዝብ ጥያቄ ነው።መቀሌ ውሃ ሳይኖራት በቢልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያሸሹት ያኔ በነጠላ ጫማ አዲስ አበባ የገቡ የዛሬ  ቱጃር ህወሓቶች በሕዝብ ጥያቄ መድረሻ ጠፋቸው።የአረና አመራሮች  ሳይቀሩ የህዝብ ድምፅ ለማሰማት በመቀሌ ዩንቨርስቲ ውስጥ ሃሳባቸውን ለመስጠት ሲሞክሩ አቦይ ስብሐት ሳይቀሩ በጭብጨባ ለማስቆም ሲሞክሩ ታዩ። የህዝቡ ጥይቄ ግን አልቆመም። ስለሆነም አንድ አይነት ሥራ ለሕዝቡ መስጠት አለባቸው። ይህም ጦርነት መፍጠር ነው።ጦርነት የትግራይን ህዝብም የበለጠ ለመጨፍለቅ ይመቻቸዋል።ስለሆነም ጦርነቱ ይፈለጋል።

ጦርነቱን ደግሞ ''በትግራይ ሕዝብ እና በዓማራ ሕዝብ መሐል'' እንደሚደረግ በአክትቪስቶቻቸው ሲናገሩ ትንሽም እፍረት የለም። እዚህ ላይ የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲም ሆነ ህወሓት በትግራይ እና በዓማራ ሕዝብ መሐል የሚደረግ ጦርነት የሚል ስያሜ ማቆም እንዳለባቸው ለምድያዎቻቸው መንገር አለባቸው።በፊውዳሉ ስርዓት የሚደረጉ የገዢዎች ጦርነቶችን ታሪክ አባቶቻችን ሲፅፉ ጥንቁቅ ነበሩ።አንድም ታሪክ ላይ ትግራይ እና ጎንደር ወይንም ወሎ እና ትግራይ ተዋግተው አይሉም ራስ እገሌ ከደጃች እገሌ ጋር ወይንም የትግራዩ ገዢ እገሌ ከጎጃሙ ገዢ እገሌ እያሉ ይፅፋሉ እንጂ ሀገር ከሀገር ተጣላ ብለው የፃፉት ታሪክ የለም።የሚጣሉ ገዢዎች ናቸው።ለእዚህ ነው ላሸነፉት የእርስ በርስ ጦርነት አንድም ማስታወሻ ሃውልት ትተው አላለፉም።ምክንያቱም መጪው ትውልድን አርቀው የሚመለከቱ እና ርዕያቸው ሐገራዊ እና ዘመን ተሻጋሪ ስለነበር ነው።

ለማጠቃለል በዓማራ እና ትግራይ መሐል ጦርነት ብሎ ነገር የለም በህወሓት እና አዲፓ መሐል ካለም የጅል ጫወታችሁን እንድታቆሙ ነው የምትጠየቁት።ለመሆኑ ይህ ምስኪን ገበሬ በምን ዕዳው ነው ኢትዮጵያን በብሔር  ከፋፍለው እና ሀገር ዘርፈው ከሄዱ ሙሰኞች ጋር ተሰልፎ እርስ በርሱ የሚዋጋው? ለምንስ ተብሎ ነው የውጭ ጠላት ሳይመጣበት  እርስ በርሱ የምተላለቀው? ይህ የእሳት ዳር ጫወታ ማቆም የሁሉም ኃላፊነት ነው።የፌድራል መንግስትም የሀገር ፀጥታ የማስከበር ተግባሩን መወጣት አለበት።በአሁን ሰዓት ለጦርነት የሚያነሳሳ አንዳችም ምክንያት ሊኖር አይገባውም።ህወሓቶች በህዝባዊ ማዕበል ያጡት ስልጣን ቁጭት  በሌላው ትግራይ ሕዝብ ውስጥ አድሮ ለጦርነት የሚያነሳሳ ምቹ ሁኔታ ያለ መስሏቸው ይሆናል። ይህ ስሜት ያለው እነርሱ ውስጥ ነው እንጂ ሌላው ሕዝብ የዕለት ኑሮውን ለመሙላት እየተውተረተረ ነው።ዶ/ር አረጋዊ ከሳምንት በፊት ለኤል ቲቪ እንደተናገሩት ''ህወሐቶች ሕዝቡን አቆርቁዘውታል።በአሁኑ ሰዓት ከትግራይ ሕዝብ 85% የሚሆነውን ሕዝብ ህወሓት የሚያኖረው በምግብ ለስራ  መርሐግብር ነው '' ብለዋል።የስልጣን ጥማቱ ያለው ህወሓት እና የጥቅም ተጋርዎቻቸው ዙርይ ነው።ሌላው እንዲሁ ስሜት ውስጥ ያለ እና የነገ ተስፋውን የሚጠብቅ ነው።በዓማራ ክልልም ያለው ይሄው ነው።ያለውን መሬት በበሬ አርሶ ቤተሰቡን ለመመገብ የሚታትር ሕዝብ ዛሬ ላይ ጦርነት ናፍቆታል ማለት ዘበት ነው።ስለሆነም በምንም መለኪያ የሚፈለግ ጦርነትም ሆነ ለጦርነት ምቹ የሆነ ነባራዊ ሁኔታ የለም።ሕዝቡን በጎሳ ከፋፍላችሁ በማጫረስ ጎልምሳችሁ እና አርጅታችሁ፣ ዛሬም ደም ለማፋሰስ የምትጣደፉ የዕርግማን ትውልድ አካሎች ሆይ! ይልቅ የዕርጅና ዘመናችሁን የመፀፀቻ እና የንስሐ ዘመን አድርጉት።

ጉዳያችን / GUDAYACHN 
www.gudayachn.com

No comments:

ለፕሮፌሰር መራር፣ልደቱ፣ጀዋርና ኢንጅነር ይልቃል ዘፈን ይህችን ዜማ እንምረጥላቸው።

በቅድምያ ስለ አራቱም የመግቢያ ማስታወሻና ወቅታዊ ሁኔታቸው። አራቱም ከመስከረም በኋላ መንግስት የለም ብለው ኢትዮጵያን ለእርስ በርስ ጦርነት ሊነክሯት ሞክረዋል።ዝርዝሩን፣ከእነማን ጋር መክረው እንደነበር፣ለኢትዮጵያ ደግሰው...