ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, October 31, 2016

የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ምስረታ በተመለከተ (የጉዳያችን ምልከታ)



ጉዳያችን / Gudayachn
ጥቅምት 21፣2009 ዓም 
================
  • ምስረታው ማዕከላዊ እና አሰባሳቢ ሚናው ላይ ያተኩር። 
  • ዐማራው ላይ የደረሰውን በደል እና እየወጣ ያለውን የፖለቲካ ኃይል ማዳመጥ ይገባል።
  • የአገራዊ ንቅናቄው ድምፁን የሚያሰማበት አንድ የሚድያ ፕሮግራም ሊኖረው ይገባል።

ምስረታው ማዕከላዊ እና አሰባሳቢ ሚናው ላይ ያተኩር
=======================================
ጥቅምት 20፣2009 ዓም ዋሽንግተን ዲሲ ላይ በአራት ድርጅቶች ፊርማ የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ መመስረቱን ኢሳት በቀጥታ ከስፍራው ዘግቧል።ምስረታው ወቅታዊ እና አስፈላጊ ነው።በስራው ላይ የደከሙ ምሁራን ምስጋና ይገባቸዋል።የእዚህ አይነቱ ስብስብ ሲፈጠር ማዕከላዊ እና አሰባሳቢ ሚናው የጎላ መሆኑ ጥቅም አለው። ኢትዮጵያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ ሁለት የመንግስት ለውጥ አልፋለች።በሁለቱም ለውጥ ወቅት ግን የተዘጋጀ ማዕከላዊነትን እና የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችን ሃሳብ የሚያንፀባርቅ ተቋም አለመኖሩ ሽግግሩ እንዲጠለፍ ሆኗል።አሁንም የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ማዕከላዊ እና አሰባሳቢ ሚናውን የሚያጎሎ ስልታዊ ስራዎች ላይ ማተኮር አለበት።

ዐማራው ላይ የደረሰውን በደል እና እየወጣ ያለውን የፖለቲካ ኃይል ማዳመጥ ይገባል
========================================
በኢትዮጵያ ውስጥ ጉልህ ብቻ ሳይሆን በስብጥሩም ሆነ ለኢትዮጵያ እንደ ሀገር መቀጠል ከፍተኛ መስዋዕትነት ከከፈሉት ውስጥ የዐማራው ኅብረተሰብ አንዱ ነው።ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ በሕወሓት የፖለቲካ ፕሮግራም (ማንፌስቶ) ውስጥ ´´ጠላት´´ በሚል ቃል የተፈረጀ ኅብረተሰብ ነው። ለእዚህ ፍረጃ እስካሁን ሕወሓት ይቅርታ አልጠየቀም።ይልቁንም ይህንን ኅብረተሰብ በትውልዱ ብቻ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ በይፋ ስነዛበት ሰንብቷል።ይህ ብቻ አይደለም።በቀጥታ በሕወሓት እና እርሱ በቀሰቀሳቸው ሁሉ በአደባባይ ደሙ ፈሷል፣እንደ አውሬ እየተሳደደ አንገቱ ተቀልቷል፣ከሶስት ትውልድ በላይ ከኖረበት መሬት እየተገፋ ስደተኛ ሆኗል።ይህ ሁሉ ሲሆን የሕወሐት መንግስት አንዳችም የዜግነት ክብሩን አልጠበቀለትም።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ይህንን በደል በሚገባ አለመረዳት በእራሱ ትልቅ ችግር ይዞ ይመጣል።አሁን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ወጣቶች  የእዚህን ኅብረተሰብ ብሶት የሚያንፀባርቁት በቅርብ በሀገር ቤት የደረሰውን ሁሉ ስለሚረዱ እና ለመረጃው ቅርብ መሆናቸውን ማመን ይገባል።በደሉ ይህ ፅሁፍ እየተፃፈ በዛሬው እለት ብቻ ከ200 በላይ በሚሆኑ የዐማራ ተወላጆች ላይ የግድያ ትዕዛዝ ወጥቷል።በሺህ የሚቆጠሩ ወደ እስር ቤት ተግዘዋል።በኢትዮጵያ ምድር በአሁኑ ወቅት በስፋት እና በብዛት የጦር መሳርያ አንስቶ እየተፋለመ ያለ ኃይል በእዚሁ ዐማራ  መሬት ላይ ይገኛል።ይህ በእራሱ ማንም የፖለቲካ ኃይል ይህንን ክፍል አርቆ ወደፊት ሊሄድ እንደማይችል አይነተኛ ማሳያ ነው።በተለይ የትጥቅ ትግሉ ከሕወሓት ጋር ብቻ ሳይሆን ከሱዳን ወታደሮች ጋርም መሆኑ የእዚህን ኃይል አካባቢያዊ ተፅኖ ከወዲሁ ለመረዳት ያስችላል።

ይህንን የፖለቲካ ክስተት በአግባቡ አለመያዝ በእራሱ ለነገዋ ኢትዮጵያ ትልቅ ስጋት ነው።እጅግ የመረረ ስሜት፣እንቅስቃሴ እና ቁጭት እየተሰማ ነው።ይህንን ስሜት ማዳመጥ፣የተፈፀመውን በደል መረዳት እና ወደ ጋራ ኢትዮጵያዊ አጀንዳ መቀየር የኢትዮያ የጋራ ንቅናቄ ሊሰራው ከሚገባቸው ቀዳሚ ተግባሮች ውስጥ አንዱ መሆን አለበት።ይህ ማለት በደል በሌላው ላይ አልደረሰም ማለት  አይደለም።ሆኖም ግን  በአንዳንድ የአገራችን ማኅበረሰቦች በተለይ በዐማራው ላይ የሚፈፀሙት ጥቃቶች ተቋማዊ እና ኢትዮጵያን በእረጅም ጊዜ የመበታተን እቅድ ያላቸው ሁሉ በስልታዊ ኢላማነት  የሚፈፀሙ ከመሆናቸው አንፃር ልዩ ትኩረትን ይሻሉ ለማለት ነው።


የአገራዊ ንቅናቄው ድምፁን የሚያሰማበት አንድ የሚድያ ፕሮግራም ሊኖረው ይገባል
===================================
የአገራዊ ንቅናቄው ትናንት በአዳራሽ እንደተመለከትነው በሚቀጥሉት ጊዜያት ምንም ድምፁን ሳያሰማ ወራት ካስቆጠረ ፍሬ ቢስ ይሆናል።አሁን ያቀፋቸው እና ወደፊት የሚያቅፋቸውን ድርጅቶች የጋራ ተግባራት፣ርዕዮች እና ዕቅድ ሁሉ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያደርስበት ድምፅ ያስፈልገዋል።ይህ ድምፅ ደግሞ ሌሎች የበለጠ እንዲገናኙት የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን እግረ መንገዱን ላለፉት 25 ዓመታት የተጎሳቆለውን አገራዊ እና ኢትዮጵያዊ አጀንዳ በአዲሱ ትውልድ ላይ ይቀርፃል።ይህ ትውልድ በእጅጉ ተጎድቷል።ይህ ትውልድ አፋር ተወላጅ ኢትዮጵያዊ የሚል የማይመስለው የወያኔ የሚያደነቁር ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ነው።የእዚህ አይነት አገራዊ ንቅናቄ ኢትዮጵያዊነት በአፋሩ፣በኦሮሞው፣በሲዳማው ሁሉ ሲወሳ የማሰማት ኃላፊነት አለበት።

የአገራዊ ንቅናቄው ባለ አደራ እና ጠባቂ ሕዝብ ነው።ዋስትናውም ሕዝብ ነው።ከአገራዊ ንቅናቄው አፈንግጦ የግል እና የቡድን ጥቅሙን ከአገራዊ አጀንዳ ለማስቀደም የሚፈልግ ድርጅት የሚዳኘው በሕዝብ ነው።ይህንን ለማድረግ ግን አገራዊ ንቅናቄው ለሕዝብ መገለጥ አለባቸው የሚላቸውን መረጃዎች እና ልዩ የሚድያ ፕሮግራም በቶሎ መጀመር አለበት።ለምሳሌ በኢሳት ላይ ሳምንታዊ የግማሽ ሰዓት ቪድዮ ፕሮግራም ሊኖረው ይችላል።ይህ ካልሆነ ግን በመሬት ላይ የሚሰሩ የጋራ ስራዎችን ከሕዝብ ጋር ለማቀናጀት ችግር ይገጥመዋል።

ባጠቃላይ የአገራዊ ንቅናቄው ዋና መሰረት ያደረገው ችግራቸውን በኢትዮጵያዊነት እና በኢትዮጵያ ስር ለመፍታት የተዘጋጁ ድርጅቶችን ማሰባሰብ መጀመሩ ቁልፍ እና አስፈላጊው ጉዳይ ሲሆን በእዚህ ፅንሰ ሃሳብ ዙርያ በኢትዮጵያ ያሉ ለዘመናት የቆዩ ችግሮችን በእየደረጃው ለመፍታት ትልቅ በር ከፋች ነው።ይህ የሚሆነው ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ የእኔ ብሎ ንቅናቄውን ሲደግፍ እና ንቅናቄውም እራሱን ሁሉን አቀፍነቱን እያሰፋ ሲሄድ ነው።



ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...