Friday, September 13, 2013

ትኩስ ዜና ስለ ዘመን ተሻጋሪው አየርመንገዳችን


ኢትዮጵያ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ከገነባቻቸው ተቋማት ውስጥ በውጤታማነቱ የሚጠቀሰው አንዱ እና ጉልሁ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው።የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየዘመኑ ሀገራችን ከሚገጥማት ፖለቲካዊ ፈተናዎችን የሚወጣበት የእራሱ የሆነ ''የጥሩ ነጋዴ ክህሎት'' ማዳበሩን የሚናገሩ አሉ።ለእዚህ አይነቱ ክህሎት ያላበሰው አይነተኛ ምክንያት ደግሞ  የረጅም ጊዜ ልምድ ያዳበሩ ሰራተኞቹ ድርጅቱን በጡረታ አልያም ለሌላ ድርጅት በተሻለ ደሞዝ ትተው ቢሄዱምካሉበት ሀገር ሆነው ማኔጅመንቱን በምክር ከማገልገላቸውም በላይ የእኔነት ስሜት (belongingness) በሌሎች ላይ በማሳደር የሚፈጥሩት በጎ ተፅኖ ተጠቃሽ ነው።


የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች ከድርጅቱ በጡረታም ሆነ የተሻለ ሥራ አግኝተው ከወጡም በኃላ ጠንካራ በሆኑት ማኅበራቱ ለምሳሌ በገንዘብ ቁጠባ እና ብድር ማኅበር፣በጡረተኞች ማህበር፣የአብራሪዎች ማኅበር በመሳስሉት መንገድ ድርጅቱ የሚያገኝበት መንገድ አለው።ይህም እንደ አንዳንድ መስርያቤቶች ሰራተኞች ጡረታ ሲወጡ ድርጅቱን በሩቅ ተመልካች እንዳይሆኑ ባለማድረጉ ለአብነት ተጠቃሽ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በያዝነው ሳምንት መጀመርያ ላይ መሰረቱን አሜሪካ፣ካሊፎርንያ  ያደረገው Airline Passenger Experience Association (APEX) በተሰኘ ድርጅት ተሸላሚ ሆኗል።

ይሄው በመላው አለም በአየር መንገድ ለሚጠቀሙ መንገደኞች ምቾት የሚሰራው ድርጅት  በአለም ዙርያ በአየር መንገድ ለሚጠቀሙ መንገደኞች በቀጥታ በሚጠይቀው መጠይቅ በሚልዮን የሚቆጠሩ  መንገደኞች የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምርጫቸው መሆኑን እንደገለፁለት አሳውቆ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ''የ 2013 በአፍሪካ በደንበኞች የበለጠ ተመራጭነት'' ሽልማት አሸናፊ መሆኑን ገልጧል።ዜናውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ  እና ''All africa.com'' መስከረም 2/2006 ዓም በድህረ ገፃቸው ላይ ዘግበውታል።

በሌላ በኩል  ''ሰላምታ'' የተሰኘው የኢትዮጵያ አየርመንገድ መፅሄት በዓለም ላይ ካሉት የበረራ መፅሄቶች ውስጥ ከአምስቱ ምርጦች ውስጥ መደመሩ እና ለሽልማት መብቃቱ ሌላው ተጨማሪ  የዜናው አካል ነበር።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከብዙ ድርጅቶች ብዙ ሽልማቶችን ተቀብሏል።እንደዚህ በቀጥታ በሚልዮን የሚቆጠሩ ደንበኞች ሲመርጡት መመረጡን ደግሞ ገለልተኛ የሆነ ድርጅት ሲያረጋግጥ ሀገርኛ ደስታ ነው።ለዘመን ተሻጋሪው አየር መንገዳችን መልካም አዲስ ዘመን።

ጌታቸው በቀለ 
ኦስሎ 

Tuesday, September 10, 2013

የ2005 ዓም የጉዳያችን ጡመራ ሁለት ምርጦች


የእኔ የ2005ዓም ምርጤ ማነው? ብዬ አሰብኩ።

ዘንድሮ ማንን አደነቅሁ? ብዬ እራሴ ለእራሴ ጠየቅሁት? ለአመታት ያጣነውን የሙያውን ስብዕና እያላበሱ ያሉ ሁለት ክቡራኔን አገኘሁ።የጋዜጠኛ ሙያ ስብዕናን።

ዳኛው እኔው መራጩ እራሴው። ምን ቀረ?
በ 2005 ዓም ብዙ መልካም የሰሩ ሰዎች ይኖራሉ። እኔ ግን ስለ እነኚህ ኢትዮጵያውያን ''የአመቱ ሰው'' ብላቸው ማን ከልካይ አለብኝ?

ማንነህ እና ነው አንተ የአመቱ ምርጥህን የምትመርጠው? ማለት አይቻልም።በጡመራ መድረክ(ብሎግ) ሁሉም ሰው ሃሳቡን በነፃ እንዲገልፅ የፈቀደው ህገ-ቴክኖሎጂ የእዚህ አይነቱን ጥያቄ አያስተናግድምና።

በ 2005 ዓም ብዙ ነገር አድንቄ ይሆናል።ሀገራቸውን ከልብ ከሚወዱ ውስጥ በሩቁ የተመለከትኩትን ግን እንዳደንቅ ይፈቀድልኝ።

ደግነቱ አያውቁኝ አላውቃቸው።የቴሌቭዥን መስኮት አገናኘን እንጂ።እኔ በመመልከት እነርሱ በማቅረብ። ሌላ የምሸልማቸው የለኝም።ያለችኝ ትንሿ የጡመራ መድረክ (ጉዳያችን ጡመራ) ነች።

እነኚህ ሁለት ምርጦቼ ስለሚከተሉት ሶስት ነገሮች የአመቱ ምርጥ ጋዜጠኞች መባል አለባቸው እላለሁ።

  •  ጋዜጠኝነትን ኢትዮጵያዊ ጨዋነት፣ትሕትናን እና ድፍረትን በአንድነት አላብሰውታል፣
  •  የሃገር መውደድ ከፊታቸው ይነበባል። የእውነት መደበቅ ደግሞ  ሲያበሳጫቸው ያስታውቅባቸዋል፣
  • በሚያቀርቡት ጥያቄ ሃብታምን በሀብቱ አያፍሩትም፣ጉልበተኛውን ስለጉልበቱ አይራሩለትም ተመልካች አዕምሮ ውስጥ ሊኖር ቢችል ያሉትን ጥያቄ ያቀርባሉ።

የኢሳት ጋዜጠኞች ሲሳይ አጌና  እና ደረጄ ደስታ የ 2005 ዓም ምርጥ የጋዜጠኝነት ብቃት በማሳየት ምርጦቼ ናቸው።

ጌታቸው በቀለ
ኦስሎ


ጋዜጠኛ ደረጄ ደስታ                                           




              ጋዜጠኛ   ሲሳይ አጌና



























Friday, September 6, 2013

ከሰላሳ ሺህ ቃላት በላይ የያዘ ኖርዌይኛ-በአማርኛ አዲስ መዝገበ ቃላት በገበያ ላይ ዋለ

አምስት መቶ ስልሳ ገፅ የያዘ ኖርዌይኛ በአማርኛ  መዝገበ ቃላት በአይነቱ ልዩ በሁለት ኢትዮጵያውያን ተዘጋጅቶ እና በኖርዌይ ትምህርት ሚኒስቴር ታትሞ በመፃህፍት መደብሮች በገበያ ላይ መዋሉን ለማወቅ ተችሏል።በኖርዌይ የብዙ ሀገሮች መዝገበ ቃላት (የሱማልኛን ጨምሮ) በኖርዌይኛ ተተርጉሞ መኖሩ ሲታወቅ የኢትዮጵያ ግን በእየመፃሕፍት መደብሮች አልፎ አልፎ ከሚታዩት  በቃላት ብዛታቸውም ሆነ በይዘታቸው እጅግ ትንንሾች እና የተወሰኑ ቃላትን ብቻ የያዙ ጥቂት የአማርኛ እና የትግሪኛ መዝገበ ቃላት ብቻ በመኖራቸው በብዙዎች ዘንድ ደረጃውን የጠበቀ የመዝገበ ቃላት አስፈላጊነት ጉዳይ ሲወሳ ነበር። 

ይህ ከሰላሳ ሺህ በላይ ቃላት መያዙ የተነገረለት መዝገበ ቃላት የተዘጋጀው በሁለት ኢትዮጵያውያን ማለትም በአቶ እንግዳ እሸት ታደሰ እና  በተባባሪያቸው አቶ አበበ ተፈራ ሲሆን እንደ አቶ እንግዳ እሸት ገለፃ መዝገበ ቃላቱን ለማዘጋጀት እና ደረጃውን የጠበቀ አድርጎ ለማውጣት  ሃያ አመታት እንደደከሙበት ለማወቅ ተችሏል። 

ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት ሀገር ሊሰሯቸው ከሚገባቸው ተግባራት ውስጥ ዋነኞቹ እንደዚህ አይነት ትውልድ ተሻጋሪ እና ለሀገር የሚጠቅሙ ስራዎች መሆን እንደሚገባ የኢትዮጵያውያኑን ሥራ በአብነት መጥቀስ ይቻላል።

በመጨረሻም መፅሐፉን በመስመር ላይ ( on line) ለማዘዝም ሆነ በአካል ወደ መደብር ሄደው  ለመጠየቅ የመፅሐፉን ኮድ (ISBN number 978-82-450-1360-3) መያዝ ጊዜ ይቆጥባል።



ጌታቸው በቀለ 
ኦስሎ 


Wednesday, September 4, 2013

የሶርያ ጉዳይ (አጭር ማስታወሻ)


President Barack Obama meets with Members of Congress to discuss Syria in the Cabinet Room of the White House, Sept. 3, 2013. (Official White House Photo by Pete Souza)
ፕሬዝዳንት ኦባማ በዋይትሐውስ የካቢኔ መሰብሰብያ አዳራሽ ውስጥ ከምክርቤት አባላት ጋር ሲወያዩ (ማክሰኞ ነሐሴ 28/2005 ዓም ፎቶ በፔተ ሳኡዛ )

አሜሪካ በተናጥል በሶርያ ላይ ጥቃት የመፈፀሟ ግምት እያደገ ነው።ከምክርቤቱ ስብሰባ በኃላም ጉዳዩን በቀላሉ ማጣጣል አልተቻለም።ፈረንሳይ ጥቃቱን ብትደግፍም ብቻዬን ግን አይሆንም ብላለች።ቢያንስ የአሜሪካ ከጎኗ መቆም አስፈላጊ ነው እያለች ነው።የሶርያው በሽር አል-አሳድ ወደመጨረሻ ደረጃ ላይ ሲደርሱ ያለ የሌለ ኃይላቸውን (በተለይ በአለም በኬሚካል የጦር መሳርያ ምርት ቀደምት የሆነችውን ሀገራቸውን) በእስራኤል ላይ ሊያሳዩ ይችላሉ ተብሎ ተፍርቷል።እስራኤል ለዜጎቿ የፊት መሸፈኛ ጭንብል ማደል ከጀመረች ሳምንታት ተቆጥረዋል። ኦባማ ፈለጉት አልፈለጉትም አሜሪካ እያለች  የአይሁዳውቷ ሀገር ጥቃት ማየት የማይችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።

የእንግሊዝ ፓርላማ በጉዳዩ ላይ አሉታዊ ድምፅ ቢሰጥም ከመስከረም 5 እስከ 6/2013 እኤአ በሩስያ ዋና ከተማ ቅዱስ ፔተርስፐርግ (St. Petersburg) ከተማ የሚደረገው የቡድን 20 ሀገሮች ስብሰባ ላይ የአሜሪካ እና የሩስያ ፍጥጫ በሶርያ ጉዳይ ላይ ጎልቶ የመውጣት ዕድል እንዳለው ይገመታል።ከእዚህ በተለየ ግን አሜሪካ እንደተገመተው ጥቃት ከፈፀመች እና ጦርነቱ በአጭሩ ከማለቅ ይልቅ የአካባቢውን ሀገሮች በረጅም ጊዜ ወገን እንዲይዙ ወደመምራት ከሄደ ለአፍሪካ ቀንድም የራሱ የሆነ አጀንዳ ይዞ ሊመጣ ይችላል።

ጦርነቱን በአሜሪካ ዘመቻ ቢጀመር በአጭር ጊዜ ላለመጠናቀቁ አንዱ እና አይነተኛ አመላካች ጉዳይ በአሜሪካ በትጥቅ እና ስንቅ የተደገፉት  የባሽር ተቀናቃኞች እራሳቸው የዘመቻ-አሜሪካንን መጀመር ፈፅመው እንደማይቀበሉ እያሳወቁ መሆኑ ነው።ለሁሉም ግን ጉዳዩ ከአንድመቶ አስር ሺህ በላይ ሶርያውያን ከሞቱ በኃላ የአሜሪካ የዘመቻ ጉሰማ አለምአቀፉ ሕብረተሰብን ለማፅናናት ይሁን ወይንስ  ከምር አይሁዳውቷን ሀገር  ለመከላከል መሆኑ ከሰሞኑ የሚታዩ ክስተቶች ግልፅ ያደርጉልናል።

በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ ድልድይ አንደመሆኗ እሳቱ እሩቅ ነው በሚል ቅኝት ብቻ ማለፍ አይቻልም። እንደዛ ከታሰበ በኩሬ ውስጥ ሆና እሳት ሲነሳ የሳቀችው እንቁራሪትን መርሳት ነው። ይችው እንቁራሪት ማዶ በሚነደው እሳት ስትስቅ በመጨረሻ እሳቱን ለማጥፋት ውሃ ሲቀዱ ከባሊው ውስጥ ጨምረዋት ወደ እሳቱ እንደከተቷት ማሰብ ይገባል።ለማለት የፈለኩት ጉዳዩ  በቀጥታ ባይነካንም ጦርነቱ ከረዘመ ግን የእራሱ የሆነ አዲስ አጀንዳ እና የኃይል አሰላለፍ ይዞ አይመጣም ማለት አይቻልም ነው።እዚህ ላይ ነፍሳቸውን ይማረው እና ደራሲ እና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህን ማሰብ ይገባል።ጋሽ ማሞ በተለይ ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር የተያያዙ ታሪኮችን በትርጉም ባስነበቡን መፃህፍቶቻቸው ለምሳሌ ''የካይሮ ጆሮ ጠቢ''፣ የእኛ ሰው በደማስቆ'' መግቢያ ላይ መፅሃፎቹን ለመተርጎም ምን እንዳነሳሳቸው የሚያሰምሩበት ነጥብ አንድ እና አንድ ነው። ይሄውም መካከለኛው ምስራቅ ውስጥ የሚነሱ ጉዳዮች በሙሉ ኢትዮጵያን በታሪክም ሆነ በወቅታዊ ክስተቶች ሁሉ ይነካታል የሚል ነው።

መልካም አዲስ አመት

ጌታቸው
ኦስሎ

Tuesday, September 3, 2013

የህፃኑ ጥሪ - (እስክንድር ነጋን እና ሌሎች በግፍ የታሠሩ የህሊና እሥረኞችን ለማሰብ የተጻፈ! ግጥም በአንዱአለም በቀለ 2005ዓም)



በረንዳ ቢወጣ - እጉዋዳ ቢገባ፣
ቢጣራ ቢጣራ - አስሬ ቢል ባባ፣
እናቱን ቢያስጨንቅ - ፊቱ ተጥቦ በ'ንባ፣
ውስጧ ቢተራመስ - የሷም ሆድ ቢባባ፣
መልስ ግን የላትም - ታውቀዋለችና፣
ለጊዜው አይመጣም ...
እውነትን ፍለጋ - ትግል ላይ ነው ባባ።


ውጣ ችላው እንጂ - እሷስ ምን ታድርገው፣
ቀን ዘሞባት እንጂ - እሷስ መቼ ፈቅዳው፣
ምን ብላ ትዋሸው - እነደምን ታባብለው፣
ያን ቆሻሻ ታሪክ - ምን ብላ ትንገረው!፣
......................እንዴት ትተርከው!፣
ቢሆንም ታሪክ ነው - ይወቀው ይረዳው፣
ፈርድ የሚሰጥበት - የነገ ሥራው ነው፣
......................ብላ እያየችው፣
"ባክህ ማሙሽዬ - ነገሩ እንዲህ ነው፣
ቆየ 'ኮ ከረመ - ቤታችን ወህኒ ነው፣
አንተን የወለድኩህ - እትብትህም ያለው፣
ባታውቀውም ቅሉ - እስር ቤት እኮ ነው!፣
አባትህም ባባ - እዛችው ቦታ ነው፣
ርቆ አልሄደም - እዛው እቤቱ ነው፣
ከሞቀ ኑሮው - አብርሮ ያመጣው፣
የሃገሩ ነገር - የወገን ፍቅር ነው፣
...............እናም እዚሁ ነው፣
እዚሁ ሀገሩ - እዚሁ እስር ቤት ነው፤
ታገስ ማሙሽዬ - ታሪኩ ብዙ ነው፤
በአምላክ ቸርነት - በነፃ ተፈጥረው፣
እንዳንተው ማሙሽን - ጨቅላቸውን ትተው፣
ታስረው የሚኖሩ - ብዙ አባቶች ናቸው፤
ኦልባና ና አንዱዓለም - ፍትህ የራቃቸው፣
በቀለ ና ውብሸት - እውነት የጠማቸው፣
መቁጠር የሚታክት - ብዙ ዜጎች ናቸው፤
ይገባሃል ማሙሽ - ሁሉም እስር ቤት ነው!፤
አይዞህ ማሙሽዬ - አባትህ ጎበዝ ነው፣
ለኛም ለእነሱም - ለሁላችን ሲል ነው፤
ከኔ በፊት ሀገር - ወገኔ ብሎ ነው፣
እኔንም አንተንም - ታስሮ ሊያስፈታ ነው፤
ሀገርን ከ'ስር ቤት - እስር ቤትን ካገር...
......................ታስሮ ሊለይ ነው።
ደግሞም ማሙሽዬ - ሌላም ሚስጥር አለው፣
ምናልባት አባትህ - ቢመረጥ እኮ ነው!፣
ከሌላው ለይቶ - ምሳሌ ሊያረገው፣
እሱን ሻማ አርጎት - ለሌላ ሊያበራው፣
በሱ ወህኒ መውረድ - ሌላውን ሊያስፈታው፣
ለዛም 'ኮ ይሆናል - ጨለማ የጣለው!፣
እንዴ ማሙሽዬ.......................!
የፈጣሪ ሥራ - ረቂቅ እኮ ነው!፣
እቺን የኛ ዓለም - ከጥፋት ያዳነው፣
የኛን ክፉ ሥራ - በደሙ ያጠበው፣
ያ የዓለም ጌታ - ሁሉን ያደረገው፣
እከብቶች ማደሪያ - በረት ተወልዶ ነው!።
የጥቁርን ውርደት - መንግሎ የጣለው፣
ማንዴላ ሃገሩን - ባ'ለም ከፍ ያረገው፣
ሃያ ሰባት ዓመት - ታሥሮ ተገርፎ ነው!።''

ብላ ስታወራው - ይሰቀጥጣታል፣
ይሄ ጨቅላ ህጻን - እንዴት ይገባዋል!፣
ሃገርን ከእሥር ቤት....................
እሥር ቤትን ካገር - እንዴት የለየዋል?፣
ቢሆንም ግን ቅሉ - ማሙሽ ያስተውላል፣
አባቱን ሊያይ ሲሄድ - ፖሊስ ይቆጣዋል፣
ከእቅፉ እንዳይቆይ - በብረት ተከቧል፣
ባባ ወጥቶ አይመጣ - በግረ ሙቅ ታሥሯል፣
እንዴት አያስጨንቅ..................!
ሁሉም ታሥሮ እያየ - ምኑን ይለየዋል!፣
ያባት ፍቅር ሳያይ - ሃገር እንዴት ያውቃል!?
በምን መመዘኛ..........................
ሃገር ተረካቢ - ተተኪ ይባላል?፣
እሥር ቤት ነው ሃገር - ምኑን ይረከባል!፣
እንኳን ለዚህ ጨቅላ - እኛም ቸግሮናል፣
እንኳን ለመናገር - መስማት ወንጀል ሆኗል፣
በገዛ ጣታችን - መጻፍ ያስጠይቃል፣
ዓይናችንም ላየው - አንቀጽ የጠቀሳል፣
በነፃ ተፈጥረን - ሆኖ አለመታደል፣
ዳግመኛ ነጻነት - ከሰው ይለመናል!፤
እንቆቅልሽ ነገር - እርግጥ ነው ይጨንቃል፣
ለዚህ ህፃን ጨቅላ - ለምን ይተረካል?!
ማሙሽ ግን ብልህ ነው - ተችሮት ማስተዋል፣
ሁሉንም ታዝቧል - ጠልቆ ተረድቶታል፣
መዝለል መቦረቁን - የልጅ ወጉን ትቷል፣
ይወጣል ይገባል - እናቱን ያያታል፣
እንደሰውነቱ - እውነት ይፈልጋል፣
ችላ ባትመልስም - ማሙሽ ይጠይቃል፣

''ማማ ምን ይሻላል?
እኔም ባባን ሳክል - ፖሊስ ይወስደኛል?፣
ጨለማ ክፍል ውስጥ - ይቆልፉብኛል?፣
ሰው እነዳላናግር - ይከለክሉኛል?፣
ቆይ ደሞ ማማዬ'' - ይላል ይቀጥላል፣
''ለወገኑ ሲል ነው - ያሰሩት ብለሻል፣
ይሄ ሁሉ ሥቃይ - ላገር ነው ብለሻል፣
እሱ እንዲህ ሲሆን - ወገኑ ግን የታል!?
ስሚኝ ባክሽ እናት.......................!
እንደዚህ ናት ሃገር - እኔም የማድግባት?፣''
ግን ለምን ወለድሽኝ - ምን ይሰራልኛል፣
ይላል ይገረማል - እናቱን ያያታል፣

መልስ ያጣ ጥያቄ - ምን መልስ ይኖራታል!፣
እናት ታለቅሳለች - እሱም ይጠይቃል፣
ህፃኑ ይጣራል - የአባት የወገን ያገር ያለህ ይላል፣
ላባቱ ያልሆነ - ሀገር ያስፈራዋል፣
ያቅበጠብጠዋል - ይጣራል ይጮሃል!፣
የተኛችሁ ንቁ - የነቃችሁ በረቱ አንድ ሁኑ ይለናል፣
ማሙሽ እውነቱን ነው - በጣም ያስጨንቃል፣
መውለድ እስኪያስፈራ - መጪው ያሳስበል፣
ሀገር ለማቆየት - ተተኪ ለማብቀል፣
ከዚም ጫፍ ከዚያም ጫፍ - አርቆ ማስተዋል፣
ከራስ በዘለለ - ማሰብ ያስፈልጋል፣
ደጋግሞ ደጋግሞ - መጨነቅ ይገባል፣
የህፃኑ ጥሪ - - - -ምላሽ ይፈልጋል።


Sunday, September 1, 2013

ሕጉ ለሕግ አክባሪው ከለላ ካልሰጠ ሕግ አለማክበር ሆይ ምንኛ ታላቅ ነሽ! (አጭር ማስታወሻ)


 የሕግ ከለላን እና በሕገመንግሥቱ የተቀመጠውን ሕግ ተማምነው የሰላማዊ ሰልፍ የጠየቁ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ለእሁድ ነሐሴ 26 ሰልፍ በዝግጅት ላይ ሳሉ ቅዳሜ ነሐሴ 25 ምሽት  በፅህፈት ቤታቸው ላይ በተደረገው ድንገተኛ የፌድራል ፖሊስ የማሸበር ተግባር ተደብድበዋል፣ተሰድበዋል ግማሾቹ ለከፍተኛ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል።

 የተቀመጠው ሕግ የሚሰራው የአይን ቀለም እና ምላስ እየለየ መሆኑ ተነግሯቸዋል።በድብደባው ወቅት ተሰድበዋል፣ተረግጠዋል። በኢትዮጵያ ሕግ ስር በህጋዊነት የተመዘገበ የፖለቲካ ፓርቲ ቀርቶ የንግድ ፍቃድ አውጥታ የምትሰራ ለትንሿ ኪዮስክም ተገቢ ክብር መስጠትለታደለ መንግስት የሚከውናት ትንሿ ተግባር ነበረች። ማክበር ደግሞ ለመከበር ይጠቅማል። የወያኔ ታጣቂዎች ግን ከእነርሱ አስተሳሰብ በተለየ የሚያስበውን ግለሰብም ሆነ ድርጅት በጠላትነት ፈርጀው ሃገሩ የእነርሱ የአምባገነንነት ላንቃ ማላቀቅያ ሲያደርጉት ማየት አለመታደል ነው።አንዳንዶች እጅግ ከበዛ ፍርሃታቸው እና ለስርዓቱ ካላቸው አፈር የላሰ ታማኝነት የተነሳ በሰማያዊ ፓርቲ አባላት ላይ የተፈፀመው የማሸበር ተግባር ''እንዳስደሰታቸው ሲናገሩ'' አፋቸውን ትንሽም ወለም አይላቸውም። የሰማያዊ ፓርቲ የመሰሉ ፍትህ፣ስርዓት እና የሕግ ልዕልና ይኑር የሚሉ ፓርቲዎችም ሆኑ ግለሰቦች የሚታገሉት ለእነዚህ የስርዓቱ ታማኞችም ጭምር ለነገ ዋስትና እየታገሉ መሆናቸውን አለመረዳታቸው የግንዛቤ ውሱንነትን ያመላክታል።

እርግጥ ነው ይህ ክስተት ላለፉት 22 አመታት ሲከናወን የነበረ መሆኑ ዛሬ እንደ አዲስ ሊወሳ ላይችል ይችላል።ጉዳዩን ለማውገዝም ሆነ ወያኔ የሚማርበትን ሁነኛ መንገድ መፍጠር የግድ የሰማያዊ ፓርቲ አባል መሆን ወይንም ፓርቲውን በቅርብ ማወቅ አይጠይቅም።የእዚህ አይነቱን  የእብሪት ተግባር  የመግታት ተግባር የእዚህ ትውልድ ዕዳ ለመሆኑ ግን ቅንጣት  ታክል መጠራጠር አይገባም።

የሃገራችሁ መፃኢ ዕድል አሳስቧችሁ የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆናችሁም ሆናችሁ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የታተራችሁ ሁሉ ክብር ሊቸራችሁ ይገባል።ዘመን ስም ሊለጥፍ ይችላል። በፋሽሽት ጣልያን ዘመን ለኢትዮጵያ ነፃነት በዱር በገደሉ የሚጋዳሉ አርበኞችን ፋሺሽት ''ወንበዴዎች'' ይባሉ ነበር።በዘመነ ደርግ ዲሞክራሲ ያሉ ''የኢምፐራሊዝም'' አቀንቃኞች ይባሉ ነበር።እናንተም  ለሕግ፣ለሞራል እና ለሥርዓት እንደምትገዙ በመግለፅ ጥያቄያችሁን አቀረባችሁ።መልሱ ግን በግፍ መደብደብ ሆነ።ካለስማችሁ ስም ተሰጣችሁ። የእዚህ ጊዜ ነው ታድያ ሕጉ ለሕግ አክባሪው ከለላ ካልሰጠ ሕግ አለማክበር ሆይ  ምንኛ ታላቅ ነሽ! ማለት ተገቢ የሚሆነው።





ጉዳያችን GUDAYACHNgetachewb221@gmail.com