ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, October 21, 2016

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤትን በንግድ ዘርፍ ማኅበራት ስም ዛሬም እያነታረኩት ነው (የጉዳያችን ማስታወሻ)


ጉዳያችን/ Gudayachn
ጥቅምት 12/2009 ዓም
==========================
ሕወሓት ካመሳቸው በኢትዮጵያ ጠንካራ አደረጃጀት ካላቸው ተቋማት ውስጥ  የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት አንዱ ነው። ይህ በ1940 ዓም (1947 እኤአ) በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ ክትትል የተመሰረተው እና የኢትዮጵያን የንግድ እንቅስቃሴ ዘመናዊ መልክ ለማስያዝ ትልቅ ሚና የተጫወተ ተቋም የሕወሓት ዱላ ያረፈበት ገና ከጅማሮው መሆኑ ይታወቃል። 

ምክር ቤቱን ለማዳከም እና በአንድ ጎጥ ስር ለመቆጣጠር ከመሞከር ጀምሮ እስከ በክልሎች የመከፋፈል ሥራ ከተሄደ በኃላ  ሕወሓት አማራጭ መንገድ አድርጎ ያቀረበው  ሌላው መንገድ ተለጣፊ ማደራጀት እና የዘርፍ ማኅበራት የሚባሉ እንዲለጠፉ እና  የምክር ቤቱን ቅርፅ የመቀየር ሙከራ ነበር።ሆኖም ግን በብዙ ትግል በኃላ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ስሙ ላይ የዘርፍ ማኅበራት የሚል ጨምሮ እንዲቀጥል ተደረገ።

በእዚህ መሰረት የዘርፍ ማኅበራት የሚባል መስርቶ በጥቃቅን ያደራጃቸውን ሳይቀር በካፒታል ከፍ ያሉትን አስርጎ አስገባ። እዚህ ላይ ለመድረስ ግን የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት እስከ ፍርድ ቤት ድረስ ያመላለሰው በርካታ ክርክሮች ሁሉ መደረጉ ይታወሳል።ምክር ቤቱን ይመሩ የነበሩት እነ አቶ ብርሃነ መዋ  እና አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ የገቡበት የተለያዩ አጣብቂኞች ነበሩ። አቶ እየሱስ ወርቅ ዛፉ በተለይ ከንግድ ዘርፍ ማኅበራት ጋር የነበሩ ክርክሮች ላይ የንግድ ምክር ቤቱን ለማቆየት በርካታ ውጣ ውረዶች አልፈዋል ።

ለእዚህ ማስታወሻ ምክንያት የሆነኝ እግር ጥሎኝ ዛሬ ጥቅምት 11፣2009 ዓም ሸገር ዜና ስሰማ ከተወሰኑ ዓመታት ስንሰማው የነበረው የንግድ ምክር ቤቱ ንትርክ አቶ ገብረ ሕይወት ከሚባሉ ሰው ጋር ቀጥሎ መስማቴ ነው።ነገሩ እንዲህ ነው። የንግድ ዘርፍ ማኅበራት  አቶ ገብረ ሕይወት ገ/ እግዚአብሔር የሚባሉ የቦርድ ባለስልጣን እና የደቡብን ዘርፍ ማኅበራት በመወከል ደግሞ አቶ አሸናፊ የተባሉ ሰው ምክር ቤቱ ጭቅጭቅ ላይ መሆኑን የተለዋወጡትን ቃላት የሚያሳየው የነበረውን ስዕል ነው።የደቡቡ አቶ አሸናፊ ቦርድ ሁለቴ እንዳይመረጥ ሕጉ ያዛል  ካሉ በኃላ አቶ ገብረ ሕይወት እንዴት ሁለቴ ተመረጡ? በማለት ይጠይቃሉ።
በምላሹ አቶ ገብረ ሕይወት ሕጉን ቆይተን ነው ያየነው በማለት በቦርድ ደረጃ ያሉ ሰው ስንቴ መመረጥ እንደሚችሉ በደንብ ሕጉን ሳያዩ በመቅረታቸው ድጋሚ ለምርጫ እንደመጡ ይገልፃሉ።

አቶ አሸናፊ ድሮ ገና ነው ሕጉን የተናገርኩት አልሰማ ብለው ነው በማለት ይመልሳሉ።ጉዳዩ የስርዓቱ የመከፋፈል እና ቀጥሎ የመቆጣጠር አባዜ ነው።ይህ ማለት የንግድ ምክር ቤት አንድ እንዳይሆን በክልል ይከፋፍሉታል።ቀጥለው እርስ በርስ ያነታርኩታል። ለሚቀርበው ክርክር ደግሞ ፍርድ ሲሰጡ እንደሚመቻቸው ወይንም ክርክሩን የበለጠ በሚያባብስ መንገድ ያደርጉታል።እንዲህ እያደርጉ ኢትዮጵያን በእየዘርፉ ያደማሉ፣ይዘርፋሉ።

ይችን ንትርክ ከላይ ካልኩት ጋር አገናኙት።ንግዱን የመቆጣጠር አባዜው 100% የሚያረካ አልሆነም።ከሁሉም የሚያሳፍረው ግን የንግድ ምክር ቤት ከደረጃ ዝቅ ያለ መሆን ማለት ለአንድ አገር ያለው አሉታዊ ተፅኖ ቀላል አይደለም።በሌሎች አገሮች በአፍሪካም ጭምር ከፍተኛ ክብር ያላቸው የንግዱ ማኅበረሰብ የሚወከሉበት እና የውጭ ኢንቨስተሮች ስለ አንድ ሀገር የፖለቲካም ሆነ የምጣኔ ሀብት ሁኔታ ለመረዳት ከፖለቲካ ሰዎች ይልቅ የንግድ ምክር ቤት አባላትን የበለጠ የሚያምኑበት ሁኔታ የሰፋ ነው።የአሁኑ የሕወሓት ምልምል የንግድ ምክር ቤት ግን ይህንን የሚያሟላ አልመሰለኝም።ምናልባት በቦታው ያሉትን በቅንነት የሚሰሩትን መንካት እንዳይሆንብኝ አይመስለኝም የሚለውን ያዙልኝ።

በአንድ ወቅት የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በግል ሕይወታቸው ዙርያ ከኢቢኤስ ቴሌቭዥን ጋር ያደረጉት ቃለ መጠይቅ ብዙ የሕይወት ተሞክሮን ያስተምራል።ከእዚህ በታች ያለውን ተጭነው ይመልከቱት። 

ጉዳያችን GUDAYACHN 

No comments: