ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, March 27, 2014

በመንግስት የሚደገፈው የጎሳ ፖለቲካ እንደ 'አሜባ' እየተስፋፋ ነው።የመንግስትን የጎሳ ፖለቲካን ጨምሮ በየቦታው እያቆጠቆጡ ያሉትን የጎሳ አራማጆችን አደብ ማስገዛት የሚቻለው የተቃውሞ የፖለቲካ መስመሩን ሕዝብ ሲዘውረው ነው።



ኢትዮጵያ በቅርብም ሆነ በሩቅ ጠላቶቿ የተደገሰላት ለዘመናት ሲውጠነጠን የነበረ የማጥፍያ ''ቦንብ'' በየቦታው መፈነዳዳት ጀምሯል።ጎሳን መሰረት ያደረገው አስተዳደር ለሁለት አስር ዓመታት ያህል ደጋግሞ  ሲወጋው የነበረው ኢትዮጵያዊነት በአንዳንድ ቦታዎች እየተጎዳ መሆኑን ምልክቶች እየታዩ ነው።

ትናንት ባህርዳር የመላው ኢትዮጵያ የስፖርት ውድድር ላይ በኦሮምኛ ተናጋሪ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ላይ በዋልጌ የከተማዋ ነዋሪዎች ተፈፀመ የተባለው ስብእናን የሚነካ ተግባር አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን በድርጊቱ ፈፃሚዎች ላይ ተገቢው ቅጣት አስፈላጊ መሆኑን የሚያመላክት ነው።ኢትዮጵያ ተዘዋውረው የማይነግዱባት፣በፈለጉት ክልል ሄደው በህጋዊ መንገድ እርሻ ለማረስ  ቋንቋ የሚጠየቅባት ሃገር መሆኗ ሲያሳዝነን ከርሞ ዛሬ ደግሞ የስፖርት ውድድር ለማድረግ የማይቻልባት ሀገር መሆኗ የጊዜያችን አሳዛኝ ክስተት ነው።

ኢሕአዲግ/ወያኔ የመሰረተው የጎሳ ፖለቲካን ማዕከል ያደረገ ስርዓት የችግሮቹ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑን መዘንጋት የለብንም።የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆኖ ነው እንጂ ሌላ ሃገር የኢህአዲግ አይነት የጎሳ ፖለቲካ የሚያራምድ መንግስት ቢገጥመው  22 ዓመታት አይደለም በ 6 ወራት ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እንደሚገባ ሳይታለም የተፈታ ነው።

 በሌሎች አፍሪካውያን ሃገራት ጎሳ እና ቋንቋን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ድርጅት መመስረት በሕግ የተከለከለ ነው፣እኛ ጋር ግን ይበረታታል።ይልቁን ለፍቃድ ቅድምያ የሚሰጠው በጎሳ ለተመሰረቱቱ ነው።በሃገራዊ መልክ የተደራጁ ፍቃድ ለማግኘትም ብዙ ፈተና አለባቸው።ለምሳሌ የሰማያዊ ፓርቲ ፍቃድ እንዲሰጠው አመልክቶ ለብዙ ወራት ሳይሰጠው ቆይቶ በእራሱ እውቅናውን ማወጁን ከገለፀ በኃላ ነው ፍቃድ የተሰጠው።

በሌሎች አፍሪካውያን በስልጣን ላይ ያለ ማንኛውም ሰው የመጣበትን ጎሳ የበላይነት በየመድረኩ ላይ መለፈፍ አይችልም።በኬንያ በዑጋንዳ ብንመለከት ሚኒስትሮች ይህንን ቢያደርጉ በሕግ ይቀጣሉ።እኛ ጋር ግን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የመጡበትን ብሔር መጥቀስ ብቻ ሳይሆን ከእዚህ ብሔር በመምጣታቸው ኩራት እንደሚሰማቸው ሕዝብ በተሰበሰበበት ያደረጉት ንግግር አሁንም ድረስ በብዙ ሰዎች እጅ ይገኛል።

 በሌሎች የአፍሪካ ሃገራ ውስጥ የአስተዳደር መዋቅሮች በተለይ ክልልሎች ቋንቋን መሰረት እንዳያደርጉ ጥንቃቄ ይደረጋል። ለምሳሌ ዑጋንዳን ብንመለከት የማዕከላዊው ቡጋንዳ ግዛት ውስጥ የምትገኘው የሀገሪቱ ዋና ከተማ ካምፓላ ከምዕራብ የመጡት ''መኛንኮሌ'' ሆነ ከሰሜን የመጡት ጎሳዎች እኩል በዜግነት ይኖሩበታል እንጂ በንጉሥ ደረጃ ያለው የቡጋንዳ ጎሳ የበላይነቱን አያሳይባትም።

ሌሎች ሃገራት በጎሳ ፖለቲካ ላይ ጥንቁቅ ናቸው።በእያንዳንዱ ሕግም ሆነ የሚድያ ሥራ ላይ የማይነኩ ቀይ መስመሮች ያሰምራሉ።እኛ ጋር ግን ቀዩን መስመር የሚረጋግጠው በጎሳ ላይ በተመሰረተ ሕግ የሚመራ የፖለቲካ መስመር ያለው መንግስት እራሱ ነው።ኢትዮጵያውያን ሳንጠፋ ልንቃወመው የሚገባን የመንግስት የጎሳ ፖለቲካ መስመርን ነው።ከመንግስት ሌላ በጎሳ ፖለቲካ በማናፈስ የምታወቁቱ የባሕርዳር ጥፋት ፈፃሚዎችን ጨምሮ፣በአምቦ ወረዳ አፈናቃዮች፣የጉርዳፈርዳ ውጡ ባዮች፣የቤንሻንጉል ባለግዜዎች፣የሐረር የነዋሪውን ሱቅ በእሳት አቀጣጣዮች፣በሱማሌ ክልል የኦሮምኛ ተናጋሪዎችን አሳዳጆች ወዘተ በትክክል አትከፋፍሉን ብለን መቃወም ስንችል ነው።

ድህነት በተስፋፋበት ሕብረተሰብ ውስጥ የጎሳ ፖለቲካ የነዳጅ ያህል እሳት አቀጣጣይ ነው።የከፋው እና ኑሮ የከበደው ሁሉ ብሶቱ ንግግሩ ይከብዳል። በእዚህ ላይ የጎሳ ፖለቲካ የሚያራምድ መንግስት ባለበት ሀገር።እናም መንግስት በቀዳሚነት ከጎሳ ፖለቲካ የወጣ እውነተኛ የፖሊሲ ለውጥ ያስፈልገዋል።ለእዚህ ለውጥ ዝግጁ ካልሆነ ግን ሕዝብ የጎሳ ፖለቲካ በቃን ብሎ የሚነሳበት ጊዜ ነው ማለት ነው።እናቶች ልጆቻችን በጎሳ ፖለቲካ አያልቁም! ወንዶች ለጎሳ ፖለቲካ አንተባበርም! አዛውንቶች የጎሳ ፖለቲካ አይጠቅምም! መንግስት ከጎሳ ፖለቲካ ይውጣ! መባል ያለበት ጊዜ ነው።የመንግስትን የጎሳ ፖለቲካን ጨምሮ በየቦታው እያቆጠቆጡ ያሉትን የጎሳ አራማጆችን አደብ ማስገዛት የሚቻለው የተቃውሞ የፖለቲካ መስመሩን ሕዝብ ሲዘውረው ነው።ይህ የሕልውና ጉዳይ ነው።

ጉዳያችን
መጋቢት 18/2006 ዓም 

No comments:

Beynouna Village - Ethiopia (Video) ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሃራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)

Beynouna Village - Ethiopia (Video) ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሐራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)