ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, April 6, 2016

አቶ መለስን የሸለመው ''ያራ'' የተሰኘው የኖርዌይ ማዳበርያ አምራች ኩባንያ በሌላ ዓለም አቀፍ ቅሌት ተጋለጠ!


የያራ ኩባንያ ቦርድ አባላት እና አቶ መለስ ዜናዊ  መስከረም 3/2005 ዓም እ ኤ አ በአወዛጋቢው የያራ ሽልማት ስነ ስርዓት ላይ  ፎቶ : yara.com

 ይህንን ፅሁፍ ከመፃፌ አስር  ደቂቃዎች  በፊት ''አፍተን ፖስተን'' የተሰኘው የኖርዌይ አንጋፋ ጋዜጣ በድረ-ገፁ አንድ መረጃ ለቀቀ።ይህ ዜና ምናልባት ነገ የሚታተመው የጋዜጣው ገፅ ላይ  የሚወጣ ነው።ጉዳዩ ''ያራ'' የተሰኘው የኖርዌይ መንግስታዊ የማዳበርያ አምራች ኩባንያ ስለገባበት ሌላ ቅሌት ያትታል። ''ያራ'' የተሰኘው የኖርዌይ የማዳበርያ ፋብሪካ ደግሞ ከኢትዮጵያ እርሻ ጋር ባለፉት ሃያ አራት አመታት ውስጥ አንድ አነታራኪ ጉዳይ አለው።ይሄውም የኢትዮጵያ ገበሬ በብድር በብዛት ምርቱን እንዲወስድ በአቶ መለስ  የስልጣን ዘመን መገደዱ እና አቶ መለስ ከድርጅቱ ሽልማት ማግኘታቸው ዙርያ ያጠነጥናል።

የኢትዮጵያ የእርሻ መሬት በአቶ መለስ ዘመን ከተፈፀመበት ወንጀል ውስጥ አንዱ የኬሚካል ማዳበርያ ገበሬው በግድ እንዲወስድ መደረጉ ነው። በእርግጥ ማዳበርያ ለአንድ አገር እርሻ ምርታማነት አስፈላጊ ነው።ለእዚህም  የተፈጥሮ ማዳበርያ ተመራጭ እንደሆነ ይታወቃል።የተፈጥሮ ማዳበርያ ተመራጭ የሚሆንባቸው ምክንያቶች ውስጥ  የተፈጥሮ ማዳበርያ ምንም አይነት ለጤና የሚያመጣው ጉዳት የሌለ ከመሆኑም በላይ በእየዓመቱ መሬቱ ለምዶ ካለማዳበርያ ምርት አልሰጥም አለማለቱ ነው። የኬሚካል ማዳበርያ ግን ምርቱ ለጤና እስከ ካንሰር እና ተያያዥ በሽታዎች ሁሉ የሚያጋልጥ ከመሆኑም በላይ ማዳበርያውን የለመደ መሬት በእራሱ ቶሎ የመምከን ዕድል ስለሚኖረው በእየዓመቱ ሱስ እንደያዘው ሰው ካለ ማዳበርያ ምርት የመስጠት አቅሙ በብዙ ደረጃ ስለሚቀንስ ነው።

በ1983 ዓም አቶ መለስ እና ሰራዊታቸው መንበረ ስልጣኑን ሲቆናጠጡ በመጀመርያ ያደረጉት ገበሬው የኬሚካል ማዳበርያ በብድር እንዲወስድ ማድረግ ነው።በወቅቱ የእርሻ ምርምር ባለሙያዎች ለኢትዮጵያ የሚጠቅማት የተፈጥሮ ማዳበርያ እንደ ፍግ፣እና ብስባሽ እንጂ ኬሚካል ማዳበርያ መጠቀም የለብንም በማለት መንግስትን ለማስረዳት ሞከሩ። አቶ መለስ እና ስርዓታቸው ግን ፈፅሞ አልተቀበለውም። ለእዚህም ዋነኛ ምክንያቱ እንደ ''ያራ'' ከመሰሉ ኩባንያዎች ጋር ያላቸው የውስጥ የጥቅም ግንኙነት ነው በማለት ብዙዎች አስተያየታቸውን ሲሰጡ ነበር።ይብሱን ''ያራ'' መስከረም፣2005 ዓም እ ኤ አቆጣጠር አቶ መለስን እንደሚሸልም መግለጡ እና ለሽልማቱ የተሰጠው ምክንያት ግልፅነት ማጣት ከፍተኛ ጥርጣሬ በብዙዎች ዘንድ አደረ።በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ጉዳዩን ይፋ አውጥተው በግልፅ ያራን እና አቶ መለስ ግንኙነት ጤናማ አለመሆኑን በተቃውሞ ሰልፍ ጭምር ገለጡ።

የሽልማቱ ጉዳይ የዓለም አቀፍ ዜና ድርጅቶችንም ጭምር ግራ አጋብቶ ነበር።የአቶ መለስ እና የያራ ግንኙነት ምንድነው? አቶ መለስ ምን ስላደረጉ ነው የተሸለሙት? የሚለውን ጥያቄ ለመፍታት ብዙዎች ጉዳዩን ደጋግመው አብላሉት።ከእዚህ ሁሉ ሂደት በኃላ ግን ነጥሮ የወጣው ጉዳይ አቶ መለስ ቢሮአቸው ላይ የመጣውን የግዥ ስምምነት እየፈረሙ መፍቀዳቸው እና ኢትዮጵያ  ከተፈጥሮ ማዳበርያ ይልቅ የኬሚካል ማዳበርያ ገበሬው እንዲጠቀም እስከታች ድረስ ትእዛዝ መውረዱ ነበር። ከእዚህ በተጨማሪ ማዳበርያ  አልፈልግም ያለ ገበሬ እንደ ፀረ-ምርታማ አስተሳሰብ አራማጅ እየተወሰደ በካድሬዎች እና በግብርና ኤክስተሽን ሰራተኞች የግድ የማዳበርያ ብድር ውስጥ እንዲዘፈቅ እና ማዳበርያው እንዲገዛ መገደዱ ሌላው አቶ መለስ እና አመራራቸው በኢትዮጵያ ገበሬ ላይ የጣሉት ቀንበር ነበር። በእዚህም ሥራ የ''ያራ'' ኩባንያ ሽያጭ እንዲንር ተደረገ።

ከእዚህ በስተጀርባ ሌላ የሕወሃቱ የንግድ ድርጅት ኤፈርት እጅ ደግሞ ጎልቶ ወጥቷል።በዘመነ ደርግ የኢትዮጵያ ራድዮ እና ቴሌቭዥን በነበራቸው የግብርና ፕሮግራም ላይ ሁሉ ለገበሬው የሚያስተላልፉት መልእክት የተፈጥሮ ማዳበርያ የመጠቀምን ሁለት ጥቅም ነበር። አንዱ ለመሬቱ ጤናማነት ሲሆን ሁለተኛው ደርግ ትልቅ እራስ ምታት የነበረበት የውጭ ምንዛሪ የማዳን ጥቅም በመግለፅ ነበር። አቶ መለስ እና አቶ ተፈራ ዋልዋ ግን ገበሬውን የመከሩት ዘመናዊ ማዳበርያ ተበድሮ ገዝቶ መሬቱን እንዲያመክን ነበር።እግረ መንገዳቸውንም ቀድሞ በርካታ ምርቶችን በማስመጣት የሚታወቀውን ''አማልጋሜትድ'' ኩባንያ አዋክበው ማፈረስ እና ማዳበርያ የማስመጣት ንግዱን የኤፈርት ኩባንያ እንዲወስድ አደረጉ። የእዚህ አይነቱ ድርጊት በኢትዮጵያ እርሻ ላይ እና አገራዊ ሀብት ላይ ያመጣው ውድመት በአግባቡ ቢጠና በርካታ መዘዞችን ይዞ ብቅ ማለቱ አይቀርም። 

ይሄው አቶ መለስን ከአስር ዓመት በፊት ሸለምኩ ያለው ኩባንያ ዛሬ በሌላ የጉቦ መስጠት ቅሌት ተጋልጧል።በኖርዌይ ሲታተም ከ150 አመታት በላይ ያስቆጠረው  እና አንጋፋው  ''አፍተን ፖስተን'' ጋዜጣ ''የኖርዌይ መንግስት ንብረት የሆነው ያራ ኩባንያ ካሪብያን ለሚገኙ የሼል ኩባንያዎች የ2.6 ሚልዮን ዶላር ጉቦ ሰጠ'' ''State-owned Yara paid $ 2.6 million in bribes to shell companies in the Caribbean'' በሚል ርዕስ ስር  ሰፊ ዘገባ አዘጋጅቷል።ጋዜጣው በኖርዌይኛ ስለተፃፈ  ቋንቋውን ለማትረዱ  ወደ ጉግል ወስዳችሁ ወደ እንግሊዝኛ ወይንም አማርኛ መተርጎም ይፈልጋል።
የአፍተን ፖስተን ጋዜጣ ያወጣው ዘገባ ሊንክ  ለማንበብ ይህንን  ይጫኑ።በተጨማሪም ጋዜጣው   ስለ ያራ የወጣው ዘገባ  ለኖርዌይ ህዝብም አዲስ መሆኑን  ያብራራል።ሰሞኑን ያራ የብዙሃን መገናኛዎች መነጋገርያ ርዕስ ቢሆን ብዙም እንዳትገረሙ።


ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com
መጋቢት 29/2008 ዓም (አፕሪል 7/2016) 

No comments:

ለፕሮፌሰር መራር፣ልደቱ፣ጀዋርና ኢንጅነር ይልቃል ዘፈን ይህችን ዜማ እንምረጥላቸው።

በቅድምያ ስለ አራቱም የመግቢያ ማስታወሻና ወቅታዊ ሁኔታቸው። አራቱም ከመስከረም በኋላ መንግስት የለም ብለው ኢትዮጵያን ለእርስ በርስ ጦርነት ሊነክሯት ሞክረዋል።ዝርዝሩን፣ከእነማን ጋር መክረው እንደነበር፣ለኢትዮጵያ ደግሰው...