ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, September 28, 2013

እኛ ኢትዮጵያውያን ምን ነካን? (የጉዳያችን ጡመራ ልዩ ማሳሰቢያ)



መስከረም 19/2006 ዓም (ሴፕቴምበር 29/2013 ዓም) ''ዓለም አቀፍ የቡና ቀን'' ይከበራል።በዓሉ በዓለም ዙርያ የአከባበሩ ስነ-ስርዓት እየደመቀ መጥቷል። በ1983 ዓም እ.አ.አቆጣጠር በጃፓን ለመጀመርያ ጊዜ መከበር እንደተጀመረ የተነገረለት ''ዓለም አቀፍ የቡና ቀን'' በመጀመርያዎቹ ተከታታይ አመታት ብዙም ትኩረት አላገኘም ነበር።ሆኖም ግን ከ2005 ዓም እ.አ.አቆጣጠር ወዲህ ግን በተለይ በአሜሪካ ከፍተኛ ትኩረት እየተሰጠው ነው።

ለምሳሌ ዛሬ መስከረም 19/2006 ዓም (ሴፕቴምበር 29/2013 ዓም) በአሜሪካ የሚገኙ የቡና መጠጫ ካፌዎች በነፃ ቡና ለደንበኞቻቸው በማቅረብ በአሉን ያከብራሉ። ግዙፉ የቡና አጠጪ ድርጅት ስታርባክስ (Starbucks)  በዓሉን እንዴት እንደሚያከብር ሲገልፅ በድህረገፁ ላይ ከእዚህ በታች የምትመለከቱትን የኢትዮጵያን የቡና ጀበና ፎቶ ጋር የሚከተለውን ከትቦ ነው።
''እሁድ ብሔራዊ የቡና ቀን ነው።ኑ! በአሉን በነፃ በምናቀምስዎ  በአዲሱ የኢትዮጵያ ቡና ያክብሩ።'' ይላል ከጀበናው በታች ያለው ፅሁፍ ትርጉም ደግሞ እንዲህ ይነበባል- ''እሁድ መስከረም 29 በስታርባክስ መሸጫዎች ቡና ከተገኘባት ሀገር ከኢትዮጵያ  የመጣውን አዲሱን  ቡና ቀምሰው ያጣጥሙ።'' ይላል።
''Come into a participating Starbucks store this Sunday, September 29 for a taste of our new Ethiopian coffee and discover flavors from the birthplace of coffee.''


ስታር ባክስ ለመስከረም 29/2013 ዓም ዓለም አቀፍ የቡና ቀንን በድህረ ገፁ እና በማስታወቂያ ሰሌዳ ያስተዋወቀበት ፖስተር  (http://www.starbucks.com)


በእዚህ የቡና ዓለም አቀፍ በዓል ቀን ስታርባክስ ብቻ ሳይሆን የሚሳተፈው ለምሳሌበአሜሪካዋ ግዛት በአትላንታ ብቻ

 - ካሪቡ ኮፊ (Caribou Coffee) በበዓሉ ቀን ሙሉ ለሚመጣው ሰው  ሁሉ በትንሽ የቡና ስኒ በነፃ ስያጠጡ ይውላሉ፣

 - ዱኪን ዶኑትስ (Dunkin' Donuts) ትኩስ እና ቀዝቃዛ ቡና  በልዩ ሳሎን ደንበኞቹን በነፃ ያጠጣል፣

 - ማክዶናልድ (McDonalds)  የተቆላ ቡና በተመረጡ ቦታዎች በነፃ ያቀርባል፣

 - ስታርባክስ (Starbucks) በኢትዮጵያ የቡና መጠጫ ስኒዎች ልዩ ጣዕም ያለው የኢትዮጵያ ቡና ለደንበኞቹ ሁሉ ያቀርባል።

ከሁሉ ጉዳዩን አሳሳቢ የሚያደርገው በዓሉን የተቀረው ዓለም እንዲህ ሲያከብረው እኛ ማክበሩ ባይሳካልን ስለበዓሉ አንዳች አለመተንፈሱ ነው አስደንጋጩ ጉዳይ። የኢትዮጵያ ቆንስላዎች ምንድነው የሚሰሩት? የእዚህ አይነቱን ሃገራዊ ጉዳይ ብሔራዊ ሀብት ማፍርያ አድርገው ማቅረብ ካልቻሉ ሌላ ስራቸው ምን ሊሆን ነው?ቡና በዓለም ላይ ለመጀመርያ ጊዜ የተገኘው ከኢትዮጵያ መሆኑን ከውክፕድያ እስከ ታዋቂው ስታርባክስ ድህረገፆች የሚያስነብቡን እውነታ ነው።

ቡና ማለት አሁን ላለው ዓለም በተለይ ለምዕራቡ ዓለም የእያንዳንዱ ሰው የደምስር ያህል አስፈላጊው መሆኑን መንገር ማጋነን አይደለም።መኪና ካለነዳጅ እንደማይሰራ ሁሉ የምዕራቡ ዓለም ሕዝብ ከፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር እስከ ቢልየነር፣ከሶፍትዌር ጠቢብ እስከ የጠፈር ተመራማሪ ቢያንስ በቀን አንድ ሲኒ ቡና ካልቀመሰ ስራው ሁሉ መበላሸቱ ነው።ይህ በትንሹ የተቀመጠ ስሌት ነው።በሰኔ ወር 2005 ዓም በወጣ የስታትስቲክስ ዘገባ  ከአሜሪካ ሕዝብ  54 በመቶው በላይ የቡና ሱሰኛ መሆኑን መዘገቡ እና አሜሪካ ቡና ከውጭ ለማስገባት በዓመት የምታወጣው የገንዘብ መጠን ከ 4 ቢልዮን ዶላር የማያንስ መሆኑን የሚገልፀው ጥናት በራሱ የቡናን ተፅኖ የመፍጠር አቅሙን በአግባቡ የሚያመላክት ነው። http://www.statisticbrain.com/coffee-drinking-statistics/



ኢትዮጵያውያን ምን ነካን?



ቡና ከኢትዮጵያ የመገኘቱ ያማያሻማ ማስረጃ የመጠቀሱን ያህል፣የኢትዮጵያ ቡና ቃና እና ጣዕም ልዩ እና የተወደደ የመሆኑን ያህል እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ልዩ የቡና አፈላል ባህል ባለቤት መሆኑ ሀገራችንን በጎ ጎን የምናስተዋውቅበት ልዩ ወርቃማ ዕድል ነው።ለእዚህ ደግሞ አይነተኛ አጋጣሚው  የእዚህ አይነቱ የዓለምአቀፍ የቡና ቀን ነው።ኢትዮጵያ ይህንን ቀን በልዩ ዝግጅት ለምሳሌ


  •   ልዩ የሆነ የቡና ማፍላት ስርዓት ከመስቀል አደባባይ በማዘጋጀት እና በቀጥታ እንደ ስታርባክስ ያሉ ድርጅቶች ስፖንሰር እንዲያደርጉት እና ከፍተኛ የሚድያ ሽፋን በውጭ ሀገርም ደረጃ በማሰጠት ታዋቂ ማድረግ እና ሃገርን በማስተዋወቅ፣


  •  ቡና ከኢትዮጵያ መገኘቱ ላይ አፅንኦት ሰጥቶ ይህንን የሚያስተዋውቅ ጥናታዊ ፊልም ፣ዎርክ ሾፕ፣ወዘተ በማካሄድ ጉዳዩን በየዓመቱ ማንሳት እና ለቀረው ዓለም ማስተዋወቅ፣


  •  የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአንዲት ስኒ የምትሆን ትንሽ ተቆልታ የተፈጨች ቡና (ቡና ከኢትዮጵያ መገኘቱን የሚገልፅ ፅሁፍ ለጥፎ) በላስቲክ አሽጎ ለደንበኞቹ በመስጠት ቢያስተዋውቅ።የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓመት እስከ አንድ ሚልዮን ደንበኞች የማመላለሱን አቅም ስንመለከት በአንድ ዓመት ለስንት የዓለማችን ሰዎች ማስታወቅያው እንደሚዳረስ መገመት ይቻላል።


  •  በመጨረሻም ባለ ሁሉም ኮኮብ ሆቴሎች ከውጭ ለሚመጡ ደንበኞቻቸው ከሆቴሉ መግቢያ ላይ የቡና ማፍላት ስነ-ስርዓት እንዲኖራቸው እና ለደንበኞች ለቅምሻ ያህል በትንሹ ማቅመስ እንዲችሉ ማድረግ እና የቡናውን ጣዕምም ሆነ የቡና መገኛ ሀገር ኢትዮጵያን እንዲያስተዋውቁ ማድረግ  የመሳሰሉት ስራዎችን ጠንክሮ መስራት ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው።እዚህ ላይ ለሆቴሎች ወጪ መሸፈኛ መንግስት  ከሚቀበላቸው የገቢግብር ውስጥ  ከ0.05 ፐርሰንት በታች ለእዚሁ ተግባር ቢቀንስላቸው እና ስራው መሰራቱን መቆጣጠር ቢችል እንደሀገር የሚያመጣው ጥቅም እጅግ ላቅ ያለ በሆነ ነበር።ይህ ሥራ ከቱሪዝም እስከ ውጭ የሚገኙ ኢምባሲዎች ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ እና ከፍተኛ ብሔራዊ ጥቅም ያለው ትልቅ አጀንዳ ነው።አሜሪካ በእኛው ቡና እንዲህ የሕዝቧን ማህበራዊ፣ምጣኔ ሃብታዊ እና አእምሮአዊ  ደህንነትን ስትጠብቅ እኛ ለመልካም ገፅታ ግንባታ በተገቢው መልክ አለመስራታችን አሳዛኝ ነው።ለእዚህም ነው እኛ ኢትዮጵያውያን ምን ነካን? ለማለት የሚዳዳው።መልካም ዓለም አቀፍ የቡና ቀን።


አበቃሁ
ጌታቸው በቀለ
ኦስሎ




No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።