ዛሬ ወልቃይት ጠገዴ ወረዳ ቀራቅር የምትባል ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ ነበር።በዛሬው ዕለት ብቻ ከ2000 ሕዝብ በላይ ሰልፍ ወጥቷል።የ16 ዓመት ታዳጊ በጥየት ተገድሏል።የህወሓት ደህንነት የሱዳን ታርጋ በለጠፉ መኪናዎች ይንቀሳቀሳል።
===========================================
የአሜሪካ ድምፅ ራድዮ የአማርኛው አገልግሎት ዛሬ መጋቢት 13/2008 ዓም ከወልቃይት ጠገዴ በቀጥታ በስልክ ያነጋገራቸው እና በሰልፉ የተሳተፉ ነዋሪ እንደተናገሩት:- ''ሰልፉ የተደረገው ዳንሻ ከተማ ላይ አማራ ነን ብለው በጠየቁ ወጣቶች ላይ የግድያ እና እስራት ማዋከብ ተግባር ስለነበር ይህንን በመቃወም መንገድ በመዝጋት እና በመሳሰለው ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ አድርገናል'' ብለዋል።
በዛሬው ሰልፍ ስንት ሕዝብ ተገኘ? ተብሎ ለእኚሁ ነዋሪ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ''በቀራቅር ከተማ ብቻ ዛሬ ተማሪዎች ወደ 800 ተገኝተዋል። ከሕዝቡ ገበሬው ወደ 1200 ሕዝብ ባጠቃላይ በግምት ወደ 2000 ሕዝብ ተሳትፏል ብለን እንገምታለን'' ብለዋል።
ቀሪው ቃለ ምልልስ በቀጥታ እንዲህ ቀጥሏል:-
ቪኦኤ :- ተሰልፋችሁ ወዴት ሄዳችሁ?
''ተሰልፈን ከተማውን ሁለት ጊዜ ዞረነዋል።በኃላ ወደ አስተዳደሩ ቢሮ ነው የሄድነው እሳቸው የዳንሻ መንገድ ስለተዘጋ ከህዝብ ጋር ለመደራደር ሄደዋል ተባልን።ቢሮ ይወከል አይወከል አይታወቅም አንዱ ሰብስቦን ነበር። እኛ ግን እሱን ማዳመጥ አልፈለግንም።ይሄው ሰው ግን ሰልፍ መውጣታችሁ ትክክል አይደለም።የዳንሻን ሕዝብ መወከል አትችሉም፣አማራ ነኝ ለሚል ወገን ብላችሁ መደገፍ አትችሉም የሚል መልስ ነው የሰጠን። እኛም በመልሱ ስላልተደሰትን ሌላ ስሜት ውስጥ እንዳንገባ ብለን ጥለነው ነው የሄድነው ሰውዬው እዚያው ብቻቸውን ነው የቀሩት ''
ቪኦኤ:- የታሰሩ እና የተገደሉ አሉ ብለው ነበር? የታሰሩ የሚያውቁት አለ?
''የታሰሩ ብዙ ናቸው። ስማቸውን መዘርዘር አይቻልም ብዙ ናቸው።''
ቪኦኤ:- ስንት ይሆናሉ?
''አሁን ጧት ያለን መረጃ 70 አካባቢ ደርሰዋል ተብሎ ነበር አሁን ግን የቀሩት በረሃ ይብላን ብለው ወደ በረሃ ወርደዋል።አሁን የቀሩት ወደ 40 ይሆናሉ።ሌላው ግን በርካቶች ሰዎች ሚሊሻ ታጣቂ ሁሉ ወገናችንን አንጨፈጭፍም ብለው ወደ በረሃ መውረዳቸውን እየደወሉ እየነገሩን ነው ያሉት''
ቪኦኤ:- የተገደሉት ይታወቃሉ?
''የተገደሉት አይታወቁም ሁለት በረሃ ተገለው ተገኝተዋል።አንዱ አድራሻው ጠፍቶብናል።ሊላይ ብርሃኔ የሚባል ልጅ ታፍኖ ጠፍቶብናል። አድራሻው አይታወቅም።ሁለቱ ግን በእኛ አካባቢ ሞተው ተገኝተዋል።''
ቪኦኤ:- አስከሬናቸውን አይታችኃል?
''አዎን አይተናል ግን ከየት ይምጡ ከየት አይታወቅም ሞተው አይተናቸዋል። አንዱ ግን ሊላይ ብርሃኔ ይሆናል ብለን ገምተናል።''
ቪኦኤ:- እንዴ እናንተ አቶ የላይን አታውቁትም?
''እናውቀዋለን ግን አስከሬኑ መልኩን ቀይሯል''
በመቀጠል ሌላ ተጠያቂ ቀረቡ እና ስለሁኔታው እንዲህ አሉ:-
''ከጎንደር ወደ ሁመራ የሚወስደው መንገድ ተዘግቷል።ከዳንሻ ወደ 30 ሰው አማራ ነን የሚሉ ታስረዋል።አንድ የ16 ዓመት ልጅ ትናንት ማታ በጥይት ገለውታል። ሌላይ ብርሃኔን ከጎንደር ይዘውት እስከ ሳንጃ ድረስ ይዘው ሲያመጡት ታይቷል ቡሬ የሚባል ቦታ ነው የያዙት ከእዛ አልታየም እሱንም ገድለውታል።''
ቪኦኤ:- የያዘው ማነው?
''የትግራይ ደህንነት''
ቪኦኤ:- እንዴት አወቃችሁ የትግራይ ደህንነት መሆናቸውን?
''እዚህ ሁለት ታርጋ የሌላቸው እና የሱዳን ታርጋ የለጠፈ መኪናዎች እዚህ ቆመው ሰንብተዋል።እነርሱ ናቸው የወሰዱት''
ቪኦኤ:- የመንግስት ደህንነት መሆናቸውን እንዴት አወቃችሁ?
''ይታወቃል እናውቃለን......ብዙ ሰው በረሃ ግብቷል።''
ቪኦኤ:- በረሃ ገብቶ ምን ያደርጋል?
''በረሃ ገብቶ አማራጭ መፈለግ''
ቪኦኤ:- አማራጭ ምን ይደረጋል?
''በቦታው ሰላም ከሌለ በዱር ሆኖ መታገል ይቻላል ''
ቪኦኤ:- አሁን ሰሮቃ ከተማ በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለች እርስዎ ያሉባት?
''ዝግ ነው መኪና አይንቀሳቀስም ''
ቪኦኤ :- ለምንድነው መኪና የቆመው?
''አድማ ነው አድማ''
ቪኦኤ:- መኪናዎቹ ናቸው አድማ የመቱት?
''ህዝቡ ነው የአማራ ጥያቄ ይመለስ በሚል ነው''
ቪኦኤ:- የመንግስት አካላት ናቸው መኪና እንዳይተላለፍ ያደረጉት?
''ህዝቡ ነው የመንግስት አካላት የሉም።ህዝቡ ነው መንገዱን እንጨት እና ድንጋይ ዘግቶ አማራ እየተደበደበ ነው መብታችንን ብሎ''
ቪኦኤ:- ታድያ እስካሁን መልስ የሰጣችሁ የለም?
''መልስ ከፌድራልም ከዞንም የለም አራተኛ ቀናችን ነው''
ቪኦኤ:- የሊላይ ብርሃኔ ጉዳይስ እየተከታተላችሁ ነው?
''ወንድምዬው ጧት መጥቷል አይቼዋለሁ።ወንድሜ ሞቷል ገለውታል ብሎ ሲያለቅስ አይቼዋለሁ።''
በመጨረሻም ቪኦኤ ከህወሓት በኩል ምላሽ ለማግኘት ጥረት ማድረጉን ግን ምላሽ ማግኘት አለመቻሉን አክሎ ገልጧል።ከእዚህ በተጨማሪ የአዲስ አበባ ሕዝብ በውሃ እጦት መቸገሩን እና በርካታ የከተማዋ ክፍሎች እሰከ 20 ቀን ድረስ ውሃ እንደማያዩ ነዋሪዎች አማረው ሲናገሩ አሰምቷል።
ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com
መጋቢት 14/2008 ዓም
No comments:
Post a Comment