ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, March 12, 2016

''ኩዳድ '' የአማርኛ ታሪክ ቀመስ ልብ ወለድ መፅሐፍ በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ ተመረቀ

የኩዳድ የፊት ገፅ 

በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አርአያነት ያለው ተግባር እየፈፀሙ ነው። በአራት ዓመታት ውስጥ ሁለት የአማርኛ መፃህፍት፣አንድ ዳጎስ ያለ የአማርኛ ኖርዌጅኛ መዝገበ ቃላት እና ሰዋሰው (grammar)  ታትመው ገበያ ላይ ውለዋል። ይህ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ትልቅ አርአያነት ያለው ተግባር ነው።
ወ/ሮ ዙፋን የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በኖርዌይ ሰብሳቢ የመክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ 

ዛሬ መጋቢት 3/2008 ዓም ደግሞ በደራሲ አቶ ማተቤ  መለሰ የተፃፈ ''ኩዳድ'' የተሰኘ ታሪክ ቀመስ ልብ ወለድ መፅሐፍ የምረቃ ስነ-ስርዓት ተከናውኗል።

ይህ 433 ገፆች የያዘ ታሪክ ቀመስ ልብ ወለድ  መፅሐፍ ምረቃ መርሃ ግብር ላይ በርካታ በኦስሎ እና አካባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የታደሙበት ሲሆን የመክፈቻ ስነ-ስርዓቱን የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ በኖርዌይ ሰብሳቢ ወ/ሮ ዙፋን ለምረቃ የተዘጋጀውን ሪባን በመቁረጥ መፅሐፉ መመረቁን አብስረዋል።በመቀጠልም መፅሐፉ በሶስት ምሁራን ተገምግሟል።በመፅሐፍ ግምገማው ላይ በኦስሎ ዩንቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ተክሉ አባተ፣ ዶ/ር ሙሉ ዓለም አዳም እና አቶ ይበልጣል ጋሹ የተሳተፉ ሲሆን ሶስቱም ጥልቅ የሆነ ዕይታቸውን ለታዳሚው  በየተራ አቅርበዋል።
ደራሲው አቶ ማተቤ መለሰ  ከልጆቻቸው ጋር የኬክ ቆረሳ ስነ-ስርዓት ላይ 


ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ተክሉ አባተ ከመፅሐፉ የፊት ገፅ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ የታሪኩን ፍሰት እና ተያያዥነት ከመፅሐፉ እያጣቀሱ እና የገፀ ባህርያቱን የገሃዱ ዓለም ነባራዊ ነፀብራቅ መሆን ላይ አፅንኦት ሰጥተው ያብራሩ ሲሆን ዶ/ር ሙሉ ዓለም በበኩላቸው ከደራሲው ጥረት እና ትጋት ተነስተው እስከ ቃላት አጠቃቀም ጥልቅ ግምገማቸውን አቅርበዋል።አቶ ይበልጣል ጋሹ በሌላ በኩል በመፅሐፉ ውስጥ የተጠቀሱት ታሪኮች ምን ያህል ከቦታው ባህላዊ መስተጋብር ጋር የተያያዘ መሆኑን እና የሚያካልላቸው ቦታዎች ከጎጃም እስከ ኤርትራ ከዝያም እስከ ሱማሌ ምድር ድረስ  መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በኖርዌይ ሰብሳቢ በማኅበረሰቡ ስም ለደራሲው ስጦታ ሲያበረክቱ 

ከመፅሐፉ ግምገማ በኃላ የሻይ እረፍት ተደርጎ ከታዳሚው ለገምጋሚዎች እና ለደራሲው አቶ ማተቤ መለሰ ጥያቄዎች፣አስተያየቶች እና የመልካም ምኞት መግለጫዎች ተሰምተዋል።ለቀረቡት ጥያቄዎች ደራሲው እና የመፅሐፉ ገምጋሚ ምሁራን በቂ መልስ የሰጡ ሲሆን በመጨረሻ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በኖርዌይ ለደራሲው ውድ ጊዜያቸውን ሰውተው በስደት አገር ለአገራቸው ይህንን በማበርከታቸው አርአያ ሆነውናል በሚል ልዩ ስጦታ አበርክቶላቸዋል።በመጨረሻም  ደራሲው ከአራት ልጆቻቸው ጋር በመሆን የኬክ መቁረስ ስነ-ስርዓት የተካሄደ ሲሆን የደራሲው አቶ ማተቤ መለሰ  ልጆች በጋር ይህንን የምረቃ ዝግጅት ላዘጋጁ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በኖርዌይ አባላት የምስጋና የአበባ ስጦታ አበርክተዋል።

በመፅሐፉ የፊት ገፅ ላይ እንደሚነበበው መፅሐፉን ለማዘዝም ሆነ ደራሲውን ለማግኘት የሚከተሉትን አድራሻዎች መጠቀም ይችላሉ።

ተንቀሳቃሽ ስልክ = (0047) 99850153
ኢ-ሜል = matebemelese@yahoo.com  


ጉዳያችን GUDAYACHN 
www.gudayachn.com
መጋቢት 3/2008 ዓም 

No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...