ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, March 19, 2016

በሳምንቱ ውስጥ የነበሩ አጫጭር ዜናዎች (ጉዳያችን)
አቶ ኃይለማርያም የዓለም ሕዝብ የምግብ ዕርዳታ እንዲለግስ በድጋሚ በይፋ ተማፀኑ 

 ኢትዮጵያ ትናንት ዓርብ ለዓለም ማኅበረሰብ የምግብ እርዳታ እንዲሰጣት በድጋሚ ተማፀነች። ተማፅኖውን ያቀርቡት አቶ ሃይለማርያም ሲሆኑ የምግብ እርዳታው በአፋጣኝ ካልደረሰ አደጋ እንደሚከተል ገልጠዋል። አቶ ኃይለማርያም በምግብ እራሳችንን ችለናል ባሉ በአንድ ዓመት ሳይሞላ ነው ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብን ለሁለተኛ ጊዜ የተማፀኑት።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በረሃብ ለተጎዱ ወገኖቻቸው መርዳት ቀጥለዋል 

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮያውያን በረሃብ ለተጎዱ ወገኖች መርዳታቸውን ቀጥለዋል ባለፈው ሳምንት አሜሪካ የሚገኘው በአርቲስት ታማኝ እና የሚመራው ''ግሎባል አልያንስ'' (አለማቀፋዊ ህብረት ወይንም ቃል ኪዳን ለኢትዮጵያ) የተሰኘው ድርጅት ከአንድ ሚልዮን ብር በላይ አሰባስቦ ለ'ዎርልድ ቪዥን' አስረክቧል።በአውሮፓ እና ሌሎች አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም በማሰባሰብ ላይ ናቸው።

አቶ አርከበ 'ብሉምበርግ' ቀርበው ምን አሉ?

 አቶ አርከበ በእዚህ ሳምንት ለብሉምበርግ ''በምግብ እራሳችንን ችለናል የኦሮምያው ግጭት ምጣኔ ሃብቱን አልጎዳም'' ብለዋል።እዚህ ላይ የቡና አምራች አካባቢ አመፅ ተነስቶ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ቡና ላይ የተመሰረተ ሆኖ ሳለ እንዴት ምጣኔ ሃብቱ አልተጎዳም? ብላ የብሉምበርግ ጋዜጠኛ መጠየቅ ነበረባት።አቶ አርከበ በቃለ ምልልሳቸው ላይ በኢትዮጵያ የሚነሱ ፀረ መንግስት እንቅስቃሴዎች በሙሉ ወጣቱ ሥራ ስላጣ ነው፣ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ እንከፍታለን የመሳሰሉትን ይናገሩ እንጂ አገሪቱ ግልፅ የሆነ የምጣኔ ሀብት አቅጣጫ እንደሌላት ለጋዜጠኞቹ ግልፅ ሆኗል።ለእዚህም ነው የብሉምበርግ ጋዜጠኛ ''ወዴት እየሄዳችሁ ነው ምንድነው ቀዳሚ ትኩረታችሁ?''የሚል ጥያቄ የጠየቀው።አቶ አርከበ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ እንደሚመጣ እና በቅርቡ ከዓለም 10ሩ በሕዝብ ብዛት ቀዳሚ አገራት ውስጥ እንደምትገባ ገልፀው ለመፍትሄነት ያስቀመጡት ግን ግልፅነት የሌለው የአገሪቱን አቅም ያላመላከተ እና ወደፊት ኢንቨስተር ይመጣል የሚል መልስ ነበር።በመሰረቱ አቶ አርከበ በቃለ መጠየቃቸው ላይ የምጣኔ ሀብት ቃላት (terminology) አጠቃቀም ላይ ከሌሎች ባለስልጣናት የተሻለ የእንግሊዝኛ አጠቃቀም ይታይባቸዋል።

''ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ውጭ ታሳድራለች'' ግብፅ በድጋሚ 'የኢትዮጵያን የአየር ክልል በሳተላይት ኢትየጠቆጣጠርኩ ነው 'አለች ህወሓት በዝምታ አበረታቷል። 

- ግብፅ የኢትዮጵያን የአባይ ግድብ ላይ ለ24 ሰዓታት ለመከታተል የቀድሞውን ሳተላይት በሌላ ልመቀየሯን በግልፅ ተናግራለች።የእዚህ አይነት ግልፅ ንግግሮች በግብፅ ባለስልጣናት ሲነገር ኢትዮጵያ እንደ ሉዓላዊ አገር ምላሽ አልሰጠችም።ይህ አንዱ የህወሓት አሳፋሪ ተግባሩ አካል ነው።የእዚህ አይነት ተግባር በግልፅ መነገራቸው ለኢትዮጵያ ያላቸውን ንቀት ለማሳየት ካልሆነ በቀር የአንድ ሉዓላዊት አገርን መሬት ከሳተላይት አያለሁ የሚሉ ንግግሮች በሚንስትር ደረጃ ሲነገሩ የተለመዱ አይደለም።በድብቅ አገራት ቢያደርጉትም በአደባባይ መናገር ግን ንትርክ ስለሚያስከትል አያደርጉትም የህወሓት ኢትዮጵያ ግን  በእዚህ ጉዳይ ላይ የግብፁን አምባሳደር ጠርታ ማብራርያም አጠይቅም።የመንደር አስተሳሰብ ካለህ ስለ ትልቁ አገር ማሰብ ታቆማለህ።ህወሓት ከአገር ይልቅ ለመንደር የሚጨነቅ ድርጅት ስለሆነ የኢትዮጵያን ጉዳይ እንዲህ ያጎሳቁለዋል።

''የኢትዮጵያው ደግ ክርስቲያን ንጉስ  እስልምናን ባይከላከል ኖሮ እስልምና ዛሬ አይኖርም ነበር'' የግብፁ የእስልምና እምነት አባት 

- ''በመጀመርያ እስልምናን ከለላ የሰጠልን ክርስትና ነው።የኢትዮጵያው ደግ ክርስቲያን ንጉስ ባይኖር ኖሮ እስልምና በአሁኑ ሰዓት ላይኖር ይችል ነበር'' ይህንን የተናገሩት የግብፅ የሃይማኖት አባት ለጀርመን ምክርቤት በእዚህ ሳምንት ነው። የሃይማኖት አባቱ እንደገለፁት ደጉ የአብሲንያ ንጉስ የመሐመድ ቤተሰቦችን መንከባከቡ እና በሰላም ማቆየቱ ዛሬ እስልምና ሳይጠፋ እንዲኖር አድርጎታል በማለት በማስረጃ አብራርተዋል።የግብፅ አልሃራም ጋዜጣ ዘግቦታል።ይህ ታሪካዊ ንግግር ነው።በመጀመርያ ደረጃ ንጉሡ ክርስትናውን ጠብቆ መኖሩን እና ኢትዮያ በዓለም ታላላቅ ክስተቶች ላይ አሻራዋ መኖሩ የተገለፀበት ነው።

ኢማሙ ለጀርመን ምክርቤት ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 6/2008 ዓም ቀርበው ያሉት እንዲህ የሚል ነበር።''Christianity was the first to provide sanctuary for Islam; without Abyssinia and its Christian king who protected the first Muslims, Islam would have been destroyed in its cradle,” Grand al-Azhar Imam Sheikh Ahmed al-Tayeb

''እየሰመጠ ካለ መርከብ ራስን የማዳኛ ጊዜ አሁን ነው!'' የአርበኞች ግንቦት 7 ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ሲጠናቀቅ ያወጣው መግለጫ።

በእዚህ ሳምንት ሌላው በድረገፆች የወጣው ዜና የአርበኞች ግንቦት 7 ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ በመጪዎቹ ሶስት ወራት የሚሰሩት ሥራ ላይ መወያይቱን እና ማፅደቁን ''ዘ-ሐበሻ'' ድረ-ገፅ ገልጧል።ድረ-ገፁ እንዳስታወቀው ስብስባው የሚከተሉትን  መልዕክቶች ለአባላቱና ደጋፊዎች፣ለመከላከያ ሰራዊት፣ለለህወሓት፣ ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደህዴግ እና የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች አባላት እና  ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተላልፏል። መልክቶቹም : -


1. ለአርበኞች ግንቦት 7 አባላትና ደጋፊዎች
ወሳኝ በሆነ የትግል ወቅት ላይ እንገኛለን፤ በዚህ ወቅት በትጥቅ ትግሉ በቀጥታ ተሰልፈው ያሉት አባሎቻችን፣ በአገር ውስጥ በሕዝባዊ እምቢተኝነት በመሳተፍ ላይ ያሉ አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን እና በውጭ አገራት የሚገኙ አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን ሁሉ በአንድ ልብና መንፈስ ህወሓትን ከስልጣን የማስወገድ ሥራ ላይ እንዲረባረቡ ሥራ አስፈፃሚው ጥሪ ያደርጋል።
2. ለአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለፓሊስና የደህንነት አባላት
ነገ ከሚወድቅ ሥርዓት ጎን ቆማችሁ ወገኖቻችሁን ማጥቃት ተው! የመሳሪያዎቻችሁ አፈሙዝ የሁላችንም ጠላት ወደሆነው አገዛዝ ይዙር! ከወያኔ በኋላ በሚመጣው ሥርዓት የመከላከያ ሠራዊትና ፓሊስ መበተን የለባቸውም ብለን እናምናለን፤ ይህ እንዲሆን ግን ዛሬ ከአምባገነን ሥርዓት ጎን ሳይሆን ከሕዝብ ጎን ቁሙ።
3. ለህወሓት፣ ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደህዴግ እና የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች አባላት
እየሰመጠ ካለ መርከብ ራሳችሁን አውጡ! አባል የሆናችሁባቸው ድርጅቶች ለአገራችን ብቻ ሳይሆን ለእናንተም በግል የሚበጁ አይደሉም። ቢቻል በግልጽ፤ ካልተቻለም በስውር ድርጅቶቻችሁን በማዳከም የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግልን አግዙ።
4. በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲፈጠር ለሚታገሉ የፓለቲካና ሲቪክ ማኅበራት
በጋራ የምንቆምበት ወቅት አሁን ነው። ዛሬ የምናደርጋቸው ትብብሮች የረዥም ጊዜ ውጤት ያላቸው መሆኑን ተገንዝበን ኃይላችንን እንድናስተባብር ጥሪ እናደርጋለን።
5. ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ
ጥያቄዎቻችን አካባቢ ተኮር ሊሆኑ ይችላሉ፤ ግባችን ግን የጋራ ነው። ከህወሓት አምባገነን አገዛዝ ነፃ የወጣች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትኖረን ሁላችንም በአንድነት እንድንቆም የአርበኞች ግንቦት 7 ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጥሪ ያደርጋል። 

የሚሉ ነበሩ።

ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com 

መጋቢት 10/2008 ዓም  (March 19/2016) 

No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...