ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, March 25, 2016

''አያያዙን አይቶ ጭብጦውን ቀማው'' የሃይማኖት ሰው ባርነትን እና ግፍን አይሸከምም ! ሃይማኖት ፈሪ አያደርግም ደፋር እንጂ! (የጉዳያችን ማስታወሻ)

በ1928 ዓም ሃይማኖት ሰንቀው ዕውነት ይዘው ለአገራቸው የዘመቱ ኢትዮጵያውያን 
Photo :-East Africa campaign 1940, Bisheshwar Prasad

እውነት የፍልስፍና ጉዳይ አይደለም።እውነት የህሊና ዳኝነት እና የሃይማኖት ፍሬ ነው።ሸፍጥ በአንፃሩ የአድር ባይነት እና እራስን ዝቅ አድርጎ የማየት የተንሸዋረረ አስተሳሰብ ውጤት ነው።ኢትዮጵያውያን ቀደም ባሉ ዘመናት የምንታወቅበት አንዱ መለያ ግፍ እና ባርነት ለመሸከም  ምንም አይነት የሽንገላ ቃላት የማይደልሉን መሆናችን ነበር።ለእዚህ ደግሞ አንዱ እና ዋነኛው ምክንያት የሕይወት መመርያ ፍልስፍናችን በሃይማኖት የታሸ እና ፍትህን ያስቀደመ በመሆኑ ነው።

ዓለም በሕግ ስርዓት ሳይዳኝ ኢትዮጵያውያን ''በላ ልበልሃ'' ብለው ሹሙ ፊት ቀርበው በአደባባይ ፍርዱን ሕዝብ እየተመለከተ ይሟገታሉ።ፍትህም ከሹሙ ይቀበላሉ።በፍትህ ያልተስማማ ይሞግታል።ፍርዱ አድሏዊ ነው ካለ ጠብመንዣውን (ጠበንጃውን) አልያም ጦሩን ሰብቆ ጋሻውን ወድሮ ይሸፍታል።ሸፍቶ ሳለ ሹም ቢቀየር ፍትህ ቢሻሻል ከአገሬው ታርቆ፣ ይቅር ተባብሎ ወደ ሰላማዊው ኑሮ ይመለሳል። ከእዚህ ውጭ ባርነት እና ግፍን አይሸከምም።ኢትዮጵያዊው የሃይማኖት ሰው እንዲህ ነው።ኢትዮጵያም ነፃነቷን ጠብቃ የኖረቸው ለእውነት የቆሙ የሃይማኖት ሰዎች መኖርያ በመሆኗ ነው።

የሃይማኖት ሰው ፍርሃት አያውቅም።እውነትን ይዤ የማልችለው የሚያቅተኝ ምድራዊ ነገር አለ ብሎ ፈፅሞ አያስብም።ፍርሃት፣ ሐሰትን እና ሸፍጥን በውስጣቸው ይዘው ለሚሄዱ እንጂ ለሃይማኖት ሰው ፈፅሞ ፍርሃት አያሰጋውም።የእውነት መግነጢሳዊ ኃይል በእራሱ እንደ እሳተ ገሞራ ፈንቅሎ ድል የማድረግ ኃይል ለሃይማኖት ሰው የተሰጠ ፀጋ ነው። 

ኢትዮጵያ ዛሬ የመንደራቸውን ሰው 'ቅዱስ' ከመንደራቸው ያልተወለደውን 'እርኩስ' የሚያደርጉ በዘረኝነት፣በሌብነት፣በሙስና፣ሰውን በመግደል እና በማሰር የሥልጣናቸውን መንበር ለመጠበቅ በሚውተረተረው ህወሓት እጅ ወድቃ እየማቀቀች ነው። የሃይማኖት ሰው ምኑንም ያህል ትሕትና ቢያሳይ፣ ፍቅር ቢመግብ እና ከአድልዎ ፀድቶ የሸፍጥ እና የባርነት ቀንበራቸውን  ለማሳለፍ ቢሞክር አሁን በስልጣን ላያ ያለው ቡድን እና  አቀንቃኞች ሁሉንም በጥላቻ አይን እየነደፉ ወደ ባሰ የመረረ ጥላቻ በጎ ህሊናን እንደሚቀይሩ የሚያውቀው የደረሰበት ብቻ ነው።ያልደረሰበት አይረዳውም።

ሃይማኖት ያስታግሳል።ሃይማኖት በጎ ህሊናን ስለሚያጎናፅፍ ነገሮችን በቀና ለማየት ጊዜ ይሰጣል።ሃይማኖት የሚሰራውን ግፍ እየተመለከቱ ግፍ ሰሪ ወደ ህሊናው እንዲመለስ መካሪ ዘካሪ ያደርጋል።ግፍ የሚሰራው ግን ምክርን የማይሰማ 'ደረቴ ይቅላ ሆዴ ይሙላ' ብሎ በጥጋቡ ከቀጠለ ሃይማኖት በሁለት ሰይፍ ስላ በታላቅ ኃይል  ለፍትህ  ሥራ ታስነሳለች።

ሃይማኖት ካለምንም ለውጥ አገርን ወደ ባሰ ማጥ እየከተተ እና ህዝብን እያስረገጠ ፈሪ አያደርግም።ከሁሉም ይልቅ ኢትዮጵያዊነት ደግሞ ፈፅሞ በእዚህ አይነቱ መንገድ አይገለጥም። በግፍ እና በዘረኝነት ስትገፋ ኖረህ ከመሞት የበለጠ ሌላ ሞት የለም።የሃይማኖት ሰው ከሆንክ ፍትሕን ጥራት! በግፍ እና በዘረኝነት እንዲሁም በሙስና እና ኢትዮጵያን በመክዳት ሕይወትህን ያጎሳቆሉትን፣ ይህም ሳያንሳቸው በንቀት ለተመለከቱህ እና አሁንም ይህም ሳያረካቸው ሊረግጡህ ተረከዛቸውን ላነሱብህ የማትቀመስ መሆንህን ማሳየት ኢትዮጵያዊ ግዴታህ ነው። የሃይማኖት ሰው ባርነትን እና ግፍን አይሸከምም! ከአባቶቻችንም ይህንን አልተማርንም።'አያያዙን አይቶ ጭብጦውን ቀማው' እንዲል ግፍን እና ድብቁን እና ግልፁን ዘረኝነት በግልፅ ተጋፍጠህ አገርህን ነፃ ካላወጣህ የአንተን ማንነት ጭብጦህን እሰከ ዘላለሙ አታገኘውም። በንቀት ለተመለከቱህ ሁሉ ከእዚህ በፊት በቃል እንዳስተማርካቸው አሁን ደግሞ በተግባር አስተማሪያቸው ሁን።ለዕውነት እና ለአገር በክብር መቆም ከውርደት ሞት ያድናልና።ሃይማኖት ፈሪ አያደርግም ደፋር እንጂ! አንተ በእራስህ ለእራስህ ወስን! ስራህን በቅደም ተከተል አስቀምጥ! በፍጥነት ወደ ተግባር ግባ!



ጉዳያችን GUDAYACHN

 www.gudayachn.com

መጋቢት 16/2008 ዓም 

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...