President Barack Obama meets with Members of Congress to discuss Syria in the Cabinet Room of the White House, Sept. 3, 2013. (Official White House Photo by Pete Souza)
ፕሬዝዳንት ኦባማ በዋይትሐውስ የካቢኔ መሰብሰብያ አዳራሽ ውስጥ ከምክርቤት አባላት ጋር ሲወያዩ (ማክሰኞ ነሐሴ 28/2005 ዓም ፎቶ በፔተ ሳኡዛ )
አሜሪካ በተናጥል በሶርያ ላይ ጥቃት የመፈፀሟ ግምት እያደገ ነው።ከምክርቤቱ ስብሰባ በኃላም ጉዳዩን በቀላሉ ማጣጣል አልተቻለም።ፈረንሳይ ጥቃቱን ብትደግፍም ብቻዬን ግን አይሆንም ብላለች።ቢያንስ የአሜሪካ ከጎኗ መቆም አስፈላጊ ነው እያለች ነው።የሶርያው በሽር አል-አሳድ ወደመጨረሻ ደረጃ ላይ ሲደርሱ ያለ የሌለ ኃይላቸውን (በተለይ በአለም በኬሚካል የጦር መሳርያ ምርት ቀደምት የሆነችውን ሀገራቸውን) በእስራኤል ላይ ሊያሳዩ ይችላሉ ተብሎ ተፍርቷል።እስራኤል ለዜጎቿ የፊት መሸፈኛ ጭንብል ማደል ከጀመረች ሳምንታት ተቆጥረዋል። ኦባማ ፈለጉት አልፈለጉትም አሜሪካ እያለች የአይሁዳውቷ ሀገር ጥቃት ማየት የማይችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።
የእንግሊዝ ፓርላማ በጉዳዩ ላይ አሉታዊ ድምፅ ቢሰጥም ከመስከረም 5 እስከ 6/2013 እኤአ በሩስያ ዋና ከተማ ቅዱስ ፔተርስፐርግ (St. Petersburg) ከተማ የሚደረገው የቡድን 20 ሀገሮች ስብሰባ ላይ የአሜሪካ እና የሩስያ ፍጥጫ በሶርያ ጉዳይ ላይ ጎልቶ የመውጣት ዕድል እንዳለው ይገመታል።ከእዚህ በተለየ ግን አሜሪካ እንደተገመተው ጥቃት ከፈፀመች እና ጦርነቱ በአጭሩ ከማለቅ ይልቅ የአካባቢውን ሀገሮች በረጅም ጊዜ ወገን እንዲይዙ ወደመምራት ከሄደ ለአፍሪካ ቀንድም የራሱ የሆነ አጀንዳ ይዞ ሊመጣ ይችላል።
ጦርነቱን በአሜሪካ ዘመቻ ቢጀመር በአጭር ጊዜ ላለመጠናቀቁ አንዱ እና አይነተኛ አመላካች ጉዳይ በአሜሪካ በትጥቅ እና ስንቅ የተደገፉት የባሽር ተቀናቃኞች እራሳቸው የዘመቻ-አሜሪካንን መጀመር ፈፅመው እንደማይቀበሉ እያሳወቁ መሆኑ ነው።ለሁሉም ግን ጉዳዩ ከአንድመቶ አስር ሺህ በላይ ሶርያውያን ከሞቱ በኃላ የአሜሪካ የዘመቻ ጉሰማ አለምአቀፉ ሕብረተሰብን ለማፅናናት ይሁን ወይንስ ከምር አይሁዳውቷን ሀገር ለመከላከል መሆኑ ከሰሞኑ የሚታዩ ክስተቶች ግልፅ ያደርጉልናል።
በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ ድልድይ አንደመሆኗ እሳቱ እሩቅ ነው በሚል ቅኝት ብቻ ማለፍ አይቻልም። እንደዛ ከታሰበ በኩሬ ውስጥ ሆና እሳት ሲነሳ የሳቀችው እንቁራሪትን መርሳት ነው። ይችው እንቁራሪት ማዶ በሚነደው እሳት ስትስቅ በመጨረሻ እሳቱን ለማጥፋት ውሃ ሲቀዱ ከባሊው ውስጥ ጨምረዋት ወደ እሳቱ እንደከተቷት ማሰብ ይገባል።ለማለት የፈለኩት ጉዳዩ በቀጥታ ባይነካንም ጦርነቱ ከረዘመ ግን የእራሱ የሆነ አዲስ አጀንዳ እና የኃይል አሰላለፍ ይዞ አይመጣም ማለት አይቻልም ነው።እዚህ ላይ ነፍሳቸውን ይማረው እና ደራሲ እና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህን ማሰብ ይገባል።ጋሽ ማሞ በተለይ ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር የተያያዙ ታሪኮችን በትርጉም ባስነበቡን መፃህፍቶቻቸው ለምሳሌ ''የካይሮ ጆሮ ጠቢ''፣ የእኛ ሰው በደማስቆ'' መግቢያ ላይ መፅሃፎቹን ለመተርጎም ምን እንዳነሳሳቸው የሚያሰምሩበት ነጥብ አንድ እና አንድ ነው። ይሄውም መካከለኛው ምስራቅ ውስጥ የሚነሱ ጉዳዮች በሙሉ ኢትዮጵያን በታሪክም ሆነ በወቅታዊ ክስተቶች ሁሉ ይነካታል የሚል ነው።
መልካም አዲስ አመት
ጌታቸው
ኦስሎ
No comments:
Post a Comment