ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, September 3, 2013

የህፃኑ ጥሪ - (እስክንድር ነጋን እና ሌሎች በግፍ የታሠሩ የህሊና እሥረኞችን ለማሰብ የተጻፈ! ግጥም በአንዱአለም በቀለ 2005ዓም)በረንዳ ቢወጣ - እጉዋዳ ቢገባ፣
ቢጣራ ቢጣራ - አስሬ ቢል ባባ፣
እናቱን ቢያስጨንቅ - ፊቱ ተጥቦ በ'ንባ፣
ውስጧ ቢተራመስ - የሷም ሆድ ቢባባ፣
መልስ ግን የላትም - ታውቀዋለችና፣
ለጊዜው አይመጣም ...
እውነትን ፍለጋ - ትግል ላይ ነው ባባ።


ውጣ ችላው እንጂ - እሷስ ምን ታድርገው፣
ቀን ዘሞባት እንጂ - እሷስ መቼ ፈቅዳው፣
ምን ብላ ትዋሸው - እነደምን ታባብለው፣
ያን ቆሻሻ ታሪክ - ምን ብላ ትንገረው!፣
......................እንዴት ትተርከው!፣
ቢሆንም ታሪክ ነው - ይወቀው ይረዳው፣
ፈርድ የሚሰጥበት - የነገ ሥራው ነው፣
......................ብላ እያየችው፣
"ባክህ ማሙሽዬ - ነገሩ እንዲህ ነው፣
ቆየ 'ኮ ከረመ - ቤታችን ወህኒ ነው፣
አንተን የወለድኩህ - እትብትህም ያለው፣
ባታውቀውም ቅሉ - እስር ቤት እኮ ነው!፣
አባትህም ባባ - እዛችው ቦታ ነው፣
ርቆ አልሄደም - እዛው እቤቱ ነው፣
ከሞቀ ኑሮው - አብርሮ ያመጣው፣
የሃገሩ ነገር - የወገን ፍቅር ነው፣
...............እናም እዚሁ ነው፣
እዚሁ ሀገሩ - እዚሁ እስር ቤት ነው፤
ታገስ ማሙሽዬ - ታሪኩ ብዙ ነው፤
በአምላክ ቸርነት - በነፃ ተፈጥረው፣
እንዳንተው ማሙሽን - ጨቅላቸውን ትተው፣
ታስረው የሚኖሩ - ብዙ አባቶች ናቸው፤
ኦልባና ና አንዱዓለም - ፍትህ የራቃቸው፣
በቀለ ና ውብሸት - እውነት የጠማቸው፣
መቁጠር የሚታክት - ብዙ ዜጎች ናቸው፤
ይገባሃል ማሙሽ - ሁሉም እስር ቤት ነው!፤
አይዞህ ማሙሽዬ - አባትህ ጎበዝ ነው፣
ለኛም ለእነሱም - ለሁላችን ሲል ነው፤
ከኔ በፊት ሀገር - ወገኔ ብሎ ነው፣
እኔንም አንተንም - ታስሮ ሊያስፈታ ነው፤
ሀገርን ከ'ስር ቤት - እስር ቤትን ካገር...
......................ታስሮ ሊለይ ነው።
ደግሞም ማሙሽዬ - ሌላም ሚስጥር አለው፣
ምናልባት አባትህ - ቢመረጥ እኮ ነው!፣
ከሌላው ለይቶ - ምሳሌ ሊያረገው፣
እሱን ሻማ አርጎት - ለሌላ ሊያበራው፣
በሱ ወህኒ መውረድ - ሌላውን ሊያስፈታው፣
ለዛም 'ኮ ይሆናል - ጨለማ የጣለው!፣
እንዴ ማሙሽዬ.......................!
የፈጣሪ ሥራ - ረቂቅ እኮ ነው!፣
እቺን የኛ ዓለም - ከጥፋት ያዳነው፣
የኛን ክፉ ሥራ - በደሙ ያጠበው፣
ያ የዓለም ጌታ - ሁሉን ያደረገው፣
እከብቶች ማደሪያ - በረት ተወልዶ ነው!።
የጥቁርን ውርደት - መንግሎ የጣለው፣
ማንዴላ ሃገሩን - ባ'ለም ከፍ ያረገው፣
ሃያ ሰባት ዓመት - ታሥሮ ተገርፎ ነው!።''

ብላ ስታወራው - ይሰቀጥጣታል፣
ይሄ ጨቅላ ህጻን - እንዴት ይገባዋል!፣
ሃገርን ከእሥር ቤት....................
እሥር ቤትን ካገር - እንዴት የለየዋል?፣
ቢሆንም ግን ቅሉ - ማሙሽ ያስተውላል፣
አባቱን ሊያይ ሲሄድ - ፖሊስ ይቆጣዋል፣
ከእቅፉ እንዳይቆይ - በብረት ተከቧል፣
ባባ ወጥቶ አይመጣ - በግረ ሙቅ ታሥሯል፣
እንዴት አያስጨንቅ..................!
ሁሉም ታሥሮ እያየ - ምኑን ይለየዋል!፣
ያባት ፍቅር ሳያይ - ሃገር እንዴት ያውቃል!?
በምን መመዘኛ..........................
ሃገር ተረካቢ - ተተኪ ይባላል?፣
እሥር ቤት ነው ሃገር - ምኑን ይረከባል!፣
እንኳን ለዚህ ጨቅላ - እኛም ቸግሮናል፣
እንኳን ለመናገር - መስማት ወንጀል ሆኗል፣
በገዛ ጣታችን - መጻፍ ያስጠይቃል፣
ዓይናችንም ላየው - አንቀጽ የጠቀሳል፣
በነፃ ተፈጥረን - ሆኖ አለመታደል፣
ዳግመኛ ነጻነት - ከሰው ይለመናል!፤
እንቆቅልሽ ነገር - እርግጥ ነው ይጨንቃል፣
ለዚህ ህፃን ጨቅላ - ለምን ይተረካል?!
ማሙሽ ግን ብልህ ነው - ተችሮት ማስተዋል፣
ሁሉንም ታዝቧል - ጠልቆ ተረድቶታል፣
መዝለል መቦረቁን - የልጅ ወጉን ትቷል፣
ይወጣል ይገባል - እናቱን ያያታል፣
እንደሰውነቱ - እውነት ይፈልጋል፣
ችላ ባትመልስም - ማሙሽ ይጠይቃል፣

''ማማ ምን ይሻላል?
እኔም ባባን ሳክል - ፖሊስ ይወስደኛል?፣
ጨለማ ክፍል ውስጥ - ይቆልፉብኛል?፣
ሰው እነዳላናግር - ይከለክሉኛል?፣
ቆይ ደሞ ማማዬ'' - ይላል ይቀጥላል፣
''ለወገኑ ሲል ነው - ያሰሩት ብለሻል፣
ይሄ ሁሉ ሥቃይ - ላገር ነው ብለሻል፣
እሱ እንዲህ ሲሆን - ወገኑ ግን የታል!?
ስሚኝ ባክሽ እናት.......................!
እንደዚህ ናት ሃገር - እኔም የማድግባት?፣''
ግን ለምን ወለድሽኝ - ምን ይሰራልኛል፣
ይላል ይገረማል - እናቱን ያያታል፣

መልስ ያጣ ጥያቄ - ምን መልስ ይኖራታል!፣
እናት ታለቅሳለች - እሱም ይጠይቃል፣
ህፃኑ ይጣራል - የአባት የወገን ያገር ያለህ ይላል፣
ላባቱ ያልሆነ - ሀገር ያስፈራዋል፣
ያቅበጠብጠዋል - ይጣራል ይጮሃል!፣
የተኛችሁ ንቁ - የነቃችሁ በረቱ አንድ ሁኑ ይለናል፣
ማሙሽ እውነቱን ነው - በጣም ያስጨንቃል፣
መውለድ እስኪያስፈራ - መጪው ያሳስበል፣
ሀገር ለማቆየት - ተተኪ ለማብቀል፣
ከዚም ጫፍ ከዚያም ጫፍ - አርቆ ማስተዋል፣
ከራስ በዘለለ - ማሰብ ያስፈልጋል፣
ደጋግሞ ደጋግሞ - መጨነቅ ይገባል፣
የህፃኑ ጥሪ - - - -ምላሽ ይፈልጋል።


No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...