ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, April 3, 2016

የማኅበረ ቅዱሳን ዐውደ ርእይ መታገድ ያስታወሰኝ የማኅበረ ቅዱሳኗን ወጣት ወይዘሮ እውነተኛ ታሪክ (የጉዳያችን ማስታወሻ)
ኢትዮጵያ ምናልባት በዓይነትም፣በብቃትም፣በትህትናም  እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ትውልድ ያለ በአንድ ዘመን እና በስብስብ መልክ በብዙ ውጣ ውረዶች መካከል ለስራ ጊዜውን የሰጠ ትውልድ አግኝታ ታውቃለች ወይ? ብዬ እራሴን ስጠይቅ መልስ አጣለሁ።ውስጣቸው ስለ እምነታቸው ይንተከተካል፣የአገራቸው ጉዳይ ይንጣቸዋል፣ ቂም ማንንም ላይ አይጠመጥሙም።የትኛውንም ግለሰብ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ያከብራሉ።በትምህርት ደረጃቸው ከከፍተኛው ፕሮፌሰር እስከ አሜሪካው የጠፈር ምርምር ድረስ ተሰርማርተው ይሰራሉ።ሆኖምግን ትሑታን ናቸው።ከተሰማሩበት መደበኛ ሙያ በተጨማሪ ያላቸውን ጊዜ እንደ ሰው ሲኒማ ፣ቲያትር አልያም በእየካፌው ቁጭ ብለው ወጪ ወራጁን ሲመለከቱ አይውሉም።ይህ ማለት ግን ከኪነ ጥበብ የራቁ ናቸው ማለት አይደለም።ይልቁንም በጥበቡ ዓለም የተራቀቁበት አንቱ የተባሉ ከመካከላቸው አሉ።አሁንም ግን ትሕትናን እና እራስን መግዛት ከሁሉ በፊት የቀደመ ገንዘባቸው ነው።

ከመደበኛ ጊዜያቸው በተጨማሪ በሃይማኖታዊ፣ማሕበራዊ እና ሰብአዊ ጉዳዮች ላይ ለማዋል ደፋ ቀና ይላሉ። በእዚህ በጎ ተግባር በርካታ ችግሮች የገጠማቸው አሉ።ስብዕናቸው የሚማርክ፣ተናግረው የሚያሳምኑ፣እውነኞች ሰዎች ማኅበረ ቅዱሳን ውስጥ ታያላችሁ።ይህ ማለት ከማንም ፍጡራን የተለዩ ናቸው እያልኩ አይደለም። እንደማንም የሰው ባህሪ ስህተት፣ማጥፋት ይኖራል።ፍሬያቸው ግን ሁሌ እየቀደመ ልቦናን ያርሳል።ከእዚህ በታች እውነተኛ ስሟን የማልጠቅሳት ወጣቷ ወይዘሮ በሚል እውነተኛ ታሪክ ላስነብባችሁ ነው። አንዳንድ ጊዜ ማኅበረ ቅዱሳን ሲባል በውስጡ በምን ያህል ደረጃ እራሳቸውን ለሚያገለግሉት መንፈሳዊ አገልግሎት የሰጡ እንዳሉ የማንረዳ ብዙ አለን።ታሪኩ እውነተኛ እንደመሆኑ መጠን በትንሹ አንዷን የማኅበሩን አገልጋዮች ስሜት የምታሳይ ትመስለኛለች። ወጣቷ ወይዘሮ እነሆ:- 

ወጣቷ ወይዘሮ 

ስትናገር ትሕትናዋ ከፊቷ ላይ ይነበባል።የድምፅ ቅላፄዋ ለትልቅ የቴሌቭዥን ጣብያ መርሃ ግብር አቅራቢነት የተስማማ ነው።እንግዳ ስታናግር አንገቷን በትንሹ ወደ ጎን ዘንበል አድርጋ ነው።የሚያከራክር ጉዳይ ቢገጥማት ተናጋሪው ተናግሮ እስኪጨርስ ጠብቃ ታወራለች እንጂ ለነገር ምላሽ በላይ በላዩ መናገር አይሆንላትም። ወጣቷ ወይዘሮ በምጣኔ ሀብት ማስተርስ ከሰራችበት ከባህር ማዶ ዩንቨርስቲ ትምህርቷን አጠናቃ ወደ አገሯ ስትመለስ እንደ ሌሎች በወጣችበት አገር የመቅረት እና የበለጠ ክፍያ የማግኘት ዕድል እንዳላት አልጠፋትም። ነገር ግን አገሯ ያለው ድህነት ሕሊናዋን እንደ እሾህ እየወጋት እረፍት ነስቷታል።እናም ወደ አገሯ ካሉት ችግሮች ጋር ሁሉ ተጋፍጣ ለመስራት ተመለሰች።

ወደ አገሯ ከተመለሰችም በኃላ በአንድ የምዕራብ አህጉራዊ የጥናት ማዕከል ዳጎስ ባለ ደሞዝ ሥራ አግኝታለች።ማኅበረ ቅዱሳን በምትሰጠው አገልግሎት ደግሞ ሙሉ እሷነቷን ሰጥታለች።የገዳማቱ መፍረስ፣የመነኮሳቱ መሰደድ፣የመምህራኑ የሚበሉት ማጣት እረፍት ነስቷታል።ከቀን ስራዋ እንደወጣች እስከ እኩለ ሌሊት በሳምንት ሁለት ቀናት ደግሞ እያደረች የማኅበሩን የአገልግሎት ተግባራት ትሰራለች።ባብዛኛው በገዳማት እና የአብነት ትምህርት ቤቶች ሥራ የሚሰሩ ስራዎች ላይ ሁሉ በነፃ ታገለግላለች።በእዚህ ሁሉ ላይ የበተሰቧን፣የልጆቿን እና የባለበቷን ጊዜ ሁሉ የምታጠፋው እዚሁ አገልግሎት ላይ ነው።

መኮረኒው 

ወጣቷ ወይዘሮ ከስራ መጥታ ወደ ማኅበረ ቅዱሳን  አገልግሎት ልትወጣ ስትል የቤት ሰራተኛዋ ለመኪናዋ የውጭ በር እየከፈተችላት ነበር።በሩን አልፋ ልትሄድ የመኪናዋን የፊት አካል እዳስወጣች  ሰራተኛዋ ልታናግራት እንደምትፈልግ በእጇ ምልክት ስትሰጣት በኃላ መስኮት ተመለከተቻት። ወዲያው ቶሎ ብላ  በመስኮት የመኪናዋን መስኮት ዝቅ አድርጋ 

'' ወዬ ምነው? የምጠይቂኝ ነገር አለ?'' ብላ ጠየቀቻት። የቤት ሰራተኛዋ '' አዎ! ዘይት ገዝተሽ ነይ ብዬሻለሁ እረስተሽዋል።ደሞ ልጆቹ ነገም መኮረኒ ይዘው ትምህርት ቤት ሊሄዱ ነው?'' አለች የቤት ሰራተኛዋ። ወጣቷ ወይዘሮ ሁለት እጆቿን መኪናዋ መሪ ላይ እንዳደረገች ወደ ፊት ያለው መንገድ ላይ አይኗን እንደተከለች ፍዝዝ አለች። ቀጥላ አይኖቿን ወደ ሰራተኛዋ ስትመልስ አይኗ እንባ ሊፈሰው ሙሉ በሙሉ ገበታ ላይ እንደተንጣለለ ውሃ ይዋልላል። የቤት ሰራተኛዋ ተደናገጠች 
''ምነው ታትየ ልጆቹ እኮ ምንም አላሉም እኔ ነኝ እንዲሁ ሳስበው ትናንት መኮረኔ ዛሬም ብዬ ነው'' አለች እና ወደ መሬት አቀርቅራ መሬቱን ባደረገችው ኮንጎ ጫማ በትንሹ ትጭር ጀመር።

''አንቺ አላጠፋሽም።አንቺማ ትክክል ነው የነገርሽኝ'' አለች ወጣቷ ወይዘሮ '' አየሽ አንቺ የእኔ ልጆች መኮረኒ እንዳይሰለቻቸው ስትይኝ እኔ ደሞ የሚበሉት ዳቦ ያጡት ጅማ  መንገድ ኪዳነ ምህረት የተጠለሉት ልጆች ትዝ አሉኝ።እድሜ ልካቸውን ከውሻ እና ከዘራፊ ጋር እየታገሉ ተምረው ሊቃውንት ተብለው መከበር ሲገባቸው በልመና በእየከተማው የሚንከራተቱት በአይኔ መጡ።ስለ ልጆቹ አትጨነቂ ምን ጎደለባቸው።ብዙ ለህሊና የሚከብዱ ችግረኞች አሉ።'' አለችና ከመኪናዋ በስተቀኝ ካለው ወንበር ፊት ለፊት ያለውን ኪስ ከፍታ ሶፍት አውጥታ የአይኗን እንባ መጥረግ ጀመረች። ቀጥላም የሰራተኛዋን ስሜት መጠበቅ እንዳለባት አሰበች እና ፈገግታ አሳይታት ከግቢው ወጣች። 

የስራ መልቀቂያው 

ሰዓቱ ከምሽቱ አራት ሰዓት ሆኗል።ወጣቷ ወይዘሮ ወደ ቤቷ ገና መግባቷ ነው።ለወትሮው እንደመጣች ልጆቿን እና ባለቤቷን ስማ  ቀጥታ ወደ መኝታቤት ገብታ ልብሷን ትቀይር ነበር።ዛሬ ግን ሁሉንም ከሳመች በኃላ ቦርሳዋን እንደያዘች  በደከመ ስሜት ሶፋው ላይ ተቀመጠች። ልጆቿን ባለቤቷን አየቻቸው።አንድ ውሳኔ የሚያስፈልገው ጉዳይ ገጥሟታል።በገጠር እርዳታ የሚፈልጉ እና አፋጣኝ የድረሱልን ደብዳቤ የፃፉ አብያተ ክርስቲያናት እና የአብነት ትምህርት መምህራን ደብዳቤ ስታነብ ነው የዋለችው። ለእነኝህ ሁሉ ፕሮጀክት በአፋጣኝ ተቀርፆ እና እርዳታ ተፈልጎ ወደ ሥራ መገባት አለበት።ይህ ሁሉ ሥራ ደግሞ አሁን ቀን ከምትሰራበት የአማካሪ ድርጅት በተረፈ ሰዓት ምሽት ላይ እና አንዳንዴም እየታደረ ተሰርቶ  የሚሳካ አይደለም።በመሆኑም ሁለት አጣብቂኝ ውስጥ ገባች። አንዱ አሁን የያዘችውን ምናልባትም በቅርብ ልታገኘው የማትችለውን ሥራ ትቶ ለተወሰኑ ወራት ምናልባትም አመታት የአብያተ ክርስቲያናቱን ፕሮጀክት በሥራ መተርጎም ወይንም ችግሩን እየሰሙ  ከንፈር እየመጠጡ መኖር።ስራዋን ከለቀቀች ደግሞ በባሏ ደሞዝ ብቻ ልጆቹን ትምህርት ቤት ከፍላ፣የቤት ወጪ ሽፍና የማይቻል ነው።ነገር ግን የልጆቿ ችግር ምንም የሚበሉት ከሌላቸው መምህራን እና ገዳማውያን ጋር ማነፃፀር አልፈለገችም። ለባለቤቷ አማከረችው።በጉዳዩ ሁለቱም አዘኑ። እርሷ ግን በእዚችው  ምሽት ኮምፒተሯን ከፍታ የስራ መልቀቅያ ደብዳቤ ማርቀቅ ጀመረች። አንድ አንቀፅ ፅፋ ወደ ልጆቿ ቀና ብላ አየች ይስቃሉ።'እግዚአብሔር ያሳድጋችኃል' አለች በልቧ እና መልቀቅያ ደብዳቤዋን መፃፍ ቀጠለች። ወጣቷ ወይዘሯ ይህንን ሥራ ለመልቀቅ እና የገዳማውያኑን ፕሮጀክት በነፃ ለመስራት ስትወስን የምትለቀው ሥራ ከሁለት አስር ሺዎች ብር በላይ ደሞዝ ይከፈላት የነበረ ሥራ ነበር።

እንዳሰበችው አልቀረም ጧት ማመልከቻዋን ለአለቃዋ ሰጠች።አለቃዋ ጤንነቷን ተጠራጠሩ።የገጠማት  የስራ ችግር ካለ እንደሚያስተካክሉላት።አስፈላጊ ከሆነ ከእነ ቤተሰቧ የድርጅቱ ቅርንጫፍ ባለበት በየትኛውም የዓለም ክፍል እንደሚያስመድቧት ቃል ገቡ። ወጣቷ ወይዘሮ  ግን አልተቀበለችም። ይልቁንም የምስኪኖቹ መነኮሳት እና መምህራን ሕይወት እየታወሳት ሲቃ ያዛት። በመጨረሻ አለቃዋን ለደግነታቸው ሁሉ አመስግና ተሰናብታቸው ቀጥታ በነፃ ለማገልገል ወደ ማኅበረ ቅዱሳን ፅህፈት ቤት አመራች። 

 በግዮን ሆቴል ኮሪደር ላይ  

ወጣቷ ወይዘሮ ከፍተኛ ደሞዝ የምታገኝበትን ሥራ ለቃ የገዳማቱን እና በመላው አገሪቱ ግዛት ለተቀረፁ ፕሮጀክቶች ሙሉ ጊዜዋን ሰጠች።ባለቤቷ የሚስቱን ስሜት ለመጠበቅ የቤት ውስጥ ያሉ ችግሮችን ሳይነግራት በቻለው እየሸፈነ አሳለፈ።ወይዘሮዋ ለአንድ ዓመት የፕሮጀክቶቹን ስራዎች በርካታ በነፃ የሚያገለግሉ ወጣቶች ጋር ሆና በርካታ ፕሮጀክቶች አስነደፈች፣በጀት አፈላልጋ አገኘች። ከአንድ ዓመት በፊት የተሰማት  ተስፋ መቁረጥ በብርታት ሲቀየር ተሰማት።ይህንን ተግባሯን የሰሙ በዝናዋ  እና በችሎታዋ ባለፈው ትሰራው የነበረ ተመሳሳይ ሥራ አገኘች። ሕይወት ቀጠለ።

የካቲት፣2006 ዓም ማኅበረ ቅዱሳን በገጠር ያሉ ገዳማት እና የአብነት ትምሕርት ቤቶች ችግር በእጅጉ ይቀርፋል የተባለ ፕሮጀክት ለመቅረፅ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ካላቸው የመንግስት አካላት፣የቤተ ክህነት መምሪያ አካሎች፣ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሁሉ ያካተተ የምክክር ጉባኤ በግዮን ሆቴል አዘጋጀ። ለማዘጋጀትም ቀደም ብሎ የቤተ ክህነትን ፈቃድ እና ደብዳቤ ሁሉ አግኝቶ ስለነበር እና የጉባኤው አላማ፣ግብ እና ተሳታፊዎች ሁሉ ቀደም ብሎ አሳውቆ ስለነበር አንዳች እክል ይገጥመዋል ብሎ ያሰበ የለም።ወጣቷ ወይዘሮ በተለይ ውስጧ የደማበት አንዱ ጉዳይ በእንደዚህ አይነቱ ጉባኤ አይነተኛ መልስ እንደሚያገኝ አምናለች እና እጅግ ተደስታለች። 

ሆኖም ግን የታሰበው እና የሆነው ተለያየ።ማኅበሩ ለግዮን ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ ከከፈለ በኃላ እንግዶቹን ጠርቶ እየተጠባበቀ እና ጉባኤው ሊከፈት ሰዓታት ሲቀሩት።ጉባኤው ታግዷል የሚል አሳዛኝ ዜና ደረሰ። አንዳንዶቹ እንግዶች ከዓለም ባንክ ተወካዮች ጨምሮ የሚሳተፉበት ስለነበር እንደ አገርም የሚያሳፍር ነበር። ወጣቷ ወይዘሮ ይህንን ስትሰማ በግዮን ሆቴል ኮሪደር ላይ እንደቆመች እንባዋ ጉንጮቿን ሳይነካ ወለሉ ላይ ተንጠባጠበ። ሰውነቷ ተንቀጠቀጠ።ለምን? ለአገራችን በነፃ በሰራን? በእራሳችን ገንዘብ የተቸገሩትን በረዳን? ለቅሶዋን መቆጣጠር አልቻለችም። አብረዋት የወጡት የወረዱት  ሁሉ ልባቸው ተሰበረ።ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑት በአገሪቱ አሉ የተባሉ ለጉባኤው የመጡ ሊቃውንት በማኅበረ ቅዱሳን ቢሮ ገብተው ፈሰሱ።ጉባኤው መሰረዙን ሲሰሙ እንባቸውን ወደ መንበረ ፀባኦት እረጩ። ወጣቷ ወይዘሮ ለእዚህ ጉባኤ ከቤት ወጥታ ማኅበረ ቅዱሳን እያደረች ስትሰራ ሶስት ቀናት ሆኗታል። ልጆቿን ከትምህርት ቤት ሲመጡ ባለቤቷ በአራት ኪሎ በኩል ሲያልፍ ለአንድ አፍታ ወጥታ ስማቸው ወደ  ማኅበሩ ፅህፈት ቤት ትመለሳለች። ይህንን ያህል የደከመችለት ጉባኤ በሁለት መስመር በፓትርያሪኩ እና አጋሮቻቸው ከመንግስት ጋር ሆነው አሳገዱት። እንደ ቀላል ነገር አስቆሙት። ከፍሪጅ ውስጥ ጭማቂ አውጥቶ እንደመጠጣት ቀላል አደረጉት አና አስቆሙት። ወጣቷ ወይዘሮ ግን በግዮን ሆቴል  ኮሪደር ላይ እንቅልፍ አጥቶ በሰነበተ አይኖቿ እንባ አውጥታ አለቀሰች። 

የጨለማው ቡድን አባላት በጎጥ ከተደራጀው መንግስታቸው ጋር ሆነው ዛሬም  የቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ  እንደ ገና የበግ ቅቅል አጥንት የሚግጡቱ የውስኪ ቤት ደንበኞች ግን ተሳሳቁ።እነርሱ አንዴ በሃይማኖት፣አንዴ በካድሬ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በጎጥ ካባ እየተምነሸነሹ  የዋሃኑን እንባ ያራጫሉ።ባለፈው ሳምንትም በአዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማዕከል የተዘጋጀውን ዐውደ ርእይ መርሃ ግብሩ ሊከፈት ሰዓታት ሲቀሩት በጎጥ በተቧደነ መንግስታቸው አማካይነት ሲያሳግዱ አመድ እንደቃመ እንስሳ እያስካኩ ነበር።ብዙዎች የወጣቷ ወይዘሮ መሰሎች ግን እንባቸው በጉንጫቸው ላይ እየወረደ ነው።በገዳማት ያሉት የማኅበረ ቅዱሳን የትሩፋት ሥራ የሚያውቁ መናንያን ሁሉ ግን በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ለተሰራው ግፍ ፍርድን ከሰማይ እያስቆረጡ ነው።ይህ ትውልድ በጎጠኞች የተሰራበት ግፍ እንዲህ በእዚች አጭር ፅሁፍ የሚያልቅ አይደለም።በርካታ ጥራዞች የሚወጣቸው ታሪኮች ታሪክ ፀሐፊዎችን እየጠበቁ ነው።ውሎ አድሮ ግን ይህ ሁሉ ግፍ ለግፈኞቹ የማይራመዱት እሾህ ማብቀሉ አይቀርም። ግፍ 


የግዮኑ ጉባኤ እግድ ዜና ለማንበብ ይህንን ይጫኑ:- https://haratewahido.wordpress.com/2014/02/14/ሰበር-ዜና-ማኅበረ-ቅዱሳን-ለአብነት-መምህ/ 

የማኅበረ ቅዱሳን ከሳምንት በፊት በመንግስት የታገደው ዐውደ ርእይ መግለጫ ቪድዮ https://www.youtube.com/watch?v=rEYPrD9s13Q 


ጉዳያችን GUDAYACHN

 www.gudayachn.com 
መጋቢት 26/2008 ዓም 

No comments: