ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, March 8, 2016

በኢትዮጵያ የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናት ቁጥር እየጨመረ ነው።100 ሺህ ሕፃናት በአዲስ አበባ፣በሌሎች ከተሞች ደግሞ 600ሺህ ሕፃናት የጎዳና ተዳዳሪ ናቸው።150ሺህ መንግስት ያመነው ቁጥር ነው።(ጉዳያችን)

በአዲስ አበባ የነገ ትውልድ ተረካቢዎች የትምህርት ጊዜያቸው እንዲህ እየባከነ ነው
 በኢትዮጵያ ምን ያህል ማኅበራዊ ቀውስ እየደረሰ መሆኑን እና ለእዚህም መንግስት ምንም የአጭር እና የእረጅም ጊዜ የመፍትሄ ሃሳብ የሌለው ነገር ግን በድንገት የጎዳና ተዳዳሪዎችን በሙያ አሰለጠንኩ እያለ መልሶ ወደ ጎዳና  እያወጣቸው መሆኑን የምናውቅ ብዙ አይመስለኝም። በተለይ ቁጥር ብዙ ነገርን ያመላክታል እና የችግሩ ግዝፈት ምን ያህል እንደሆነ ለማየት የዩኒሴፍ እና የኢሪን ሪፖርት መሰረተ በማድረግ እንደሚከተለው ለማቅረብ እሞክራለሁ።
ከጥቂት አመታት በፊት የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት አድን ድርጅት (UNICEF)፣ 4.6 ሚልዮን ሕፃናት ወላጅ አልባ መሆናቸውን እና በአዲስ አበባ ብቻ 30% የሚሆኑ እድሜያቸው በ10 እና 14 መካከል ያሉ ልጃገረዶች ከወላጆቻቸው ውጭ ይኖራሉ ይላል። በእዚህ ሪፖርት መሰረት ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ቀዳሚ ከሚባሉት የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናት የበዛባቸው አገሮች ተርታ መሆኗንም ይሄው ሪፖርት አክሎ ያብራራል። ይህ አስደንጋጭ ሪፖርት ነው።
የቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት የዜና ወኪል (ኢሪን (IRIN) (ካለፈው ዓመት ወዲህ ከተባበሩት መንግሥታት ጥገኝነት ወጥቶ በመላው ዓለም ከ200 በላይ ወኪሎቹ አማካይነት በግል የዜና ወኪልነት ቀጥሏል) ቀደም ባሉ አመታት እንደዘገበው በኢትዮጵያ የጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር እራሱ የሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያመነው 150 ሺህ ሲሆን የእርዳታ ድርጅቶች ግን በአዲስ አበባ ብቻ ቁጥሩን 100ሺህ ሲያደርሱት በሌሎች ከተሞች የሚገኙትን ሲጨምር ከግማሽ ሚልዮን በላይ ማለትም 600 ሺህ እንደሚደርስ በጥናታቸው እንደገለፁ ያብራራል።ይህ የሁሉም ሕብረተሰብ ኃላፊነት ቢሆንም በቀዳሚነት ግን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ቀዳሚ ኃላፊነት ነው። ከላይ የተጠቀሱት ሪፖርቶች ወዲህ በርካታ መፈናቀሎች እና የድህነት መጠኑም በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ይታወቃል።ይህ ማለት በአሁኑ ጊዜ ከላይ በዩኒሴፍም ሆነ በኢሪን የቀረቡት ቁጥሮች የበለጠ እንደሚሆኑ ይታመናል።ከእዚህ ጋር በተያያዘ በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ በሆነ አንድ ጥናት ላይ የኢትዮጵያ የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር እስከ 2030 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር እስከ 40% እንደሚሄድ ያብራራል።ይህ እንግዲህ የአገልግሎት ዘርፉ እንጂ በርካታ ሰው የሚቀጥር ኢንዱስትሪ የሌላት አገር አሁንም መጪውን የከፋ ያደርገዋል። ይህ ማለት ደግሞ አንዳችም የረባ የድህነት ቅነሳ ስልትም ሆነ ፖሊሲ የሌለው ይልቁንም የአገሪቱን ሀብት ባብዛኛው ስልጣኑን ለማስጠበቅ የምታትር አምባገነን ህወሓት በስልጣን ላይ መኖሩ የችግሩ ዋና ምንጭ ሆኖ ይታያል።
በመጀመርያ ደረጃ ለጎዳና ተዳዳሪነት የሚዳረጉት ሕፃናት አንዱ ምክንያት የስርዓቱ አምባገነናዊ ፖሊሲ ውስጥ አንዱ ከእየቦታው በግድ የሚፈናቀሉ ነዋሪዎች ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል።በአዲስ አበባ ብቻ በርካታ ሰው በግድ መሬቱን እንዲለቅ እየተደረገ ልጆቹን ለጎዳና ተዳርገዋል።ይህ እንግዲህ ከከተሞች አጎራባች ወረዳዎች ያለውን ሁኔታ ሁሉ ይጨምራል።
ሌላው እና ዋናው የችግሩ መነሻ የድህነት መጠን መጨመር ነው።ኢህአዴግ/ህወሓት ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች የውሸት ቁጥር እየሰጠ አገሪቱ አድጋለች ድህነት ቀንሷል ይበል እንጂ በመሬት ያለው እውነታ ግን የተለየ ነው።ድህነት ለመቀነስ የተቀመጠ ስልትም ሆነ ባለሙያ በሌለበት ጥቂት የስርዓቱ ታዛዦች ብቻ እንደፈለጉ በሀብት ማማ ላይ በምንጠላጠሉባት አገር ውስጥ አብዛኛው ሕዝብ የበይ ተመልካች ሆኗል።ከእዚህ ሁሉ ግን አንዳንድ ሪፖርቶች ከመውጣታቸው በፊት በመንግስት ለይስሙላ የሚሰጡት  የማታለያ ዜናዎች የበለጠ የሚያሳዝኑ ናቸው። 
ሰሞኑን የፋና ድረ ገፅ የጎዳና ተዳዳሪዎች በሹፍርና፣በኤሌክትሪክ ሙያ አሰለጠንኩ ብሎ ለፎቶ እና ለፕሮፓጋንዳ የሚጠቀምበት መንገድ አሳዛኝነቱን ስንመለከት ምን ያህል በችግሩ ሰለባ ወገኖች ላይ እየተቀለደ መሆኑን ያሳያል።በመጀመርያ ደረጃ የጎዳና ተዳዳሪዎች ችግር የመሰልጠን እና ያለመሰልጠን ብቻ አይደለም።ችግሩ ከአገሪቱ ፖለቲካዊ ስር የሰደደ ችግር እና የተሳሳተ ፖሊሲ የመጣም ጭምር ነው። ሁለተኛ መንግስት ስጋት ባደረበት ጊዜ ሁሉ እየተነሳ የጎዳና ተዳዳሪዎች ማጎር እና ስልጠና እየሰጠሁ ነው ማለት በእራሱ ስልት የጎደለው ድህነትን የሚያህል ነገር በሺ የሚቆጠሩ ወጣቶችን ፎቶ በማሳየት የችግሩ ምንጭ እራሱ መንግስት እና ፖሊሲው መሆኑን ለመሸፋፈን የሚደረገው ሙከራ አካል ነው።ይህ ደግሞ የትም የማያደርስ እና ችግሩ ገዝፎ የሚመጣ ቀን ማጣፍያው እንደሚያጥር ለማወቅ ብዙም ምርምር አይፈልግም። ከሁሉም በላይ ደግሞ የአገሪቱ ገንዘብ በአራቱም ማዕዘናት በሙሰኛ ባለስልጣናት እየተዘረፈ፣ህወሓት ለድርጅቶቹ በዓል ማክበርያ ፣በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ለመሰለል፣ ኢሳትን እና ሌሎች ወደ አገርቤት የሚተላለፉ ሚድያዎችን ለማፈን ወዘተ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ እየከሰከሰ  መሆኑን ማሰብ እና በአንፃሩ የጎዳና ተዳዳሪዎች ከግማሽ ሚልዮን በላይ መናራቸውን መመልከት በእራሱ ኢትዮጵያ ትውልዷን እያጣች ያለችው እና ለእዚህም ዋና ምክንያቱ የመጥፎ አስተዳደር ሰለባነት መሆኑ በግልፅ ይታያል።አሁን የሚታየው እውነታ ይሄው ነው።ኢትዮጵያ በጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናቷ ከአለም ቀደምቶቹ ውስጥ ገብታለች።
ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com 
የካቲት 29/2008 ዓም (ማርች 8/2016)

No comments:

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...