ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, September 16, 2013

የኤርትራ ጉዳይ በሶስት ትውልዶች ውስጥ(ልዩ የጉዳያችን ጡመራ ሪፖርታዥ)


የኤርትራው ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቅ እንደቀልድ እና እንደ እልህ የጀመሩት ''ኤርትራ ኢትዮጵያዊ አይደለችም'' ብሎም ''የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው'' አጀንዳን የሻብያ አጀንዳ እንዲሆን ካስደረጉ በኃላ ከእሳቸው በፊት የነበረው ትውልድ ባይቀበላቸውም የእሳቸውን ትውልድ ''የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው'' የሚለውን ገለፃ ለመንገር አላንገራገሩም።አቶ ኢሳያስ በአንድ ጎናቸው ተንቤን ትግራይ ቢወለዱም ያነሷት ጉዳይ ግን ኢትዮጵያን ለማዳከም ለዘመናት ከሚያልሙ አንዳንድ የአረብ ሀገራትም ሆነ ጎረቤት ሱዳንን የሚያማልል ብሎም ዳጎስ ያለ ድጎማ የሚያስገኝ የወቅቱ አዋጪ ''የገበያ ማስታወቅያ'' መሆኑን የተረዱት ይመስላሉ።

ቀዳማዊ አፄ ሃይለስላሴ ዩንቨርስቲ በነፃ ትምህርት ዕድል ይማሩ የነበሩት አቶ ኢሳያስ አፈወርቅ ''የኤርትራ ነፃነት ግንባር'' (ELF) ከመቀላቀላቸው በፊት በቻይና የፖለቲካ እና የወታደራዊ ስልጠና ለመውሰድ ተጉዘው እንደነበር ተወስቷል።አቶ ኢሳያስ እና ድርጅታቸው ከሰላሳ አመት ውግያ በኃላ ''ሁሉ ነገር ተፈፀመ!'' ብለው ተናግረው ሳይጨርሱ ሌላ ጦርነት ''በባድሜ መሬት ሰበብ'' እውነታው ግን የምጣኔ ሀብት የበላይነት ለመያዝ ከሕወሓትጋር በነበረ ግፍያ አዲስ ጦርነት ውስጥ ገብተው አስር ሺዎች ሲረግፉ አብረው ከአቶ መለስ ጋር ተዋናይ ሆነው ታዩ።ያ ''የቅኝ ግዛት ጥያቄ'' ያሉት ጉዳይ አስመራን ከያዙ በኃላም ጥያቄው ተወሳሰበባቸው።

አቶ ኢሳያስ እና ድርጅታቸው ሻብያ ስልጣን ከያዘ ሃያ ሁለት ዓመታትን አስቆጠረ።በእነኝህ ሃያ ሁለት ዓመታት ውስጥ የኤርትራ ተወላጆችሲነገራቸው የነበረው ''የአፍሪካ ታይዋን ትሆናለች'' ትንታኔ ሐሰት መሆኑን ተረዱት።ይልቁን ከአስመራ ዩንቨርስቲ ጀምሮ እስከ ቀድሞ በውሱን አቅም ይሰሩ የነበሩ ድርጅቶችን የገበያ ተወዳዳሪነት አቅም ተዳከመ።በአስር ሺዎች በሱዳን፣በኢትዮጵያ፣በየመን አድርገው ተሰደዱ።ኤርትራ ከዲፕሎማሲ እስከ አካባቢ ሃገራት ድረስ እንድትገለል አደረጉ።የአቶ ኢሳያስ ''የዓለም እይታ ፍልስፍና'' የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሆነ።እሳቸው አሜሪካንን የሚያዩበት እይታ የግል አስተያየት መሆኑ ቀረና የመንግስት ቃል አቀባይ የሚናገረው ''መዝሙረ-ኤርትራ'' ሆኖት አረፈው።አምባገነንነት አስደናቂው እና አዝናኝ ገፅታው ይሄው ነው።መሪው ሲያስነጥሰው ሁሉም ለመሳል ጉሮሮውን ይጠራርጋል።

''የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው'' የሚለው የአቶ ኢሳያስ ትውልድ ጥያቄ ዛሬም ፈተና ላይ ነው።

አቶ ኢሳያስ እና ትውልዳቸው የወቅቱ ገበያን ስሌት ያደረገው ''የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው'' አሁን በተነሳው ትውልድ የሚሞገትበት ጊዜ እሩቅ የሚመሰለው ካለ በሃሳቡ የመቀጠል መብቱን አከብራለሁ።ለእኔ ግን ይህ ጥያቄ በእራሱ የሚሞገትበት ጊዜ እንደሚመጣ አስባለሁ።የማኅበራዊ ትምህርት ሳይንስ ለምሳሌ የፖለቲካ ሳይንስ እንደ ኬሚስትሪ እና ባዮሎጂ በቤተ-ሙከራ(ላብራቶሪ) ጥናት ውጤቱን ከወዲሁ ለመወሰን አይቻልም።የሚቻለው ነገር ካለፉት፣አሁን ካለው እና መጪውን ከመተለም አንፃር በምክንያታዊ አቀራረብ ከወዲሁ ሁኔታዎችን መመልከት ነው።ከእዚህ አንፃር የኤርትራ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ሶስተኛው ትውልድ ላይ የወደቀ የእዚህ የሶስተኛው ትውልድ ጥያቄም በእርሱ ታሪካዊ ሂደት የሚፈነዳበት ሁኔታ ይኖራል።የሶስቱ በኤርትራ ጉዳይ የተሳተፉ ትውልዶች ጥያቄዎች እንደዘመናቱ ''የፖለቲካ ገበያ አዋጭነት'' እንደ አቶ ኢሳያስ ያሉ ተዋናዮች ተጫውተውበታል።ጥያቄው የሶስተኛውንም ትውልድ ጥያቄ አሁንም ''የፖለቲካ ገበያውን'' ተመልክተው ጥያቄውን በመሞረድ የአቶ ኢሳያስ ቡድን ሊመራው ይችላል ወይ? የሚለው ጥያቄ ፈታኝ ነው።መልሱ አይመስልም ነው።

ሶስቱ በኤርትራ ጉዳይ ላይ የነበሩ ትውልዶች

 1/ የመጀመርያው ትውልድ


የመጀመርያው ከአቶ ኢሳያስ በፊት የነበሩት የጣልያን እና የእንግሊዝን ቅኝ ግዛት ግፍ የሚያውቁቱ ሲሆኑ ይህ ትውልድ ከ 1900 ጀምሮ እስከ 1960ዎቹ የነበረ ትውልድ ነው።በእዚህ ዘመን ውስጥ ኤርትራ መከራ ፍዳ በቅኝ ገዢዎች ማየቷን በአይን የተመለከቱ፣የምስራቅ አፍሪካን ብቻ ሳይሆን እንደህልም የሚያልሟት እና የሚወዷት ኢትዮጵያ ክፉ እንዳይነካት እንደ አይን ብሌን  የሚሳሱላት ትውልድ ነበሩ።ይህ ትውልድ በግድም ይሁን በውድ በጣልያን የባንዳ ሰራዊት ውስጥ ገብቶ እስከ ሊብያ እና ኢትዮጵያ የዘመተ ቢሆንም ''ኢትዮጵያ ሀገሬን ቅኝ ገዢ አይዛትም'' ብሎ እንደ አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶምን አፍርቶ ግራዝያንን ያቆሰለ ትውልድ ነው።የኢጣልያ ስብከት  አላማው እና ግቡን ስለተረዳ ኢትዮጵያ እናት ሀገሬ አይደለችም የሚል አስተሳሰብ ማሰብ በራሱ አለማወቅ ብቻ ሳይሆን እራስን መካድ መሆኑን ጠንቅቆ የተረዳ ትውልድ ነው።

ጣልያን ኤርትራን በያዘችበት ጊዜ በአስመራ ከተማ ውስጥ 
- ለነጮች የተከለሉ ምግብ ቤቶች እንደ አሸን መብዛታቸውን ፣
- ከምሽቱ 11 ጀምሮ አንድም ኤርትራዊ በአስመራ ጎዳና እንዳይዘዋወር (ጣልያን እና ነጮች ብቻ የተፈቀደ ስለነበር) መታገዱን፣
- በአውቶቡስ ውስጥ ሲሄድ ኤርትራውያን ከነጮች ጋር እንዳይቀላቀሉ በመጋረጃ እንዲከለል ተደርጎ እንደ ዕቃ ይሄድ የነበረ መሆኑን፣
- እስላሙ እና ክርስቲያኑ እንዲጋደል የእስላም ቤት ከውጭ የቀይ ምልክት የክርስቲያን ቤት በነጭ ቀለም እንዲቀለም  መድረጉን ወዘተ ያውቃል።
መላከ ሰላም ዲመጥሮስ ገ/ማርያም (ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትዋሃድ እጅጉን ከገፉት የመጀመርያው ትውልድ የኤርትራ ተወላጅ) 

ይህ ትውልድ የቀንም ሆነ የማታ ሕልሙ እናት ሃገሩ ኢትዮጵያን ማየት ነበር።ለእዚህም ነበር ብዙ ሺዎች በሁመራ -ጎንደር እያደረጉ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት እና በንግድም ሆነ በከፍተኛ የመንግስት ስልጣን ሳይቀር ቦታ እያገኙ የመጡት።ይህ ትውልድ ነበር ''ኢትዮጵያ ወይንም ሞት!'' ብሎ ''የሀገር ፍቅር ማኅበር'' መስርቶ የንጉሡ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ ሆኑ ንጉሡ ሲያመነቱበት የነበረውን የተባበሩት መንግስታትን የፌድሬሽን ጥምረት ውሳኔ ከክህደት ቆጥሮ ንጉሱን መቆምያ መቀመጫ አሳጥቶ ወደ ውህደት የመራው።አምባሳደር ዘውዴ ረታ ስለነበረው ትውልድ ሲናገሩ ''ኢትዮጵያ ኤርትራ እንድትዋሃድ ለማድረግ ሞከረች ከሚለው ይልቅ ኤርትራውያን ውህደቱን አለመፈፀም በእራሱ ትልቅ ክህደት እንደተፈፀመ ከመቁጠራቸውም በላይ ኤርትራውያን በእራሳቸው ጥያቄ ውህደቱን ከመነሻው እስከመጨረሻው ድረስ በሁለት እግሩ አስኬዱት ማለት ይቀላል።እኔ በወቅቱ ምስክር ስለነበርኩ'' ያሉት።

ሁለተኛው ትውልድ


አቶ ኢሳያስ አፈወርቅ

ይህ ትውልድ ከ 1960ዎቹ እስከ 1990 ያለው ትውልድ ነው።ይህ ወቅት የሶሻልስቱ አብዮት፣ወታደራዊ ደርግ፣የኢትዮጵያ የለውጥ ማዕበል በተለያዩ ኃይሎች እጅ በመከፋፈሉ እና እንደ ድርጅትም ''ሻብያ'' ጎልቶ ከመውጣቱ አንፃር የኤርትራ ጉዳይ በተወሰኑ መሳርያ በያዙ ኃይሎች እጅ ወደቀ።ሌላው ቀርቶ የቆላው የኤርትራ ሕዝብ ጥያቄ የሚሰማው ከማጣቱም በላይ ተወካዮቹ ወደ ደርግ መጥተው አቤት ለማለት ተገደዱ።የእዚህ ትውልድ ጥያቄ ከቀይሽብር መከራ ጋር ተዳምሮ ''ነፃነት!ነፃነት!መብት!'' የሚሉትን ጥያቄዎች ሁሉ ከመለየት እና የእራስን መንግስት ከማቆም ጋር ተዛመደ።አምባገነንነትን መዋጋት የእራስ ሀገር ከመመስረት ጋር ያለው ተዛምዶ እና ቅራኔን የሚፈታ ጠፋ።የወቅቱ የብሔር ብሄረሰቦች ጥያቄ ማሰርያ ውሉ ጠፍቶ መገንጠልን መድረሻው ሲያደርገው የሚጠይቅ ጠፋ።ጉዳዩ ያሳሰባቸው የመጀመርያው ትውልድ አባላት የሚሰማቸው ጠፋ።ይልቁንም በዘመነ ደርግ  የተከበሩ የደጋው ሃማሴን እና  የኤርትራ ቆላ ተወላጅ  አባቶች በተለይ  ''የሀገር ፍቅር ማኅበር'' አባላት እና መስራቾችም ጭምር 'የኤርትራ እና የኢትዮጵያን አንድ ሕዝብ መሆን አትናገሩ' ተብለው ድብደባ፣ዛቻ አንዳንዶቹም እስካሁን በሻብያ ወኪሎች እንደሆነ በሚታሰብ መልኩ ቤታቸው መግብያ ላይ የጥይት አረር ሆኑ።

ይህንን እውነታ ወደፊት ታሪክ በሚገባ ይዘክረዋል።የሁለተኛው ትውልድ መነጋገርያ ውይይት፣መግባባት እና ሃሳብን መግለፅ ሳይሆን ''ቀና ብሎ ያየህን በጥይት አረር ድፋው'' መሰል የወረደ አስተሳሰብ ነውና ብዙዎች ደርግ እራሱ ሊታደጋቸው አለመቻሉን ሲመለከቱ ወደተለያዩ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ሃገራት ተሰደዱ።ዘመንን ዘመን ተካውና የአቶ ኢሳያስ ትውልድ በ 1983 ዓም ከሰላሳ ዓመት ጦርነት በኃላ አስመራ ሲገባ ሁኔታው አዲስ ምዕራፍ ያዘ።

ትንሽ ቆይቶ ግን ነገሮች ተቀየሩ።በመጀመርያ በኤርትራ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን፣ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣እና ኤርትራውያንን ያገቡ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የያዙትን ንብረት ትተው ወደ ኢትዮጵያ እንዲሄዱ ተደረጉ።በመጀመርያ ጊዜ የነበረው አወጣጥ በተለይ ህወሃትም በወዳጅነት ላይ ስለነበር የተፈናቃዮቹን መከራ የሚያደምጥ ጠፍቶ በአዲስ አበባ የሚታተሙ የግል ጋዜጦች ብቻ የምስኪን ስደተኞች ችግር ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስተጋቡ ብቸኛ ጠበቃዎች ሆኑ። ውሎ አድሮ ግን ሻብያ እራሱ ከህወሓት ጋር አዲስ ፍጥጫ ውስጥ ገባ።በለስ ቀንቷቸው አዲስ አበባ የገቡቱ ተፈናቃዮች በሳሪስ ቃሊቲ አካባቢ በድንክዋን ሆነው ቀይ መስቀል ይጎበኛቸው ገባ።ይህ በሆነ በሰባተኛው ዓመት ብዙም ስለ ጀት ማብረር ችሎታ የሌላቸው የአቶ ኢሳያስ አይሮፕላን አብራሪዎች ትግራይ ውስጥ ትምህርት ቤቶችን በቦንብ ደበደቡ።ሕፃናት በትምህርት ገብታ ላይ ሳሉ ተቀጠፉ።

ከጥቂት ወራት በኃላ የበቀል እርምጃው ቀጠለከሰባ ሺህ በላይ የሚሆኑ ቀኝ እና ግራ እጃቸውን ያልለዩ ሕፃናትን ጨምሮ በኢትዮጵያ ይኖሩ የነበሩ ትውልደ ኤርትራውያንን ህወሓት በማባረሩ ኢትዮጵያውያንን አሳዘነ።ብዙዎቹ ለዘመናት ያፈሩትን ንብረት በአንዲት ጀንበር ሲነጠቁ አነቡ።ከቤት ወጥተው የማያውቁ ልጆች በአውቶቡስ እየተጫኑ በትግራይ በኩል ደቡብ ኤርትራ ላይ ተወረወሩ።ምናልባት የሁለተኛው ትውልድ (የአቶ ኢሳያስ ትውልድ) የመጀመርያው ትውልድ ሲናገረገው የነበረውን ሁሉ ማሰብ የጀመረው በእዚህ ወቅት ይሆናል።የሆነው ሆኖ ይህ ወቅት ''መንግሥታት'' ተብለው የሚጠሩ ሁለት አካላት አስመራ እና አዲስ አበባ ላይ ሆነው በከረመ የመለያየት ፖለቲካቸው ሕዝብን ስያሰድዱት ተስተዋሉ።የሁለተኛው ትውልድ አባዜ በእዚህ አላበቃም በሻብያ እና በህወሓት መካከል የነበረውን የቆየ ቁርሾ ''ወደ ሀገር አጀንዳነት'' ተቀየረ እና ሁለቱም የህዝብን ስሜት እየኮረኮሩ በባድማ መሬት ስም ውግያ ገጠሙ።በውግያው የኢትዮጵያ ሰራዊት ገፍቶ  አስመራ ሊገባ ሰዓታት ቀሩት።በውቅቱ የኢትዮጵያ መንግስት ቃል አቀባይ የነበሩት ወይዘሮ ሶሎሜ በአሜሪካዊ እንግሊዝኛ በተቃኘ ንግግራቸው ለቢቢሲ ''ፎከስ ኦን አፍሪካ'' ፕሮግራም ''we gave them our lesson'' ''ዋጋቸውን ሰጠናቸው'' አሉ።ይህ ሁሉ ሲሆን ግን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሁለቱም ወገን የአፈር ሲሳይ ሆነው ነበር።

ሶስተኛው ትውልድ


በኤርትራ ጉዳይ የሶስተኛው ትውልድ ታሪክ የሚጀምረው ከ 1992ቱ የባድሜ ውግያ በኃላ ነው። ኢትዮጵያ እናቴ! ያለው የመጀመርያው ትውልድ አለፈ። ''የኤርትራ ጉዳይ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው'' ያለውም ሁለተኛው ትውልድ ብሎት ብሎት ደከመው። በመጀመርያ ኤርትራን በሀገርነት በማወጅ (በኤርትራ በኩል) እንዲያውጅ በማገዝ (በአቶ መለስ በኩል) ተፈፅሟል።ሺዎች ኢትዮጵያ ነክ ናችሁ ተብለው ከኤርትራ ተባረዋል።ሌሎች ሺዎች ኤርትራ ነክ ናችሁ ተብለው ከኢትዮጵያ ተግዘዋል።በድንበር ሰበብ ብዙ አስር ሺዎች አልቀዋል።ሁለተኛው ትውልድ ደከመው።ከእዚህ ሁሉ በኃላ የመጀመርያው ትውልድ የመከረውን የፍቅር ጥሪ እያሰበ ሳለ ሶስተኛው ትውልድ ተነሳ።
ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ከባለቤቱ ጋር 

ሶስተኛው ትውልድ በተለይ ሁለተኛው ትውልድን የሚያደንቀው በጠበንጃ አያያዙ ካልሆነ በቀር ልማት እና እድገትን ሲያመጣ ማየት አልቻለም።ይልቁን ይህ ትውልድ በመረጃ ዘመን እንደመኖሩ ታሪክ ሲነገረው በደቂቃዎች ውስጥ የተባለው ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ ስለሚችል በአራዳ አነጋገር ''የማይሸወድ'' ሆነ።ከሁሉም በላይ አቶ ኢሳያስ ቀደም ብለው ያነሱት ''የኤርትራ ጉዳይ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው'' አባባል ውላ አድራ በእዚህ በሶስተኛው ትውልድ ከባድ ፈተና ገጠማት።
  • ''ኤርትራ ቅኝ ግዛት ተይዛ የነበረው በኢጣልያ እና በሞግዝቷ እንግሊዝ ነው እንጂ በኢትዮጵያ መች ሆኖ ያውቃል?'' የሶስተኛው ትውልድ ጥያቄ ቀጠለ...
  • ''በደል እና ጭቆና ቢኖርም ይህ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ላይ የመጣ መከራ አይደለም ወይ?''
  • ''የኃይለስላሴ አስተዳደርም ሆነ የደርግ ቀይሽብር በአስመራ ላይ በተለየ ተደረገ ወይስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የቀመሰው ገፈት ነበር?''
  • ''ይህ የሚያሳየው የአቶ ኢሳያስ ትግል መሆን የነበረበት ከደርግ አምባገነንነት እና ከንጉሡ ፍፁም ዘውዳዊ ስርዓት ለመላቀቅ ብሎም ስልጣንን ከማዕከላዊ መንግስት ለመንጠቅ መሆን የለበትም ነበር ወይ?'' ወዘተ ጥያቄዎች አቶ ኢሳያስ እንዲመልሱለት ሶስተኛው ትውልድ የሚጠይቃቸው ናቸው።

ሶስተኛው ትውልድ ድንበር ከድንበር ቢዘጋበት በመከራ ላይ ሆኖ በስደት ሲገናኝ የሁለተኛውን ትውልድ ሥራ ማብሰልሰሉ አልቀረም።ጊዜ፣ቦታ እና አጋጣሚ ሲገጥመው ግን የአቶ ኢሳያስ ''የቅኝ ግዛት ጥያቄ'' ብለው የሰሩት ዶሴን ይዘት እራሳቸውን አቶ ኢሳያስን ይጠይቅበታል።
የሶስተኛው ትውልድ ጥያቄ አልቆመም..
  •  ''ከኢጣልያን የዘር መድሎ የተላበሰ አገዛዝ ከእንግሊዝ ከሞግዝትነት ባለፈ ሌላ ቅኝ ገዢ ለመሆን ታደርገው ከነበረው ዝግጅት ኤርትራ የዳነቸው ከኢትዮጵያ ጋር በፌድሬሽን ከተቀላቀለች በኃላ አይደለም ወይ?''
  • '' አስመራ በነፃነት ከ 11 ሰዓት በኃላ መሄድ የተቻለው፣የፈለጉበት ምግቤት (የነጮች የጥቁሮች)ሳይባል መመገብ የተቻለው ከፌድሬሽን በኃላ አይደለም ወይ?''
  •  ''በአስመራ መንገድ ላይ በእግር ለመሄድ 'ነጮች በሚሄዱበት መንገድ ላይ መሄድ አይቻልም' ተብሎ ለጥቁር በተከለለ መንገድ ላይ ብቻ ይሄድ የነበረው ኤርትራዊ በነፃነት በሁሉም የእግር መንገድ ላይ በዜግነቱ ኮርቶ መሄድ የቻለው ከፌድሬሽን በኃላ አደለም ወይ?''
  • ኢጣልያ ለኤርትራ ተወላጆች ትምህርት እስከ አራተኛ ክፍል ብቻ እንዲሆን መወሰኗ ያቆመው እና ኤርትራውያን የትምህርት ዕድል እስከፈለጉት ክፍል ድረስ መግፋት የቻሉት ከፌድሬሽን በኃላ አይደለም ወይ?
  • ''ለመሆኑ  በኤርትራ የተወለደው ኢትዮጵያ ከተወለደው በምን ተለያየ?  በንግግር? ወይንስ በመልክ? በአመጋገብ?ወይንስ በሃይማኖት በምን ተለያይቶ ነው የዲሞክራሲ፣የመብት እና የስልጣን ጥያቄ ''የቅኝ ግዛት ጥያቄ'' የተባለው? የሶስተኛው ትውልድ ጥያቄ ይቀጥላል።


አበቃሁ
ጌታችው በቀለ
ኦስሎ  

3 comments:

Anonymous said...

u r very analytical person. I and my friend are keeping admiring your way of presentation. please please keep in sharing your ideas.

Anonymous said...

Betam arif nw gin ye hahunu Ertrawi ye Ethiopa widket yemimegn ena mengedun biyagegn liyatfan endemifelg masawek albh
Beteley Europe lay yalu betam zeregnoch lenegeru Ethiopia wist yalutim bet leytew nw miznanut

Anonymous said...

Yemiyasaznew ye hahunu mengstachewim 10 kifil belay almefkedu
Dedeb aderegachew ye Ethiopia hizb bastemare babela tiru besera lemin telat yihonbetal lemin kifu yiserubetal ke zega belay mengstachin eyanorachew lemn endi aynet kifat behizb lay

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።