ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, April 14, 2016

ምግብ የመብት ጉዳይ ነው። መንግስት በረኃቡ ጉዳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊከሰስ ይችላል።የዩንቨርስቲ ተማሪዎች፣የከተማ ነዋሪዎች እና ገበሬዎች ሁሉ ለተራበው ሕዝብ መጮህ ካለባቸው ወቅቱ አሁን ነው! (የጉዳያችን ማስታወሻ)

የተባበሩት መንግሥታት የምግብ መብት ጉባኤ (Photo:- srfood.org)

እንደ ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ዘገባ በኢትዮጵያ ከሚኖረው ሕዝብ ከአምስቱ አንዱ ርኃብ አደጋ ላይ ነው። ዓለም አቀፍ የሕፃናት አድን ድርጅት - ዩኒሴፍም ዘገባውን ስያጠናከር በኢትዮጵያ የስድስት ሚልዮን ሕፃናት ሕይወት አደጋ ላይ ነው ብሏል።በሌላ በኩል በከተማ የሚኖረው ሕዝብ የኑሮ ውድነቱ ጣርያ ነክቶበታል።የብሔራዊ ባንክ ጥናት እንደሚያሳየው የዋጋ ግሽበቱ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 12% ደርሷል።ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች 90 ቀናት የእርዳታ ማሰባሰብያ መርሃ ግብር አዘጋጅተዋል።በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ግን በይፋ እንዳይጠይቁ ታግደዋል። (Ethiopian government stops fundraising campaign by UN agencies)
ይህ ጉዳይ ዓለም አቀፍ ወንጀልም ነው።ምግብ ከመኖር ህልውና በላይ የሰብአዊ መብት ጉዳይም ነው። መንግሥታት፣ግለሰቦች እና ኩባንያዎች ሰዎች ምግብ እንዳያገኙ ለሚያደርጉት ማናቸውም እንቅስቃሴ እና ኃላፊነት ያለመወጣት ተግባር ሁሉ በሕግ እንዲጠየቁ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ጥቂት አመታት ተቆጥረዋል

ምግብ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ነው (Right to food) የሚለውን መመርያ በአገራቸው ለተግባራዊነቱ ሥራ ከሚሰሩት አገራት ውስጥ ኤልሳ ልቫዶር፣ዮርዳኖስ እና ህንድ  ይገኙበታል።የምግብ መብት ዓለም አቀፍ ሕግ የማድረግ እንቅስቃሴ የመነጨው ከተባበሩት መንግስታት የምጣኔ ሀብት፣የማኅበራዊ እና የባሕል መብት ፅንሰ ሃሳብ ሲሆን እኤአቆጣጠር በ2012 ዓም 160 አገራት ጉዳዩን ከፍ ወዳለ ዓለም አቀፍ ሕግ ቅረፃ ለማሳደግ የመግባብያ ፊርማቸውን አስቀምጠዋል።የመግባብያ ሰነዱ አገራቱ ምግብ የመብት ጉዳይ መሆኑን የሚያሳይ ፖሊሲ በአገራቸው እንዲያወጡ እና በዓለም አቀፍ ደረጃም ተግባራዊ እንዲሆን ያሳስባል። 

በእዚህም መሰረት በ20013 እኤአ ህንድ የምግብ መብት ሕግን በብሔራዊ ሕግ ውስጥ አካተተች።ምግብ የመራብ እና አለመራብ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን መንግሥታት ብሔራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ግዴታቸውን የመወጣታቸው እና ያለመወጣታቸው ጉዳይም ጭምርም ነው።ለአንድ ሕዝብ ምግብ እንዳይደርሰው ማድረግ ከዘር ማጥፋት ወንጀል እኩል ያስጠይቃል።የምግብ ጉዳይ የኢትዮጵያቴሌቭዥን ሲመቸው ስለረሃብ ሳይመቸው ዘፈን የሚያቀርብበት ጉዳይ አይደለም።በኢትዮጵያ የሰው መብት ከሚታሰበው እና ከሚገመተው በላይ በአምባገነኑ ስርዓት ስለተረገጠ ጉዳዩን አቅልሎ የማየት አዝማምያ ይስተዋላል።ሆኖም ግን ጉዳዩ ቀላል ጉዳይ አይደለም። የሚወራው ስለ ሚልዮኖች ሕይወት ነው።የተራበው የኖርዌይን ሕዝብ ሶስት እጥፍ የሚሆን ሕዝብ ነው።ይህ ሕዝብ እንደ ምንም ነገር ዝም ሊባል አይገባም።

የምግብ መብት ጉዳይ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ በአገራት የውስጥ ፖሊሲ ከመግባት ባለፈ መንግሥታት ፍርድ ቤት አስቁሞ አስፈርዷል።በኔፓል 1998 የአገሪቱ ከፍተኛው ፍርድ ቤት መንግስቱን ምግብ ለሕዝቡ ባለማዳረሱ ምግብ እንዲያከፋፍል ፈርዶበታል።በህንድም በተመሳሳይ መልክ የእርዳታ ድርጅቶች ተሰብስበው የህንድን መንግስት  ለሕዝቡ  ምግብ ባለማድረሱ  የሚል ክስ መስርተው አስፈርደውበታል።

በመጨርሻም  ምግብ ለሕዝብ እንዳይደርስ የማድረግ ሂደት ከቢሮክራሲያዊ ድክመት ባለፈ በአገር ውስጥ የሚፈጥረው የውስጥ ቅራኔ ቀላል አይደለም።በአሁኗ በህወሓት የጎሳ ፖለቲካ የተከፋፈለች ኢትዮጵያ ውስጥ ምግብ እንዳይደርስ የተደረገው አካባቢ ከጎሳ ጭቆና አንፃር ሊመለከተው ስለሚችል ጉዳዩ ውስብስብ ችግር ይዞ መምጣቱ አይቀርም።በመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ መንግስት እየደበቀ ያለውን ርኃብ በግልፅ በአደባባይ በመቃወም የተሻለ ብሔራዊ መግባባት እና አንድነት መፍጠር ይችላል።የተራበው አካባቢ ሕዝብ በርቀት የሚኖረው ወገኑ እንደሚያስብለት የማሳያው እና ሌላው አንድነት የመፍጠርያ አጋጣሚም ነው።ስለተራበው ሕዝብ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች፣ምሁራን፣የከተማ ነዋሪዎች እና ገበሬዎች ሁሉ መጮህ ካለባቸው ወቅቱ አሁን ነው።ሚልዮኖች ከመርገፋቸው በፊት ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንድረስለት።



ጉዳያችን Gudayachn
 www.gudayachn.com

የመረጃ ማጣቀሻዎች

http://www.ohchr.org/EN/Issues/Food/Pages/FoodIndex.aspx

http://www.fao.org/3/a-i4145e.pdf

http://www.srfood.org/en/un-special-rapporteur-archive

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።