ኢትዮጵያ ያለችበትን ቁልፍ አቀማመጥ ብቻ ሳይሆን ከሱዳን እስከ ጂቡቲ ከየመን እስከ ሳውዲ ያለው በረሃማ መሬት ጋር ሲነፃፀር ምድረ ገነት ነው።እነኝህ በደረቃማ መሬት ላይ ተፈጥሮ ያሰፈረቻቸው አንዳንድ መንግሥታት የአሁኑም ሆነ መጪው ትውልዳቸውን የሚያጠጡትን ውሃ ለማግኘት ዙርያቸውን ሲያማትሩ ዓይናቸውን የጣሉት ኢትዮጵያ ላይ ነው።ከእነኝህ አማታሪዎች ውስጥ የመካከለኛው ምስራቅ ጋዜጦች እንደ ''አል-አረቢያ'' ያሉት ጋዜጦች የኢትዮጵያን ዓባይ ወንዝ ''የአረቡ ዓለም ወንዝ'' እያሉ ሲፅፉ ትንሽም 'ስቅ!' አላላቸውም።ይሄው ጋዜጣ ባሳለፍነው ክረምት ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ መገደቧ የአረቡን ዓለም ለመቆጣጠር ነው እና የአረብ ሀገሮች በሙሉ ሊነሱ ይገባል ሲሉ የአረብ ሊግ ቁንጮ መናገራቸውንም አስነብቦናል።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ፍላጎት ግልጥ ነው።ኢትዮጵያ እንድትነሳ አለመፈለግ ብቻ ሳይሆን ከፋፍለው ሊቆጣጠሯት እያለሙ ይቃዣሉ።ይህንን ህልማቸውን ደግሞ ኢትዮጵያ የውስጥ ሁከት የገባች በመሰላቸው ጊዜ ሁሉ እና የዓለምም ሆነ የመካከለኛው ምስራቅ ትኩረት በተደናበረበት ጊዜ ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ያልሞከሩበት ጊዜ የለም።የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በመግባት ቢያንስ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ ብቻ በርካታ ሴራዎችን አሴረዋል። የኢትዮጵያ እና የኤርትራም ሆነ የህወሓት 17 ዓመታት ጦርነት ብንመለከት ከገንዘብ እስከ ቁሳቁስ ከፍተኛ ድጋፍ ያገኝ የነበረው ከመካከለኛው ምስራቅ እና ሱዳን መንግሥታት ነበር።ለእዚህም ነው ''የኤርትራ ጉዳይ'' የተሰኘው መፅሐፍ ፀሐፊ ክቡር አምባሳደር ዘውዴ ረታ ''የኤርትራን ጉዳይ እግሩ ኢትዮጵያ ይሁን እንጂ ራሱ ያለው ውጪ ነው'' ያሉት።ዛሬ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መቀራረብ ያስደነገጣቸው የኢትዮጵያ የቅርብም ሆኑ የሩቅ ጠላቶች ዋና ስጋት ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር የመውጣት ሂደት እና ይህንኑ ባሕርም ሆነ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት የመቆጣጠር ህልማቸው ከንቱ እንደሚሆን ከወዲሁ ስላወቁ አርበትብቷቸዋል።
በሌላ በኩል የአፍሪካ የተፈጥሮ ሐብት መተዳደሪያቸው የሆኑ አደጉ የሚባሉ ሐገሮች የኢትዮጵያ መነሳት እንደ እነርሱ አባባል ''መንሰራራት'' እንደ አንድ ስጋት ይመለከቱታል።ይህ ደግሞ ከሁለት ምክንያቶች ይመነጫል።አንዱ፣ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ምሳሌ ሆና ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች እጅ አዙር ቅኝ አገዛዝን ለማንኮታኮት እንዳይነሱ ሲሆን።ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ ካላቸው የተፈጥሮ ሀብት፣ማዕድናት እና ጅኦ-ፖለቲካዊ ስልት አንፃር የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ወታደራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች ሁሉ በእጅ አዙር ለመዘወር ከመፈለጋቸው የተነሳ ነው።ለእዚህም ነው ኢትዮጵያን ለሃያ ሰባት ዓመታት በጎሳ ከፋፍሎ እርስ በእርስ ሲያናክስ አንዳች ያልተናገሩ መንግሥታትም ሆኑ የውጭ መገናኛ ብዙሃን፣የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሚያስደንቅ ፍጥነት ካስወገደው በኃላ ታላቅ ድንጋጤ እንደፈጠረባቸው መደበቅ አልቻሉም።
ይሄውም የስልት መወናበድ እና መደናበር ስለፈጠረባቸው የሚይዙትን እና የሚጨብጡትን አሳጥቷቸው ሲወዛገቡ ታዝበናል።በእዚህም ምክንያት የግፈኛው የቀድሞው ህወሓት ደጋፊዎችም ሆኑ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች አሁን ያላቸው ብቸኛ እና ቀሪ አቅም የሐሰት ወሬ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ማሰራጨት ሆኗል።በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የሐሰት ዜና የማሰራጨቱን ሥራ እየሰሩ ያሉት ደግሞ በዓለም ላይ ስም አላቸው የሚባሉ ዓለም አቀፍ የዜና ማሰራጫዎች ጭምር እጅግ በሚያሳፍር ሁኔታ ከእውነት የራቁ ዜናዎች ሲያሰራጩ ሰንብተዋል።በእነኝህ የዜና ስርጭቶች ዙርያ የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች የዜናዎቹን ሐሰትነት በሚያጋልጥ መንገድ የጥናት ፅሁፎቻቸውን ማቅረብ አለባቸው። ይህ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የሐሰት ዜና ኢትዮጵያን የመክበብ ቁጥር አንድ ሙከራ መሆኑን ማወቅ ይገባል።
ሁለተኛው ኢትዮጵያን የመክበብ ግብ ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ክልል የገባው የሱዳን ሰራዊት ነው።ሱዳን በቅርቡ በተጣደፈ መልኩ የትራምፕ አስተዳደር በሀገሪቱ ላይ ተጥሎ የነበረውን የዕቀባ መጣል ማንሳቷ ይታወሳል።ይህንን ተከትሎ ከአሜሪካ የገንዘብ ድርጅት ብድር ማግኘቷ እና ከግብፅ ደግሞ የአይዞሽ ባይ ምልክት መታየቱ ነው።ይህ በሱዳን በኩል የታየው ኢትዮጵያን የመክበብ ተግባር መልኩን ቀይሮ ነገ ከኢትዮጵያ ምሥራቅም ሆነ ምዕራብ በሌሎች ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር የሚናበቡ ኃይሎች ተመሳሳይ ከበባ አያደርጉም ብሎ አለማሰብ አይቻልም።ይህ በእንዲህ እያለ የከበባዎቹ ዋና ኃይል አድርገው የሚወስዱት የኢትዮጵያን ውስጣዊ ሰላም ማተራመስ ነው።ኢትዮጵያን ለማተራመስ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ስደተኞችን ሳይቀር ለመጠቀም የኢትዮጵያ ጠላቶች ማቀዳቸው አይቀርም።ኢትዮጵያ ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ወደ ሃያ የሚሆኑ ሀገራት ስደተኞች መጠጊያ ናት።ስደተኞቹ በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍል ስደተኛ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ የህክምና ችግር ፣ ከነበሩበት ሀገር በተለያዩ ጦርነቶች አልፈው ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸው ለአዕምሮ ህመም የተጋለጡ እንዲሁም ጥበቃ የሚያስፈልጋቸውም በከተማ ስደተኝነት ተመዝግበው አዲስ አበባ ይኖራሉ።
ለማጠቃለል ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን የከበባ ሙከራ ለመስበር መንቀሳቀስ አለባቸው።የመጀመርያው የከበባ ሙከራ በዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን የተፈፀመ ነው።ይህንን የሐሰት ዜና በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የሚዘሩትን ምሑራን ባገኙት ቀዳዳ ሁሉ ተጠቅመው ምላሽ መስጠት ብቻ ሳይሆን የሕግ ማስከበር ሂደቱ ባይካሄድ ኖሮ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የምስራቅ አፍሪካን በከፍተኛ ደረጃ ሊያበጣብጥ የሚችል ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል የሚያስረዱ በርካታ ፅሁፎች፣ገለጣዎች እና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራዎች በሰፊው መስራት ያስፈልጋል።በእዚህ በኩል በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ምሑራን መፃፍ በሚገባቸው ያህል ፅፈዋል ማለት አይቻልም።ኢትዮጵያ ያስተማረቻቸው ልጆቿ ለእዚህ ጊዜ ካልሆኗት ለመቼ ሊሆኗት ነው? ኢትዮጵያ በሐሰት ወሬ ይህንን ያህል ከበባ ሲፈፀምባት እንዳላዩ ማየት የት የተማርነው ሙያ ይሆን? በጦር ኃይል በኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ወረራ የፈፀመው የሱዳን ሰራዊት የኢትዮጵያ ጦር ባልተጠበቀ ሰዓት እርምጃ እንደሚወስድበት ሳይታለም የተፈታ ነው። የሐሰት ወረራ የተከፈተባት ኢትዮጵያ ላይ የአፀፋ ምላሽ መስጠት ግን የእንግሊዝኛ ፊደል የቆጠረው ከሀገር ቤት እስከ ባሕር ማዶ የሚኖረው የኢትዮጵያ ምሑር ነው።ስለሆነም ምሑሩ ከትዊተር እስከ ዓለምቀፍ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ እየተፈፀመ ያለውን ከበባ እና የማዋከብ ተግባር ሰብሮ ለመውጣት ለኢትዮጵያ የሚቆምበት ጊዜ አሁን ነው።ኢትዮጵያ ግን ዛሬም ትጣራለች ምሑሩ የት ነው?
==========////==============
============
ማስታወቂያ
============
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ?
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ -
No comments:
Post a Comment