አዲስ አበባ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ የካቲት 25/2008 ዓም ድንገተኛ ስብሰባ ጠርቷል።ሐራ ዘተዋሕዶ የተሰኘው በቤተ ክርስቲያኒቱ ዙርያ መረጃ የሚሰጠው ድረ-ገፅ እንደገለፀው ስብሰባው የተጠራው በቋሚ ሲኖዶስ ሲሆን አጀንዳዎቹ ውስጥ:
- ስለ ሰላም እና ስለ ተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት፤
- በድርቁ ምክንያት ለተጎዱት ወገኖች እየተደረገ ስላለው ርዳታና ጸሎተ ምሕላ፤
- ማዕከላዊነትን ስላልጠበቁ አሠራሮችና ስላስከተሏቸው ችግሮች፤
- ከልዩ ጽ/ቤት ስለሚወጡ ደብዳቤዎችና መጻጻፎች በተመለከተ፤
- የፓትርያርኩን የውጭ ጉዞዎች በተመለከተ፤
- በፓትርያርኩና በማኅበረ ቅዱሳን ውዝግብ፣
- በዐቢይ ጾም የጸሎተ ምሕላ ጉዳይ
የሚሉት እንደሚጠቀሱ ድረ-ገፁ ያብራራል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከፓትርያርኩ በበለጠ ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያኒቱ አካል ከመንፈስ ቅዱስ በታች ቅዱስ ሲኖዶስ መሆኑ ይታወቃል።ዛሬ አቡነ ማትያስ ስብሰባ እንደሚደረግ አለማወቃቸው እና በመጪው ሰኞ ስለምጀመረው አቢይ ፆም መግለጫ ሰጥተው እንደጨረሱ ተነስተው ለመውጣት ሲሉ ተመልሰው እንዲቀመጡ እና ሲኖዶሱ ድንገተኛ ስብሰባ እንደሚያደርግ በዋና ሥራ አስኪያጁ አቡነ ማትያስ እንደተነገራቸው ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከ1984 ዓም ጅምሮ ፓትርያሪክ አቡነ መርቆርዮስ እና ሌሎች ብፁዓን አባቶች ከአገራቸው ተሰደው እንደሚገኙ እና በአገር ቤት እና በውጭ ''ሲኖዶስ'' በሚል አባቶች መለያየታቸው ይታወቃል። ሆኖም ግን ይህ ልዩነት ሃይማኖታዊ ወይንም ዶግማዊ ሳይሆን የሥርዓት መሆኑን እና በአገር ቤት ያለው የአምባገነን ስርዓት ለውጥ ከመጣ ቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነቷን እንደምትጠብቅ የብዙዎች ተስፋ ነው።
አቡነ መርቆርዮስ ከአገር ሲሰደዱ መንበረ ጵጵስናውን የያዙት እና ከእዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አቡነ ጳውሎስ በዘመናቸው በአባቶች መካከል ፍሬ ያፈራ የአንድነት ሥራ ሳይሰራ መኖሩ እና ይብሱንም ቤተ ክርስቲያኒቱ በዘመኗ አይታ የማታውቀው የለየለት የሙስና፣የገንዘብ ብክነት እና ጎጣዊ አሰራሮች ሰፍነው ቆይተዋል።አቡነ ጳውሎስን የተኩት አቡነ ማትያስ በመንበራቸው በቆዩባቸው ሁለት አመታት ውስጥ ምንም አይነት የአሰራር መሻሻል ሳይታይ የቆየ ከመሆኑም በላይ ይብሱንም አቡነ ማትያስ የነገሮች አያያዝ አቅማቸው እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ግንኙነት እንዲሁም በተለያየ ጊዜ የሚፈጥሯቸው አዳዲስ የግጭት ሜዳዎች ብዙዎችን እጅግ ሲያሳዝን የከረመ ጉዳይ ነው።
በሌላ በኩል ከአራት ቀናት በፊት አቡነ ማትያስ ከካቶሊክ ፓፓ ፍራንሲስ ጋር በቫቲካን ተገናኝተው መምከራቸው ይታወሳል።የዛሬው የቅዱስ ሲኖዶስ ድንገተኛ የስብሰባ አጀንዳ ውስጥ አንዱ የፓትራሪኩን የውጭ ጉዞዎች የሚፈትሽ እንደሚሆን ተሰምቷል።
ባለፈ ሰኞ የካቲት 21/2008 ዓም አቡነ ማትያስ እና ፖፕ ፍራንሲስ በባቲካን ሲገናኙ
ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ ውስጥ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሕዝቡን አንድነት እና ሰላም በመጠበቅ ረገድ የተጫወተችው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው።በአገር ውስጥ የሚነሱ ማናቸውም ከቁጥጥር ውጭ የሚሆኑ እና አገሪቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ እንደ ትልቅ ጉድለት የሚጠቀሰው አንድ ማዕከላዊ፣ገለልተኛ እና ተአማኒ አካል አለመኖር ነው።በተለይ ባለፉት 24 ዓመታት እንደ አገር ካጣናቸው እሴቶች አንዱ እና ትልቁ ይህ መሆኑ ይታወቃል።ይህንን ክፍተት ለመሙላት ደግሞ በቤተ ክርስቲያኒቱ መንበር ላይ የሚቀመጡ አባቶች ሚና ትልቅ ድርሻ አለው።
ይህ እንዳይሆን ግን የቤተ ክርስቲያን አሰራር በሙሰኞች እና በስልጣን ላይ ባለው ስርዓት ጣልቃ ገብነት ቤተ ክርስቲያን የእራሷን የመልካም ስነ-ምግባር እና መንፈሳዊ ስርዓት የመምራት አቅም በየጊዜው እንዲዳከም እየተደረገ ነው።ይህ ሁኔታ ዞሮ ዞሮ የሚጎዳው እንደ አገር ኢትዮጵያን መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው።የኢትዮጵይ ቤተ ክርስቲያን ግን ኢትዮጵያ በ18 ኛው ክ/ዘመን ተነስቶ እስከ 19ኛው አጋማሽ ድረስ የዘለቀው እና የአገሪቱን አንድነት በተፈታተነው ''የዘመነ መሳፍንት'' ወቅትም ብቸኛ የህዝብ አገናኝ ድልድይ እና ገላጋይ ሆና ቆይታለች።ለእዚህ ነው ኢትዮጵያን እንደ አገር ለማጥፋት የሚነሱ ኃይሎች ሁሉ በመጀመርያ ኢላማቸውን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የሚያደርጉት።
ጉዳያችን GUDAYACHN
የካቲት 25/2008 ዓም
No comments:
Post a Comment