ወንጪ ሐይቅ (Photo =viator.com)
ጌታቸው በቀለ
================
ጊዜው የዛሬ 14 ዓመታት ገደማ ነው።በተለያየ ጊዜ ጎርጎራ እና ወንጪን ለማየት ዕድል ገጥሞኝ ነበር።ወንጪን ሁለት ጊዜ ነው የማየት ዕድሉን ያገኘሁት።ሁለቱም ጉዞዎች በቡድን ከሃምሳ ሰው ያላነሰ መንገደኛ ጋር ነበር ጉዞው።
የጎርጎራ 'መቃጠሌ'
ጎርጎራን ከማየቴ በፊት የጣና ገዳማትን ቀደም ብሎ መነሻ ከባህርዳር እያደረግን መዳረሻችንን ባህርዳር እያደረግን ካደረግነው ጉዞ ውስጥ አንዱ ጉዞ እኔ ጣና ቂርቆስን እና ዳጋ እስትፋኖስን አይቶ ጎርጎራ ወጥቶ ማደር የተያዘ መርሃግብር ነበር።ጎርጎራ ከአዲስ አበባ ሰሜን ምዕራብ 705 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።ጎርጎራ ከሐይቁ ዳር ላይ የቀድሞ ባሕር ኃይል (ስሙን ካልተሳሳትኩ) ክበብ የሆነ የተወሰኑ ምግብ እና መጠጥ መስተንግዶ ያለው እና ማደርያ ክፍሎችም ነበሩት።በእዚህ የጎርጎራ ክበብ ለሕዝቡ መስተንግዶ የሚሰጥ ይሁን እንጂ የረባ የምግብ መስተንግዶ አለመኖር ብቻ ሳይሆን የግቢው አያያዝ የቤቶቹ አለመታደስ ስመለከት እጅግ ተናድጄ ነበር።
በአንድ ቀን የጎርጎራ አዳራችን መንገደኞቹ ሁሉ ወሬያችን ይህ ሆኖ አመሸ።አንዱ ለምን ክበቡን ለግለሰብ ኮንትራት አይሰጡትም? እንዴት ይህን የመሰለ ቦታ እንዲህ ይባክናል? እዚህ ውሃው ዳር ላይ መቀመጫ ቢኖረው፣እዛ ማዶው ላይ የጀልባ ማከራያ ቢሰራ፣ ምናለፋችሁ የቀረን የቢዝነስ ፕላኑን መፃፍ ነበር።የሚገርመው የሚጠጣ ለስላሳ እና ቢራ ነው አለቀ ተብለን በጋራ የያዝነው አገልግል ነበር እራታችን የነበረው።ከእዛን ጊዜ ጀምሮ ጎርጎራ ሲባል ስለቦታው ተፈጥሮ እያደነኩ ምንም አለመደረጉ ግን 'ሲያቃትለኝ ነበር የኖረው።ይህንን አንድ ቀን እፅፈዋለሁ እያልኩ አዘገየሁት።
ወንጪ 'ያቃጠለኝ'
ወደ ወንጪ የሄድነው የወንጪ ሐይቅን ተሻግሮ የሚገኘው የወንጪ ቅዱስ ቂርቆስን ለመሳለም ነበር።ወንጪ በወሊሶ አልፎ ከአዲስ አበባ 153 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ በመኪና አራት ሰዓት የሚፈጅ መንገድ ነው።ወደ ወንጪ ሐይቅ የሚወስደውን ገረጋንቲ መንገድ አውቶብሱ እኛን ይዞ ከሐይቁ አፋፍ ላይ ሲደርስ ቆመ ትንሽ በእግራችን እንደሄድን ቁልቁል ሀይቁ ዙርያውን ካለው ምድረ ገነት ከመሰለ ደን ጋር ብቅ ሲል እውነት ለመናገር ግድግዳ ላይ ስዕል የምመለከት ነበር የመሰለኝ።ወደ ሐይቁ ለመውረድ ትንሽ ተዳፋት መሬት አለው።ተዳፋቱን ወርዳችሁ የሀይቁን ዳር ትንሽ ከሄዱ በኃላ የአካባቢው ነዋሪዎች (ባብዛኛው ኦሮምኛ የሚናገሩ ናቸው) ሁሉም ግን አማርኛ ያውቃሉ።ትንንሽ ጀልባዎች እየቀዘፉ ሃይቁን እያሻገሩ ወደ ቅዱስ ቂርቆስ ያደርሳሉ።በግምት ከ60 የማያንሰው መንገደኛ እየከፋፈልን ጀልባው ላይ ማሳፈር ያዝን።
ወደ ሀይቁ በጀልባዎቹ ስንሄድ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር እያወራን ነበር።በመሃል ጀልባው ስር ድም የሚል ድምፅ ይሰማል።ጥያቄ ጠየቅን ምንድነው ከስር የሚጮህ የሚሰማው።ጀልባው መሬት ነካ እንዴ? ጠየቅን።መለሱ ዓሳ ነው።ከስር ሲያልፍ እየነካው ነው አሉን።ዓሳ ትሸጣላችሁ? ጥያቄ አስከትልን።መልሱ ዓሳ እንደማያጠምዱ ብዙም እንዳልተሰራበት አጫወቱን።በኃላ ከወረድን በኃላ ከሌሎቹ ጀልባዎች ተመሳሳይ ጥያቄ ኖሮ ተመሳሳይ መልስ አግኝተዋል።በወቅቱ ዓሳ የሚያሰርግ የለም ማለት ይቻላል።ከእዚህ በላይ በሐይቁ አንድም የሞተር ጀልባ የለም።የሞተር ጀልባ ገዝተን ለቅዱስ ቂርቆስ ቤተክርስቲያን ለመስጠት እና የአካቢውን ሕዝብ እንድታገለግል ሃሳብ ተጠንስሶ ያደረው በእዚህ ወደ 60 የሚጠጋ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኛ ቤተክርስቲያኑን ተሳላሚ ነበር።በእርግጥ በኃላ ገንዘብ ተዋጥቶ በሀገረ ስብከት በኩል ቤተክርስቲያኒቱ የሞተር ጀልባ እንዲኖራት ተደርጎ ለሕዝቡ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
በእዚህ በወንጪ ቂርቆስ ጉብኝታችንም ላይ ከአፋፍ ላይ ሁለት ሾጣጣ (የኮርያ ቤቶች የመሰሉ) ወደፊት መዝናኛ የሚሆኑ በሁለት የግል ባለ ሀብቶች እየተሰራ መሆኑን አይቻለሁ።ነገር ግን የአካባቢው ነዋሪዎችም የሁለቱ ኢንቨስተሮች አገባብ በሙስና እንደሆነ እና ትክክል አለመሆኑን በምሬት ሲናገሩም ተመልክቻለሁ። እንደ ጎርጎራ ሁሉ ወንጪ ብዙ የሚሰራበት ትልቅ የቱሪስት ቦታ እንደሚሆን በተለይ ዓሳ ከስር ጀልባውን እየደበደበ በአግባቡ አለመሰገሩ እና ጥቅም ላይ አለመዋሉ የመልስ ጉዞአችን ላይ የአውቶብስ ውስጥ ጫወታችን ነበር።ምን ጫወታ 'መቃጠላችን' ነበር።
'ለሁሉም ጊዜ አለው' እንደተባለ ዛሬ ለጎርጎራ እና ወንጪ እንዲሁም ለኮይሻ ልማት የገበታ እራት አዲስ አበባ ላይ መዘጋጀቱን ስሰማ ይህንን ከልቤ የነበረ ጉዳይ ላጫውታችሁ ብዬ ጫር ጫር ማድረግ ጀመርኩ።ቦታዎቹ ሳይለሙ ቀልብ የሚስቡ እና የሚያስደምሙ ናቸው።የተፈጥሮ ይዞታቸው ሳይናጋ በጥንቃቄ ከለሙ ተዓምር እንደሚሆኑ እመሰክራለሁ።ቦታውን አይታችሁ ወደ ልማት እንዲቀየር ሃሳብ ያቀረባችሁ እና ወደ ሥራ እንዲቀየር የምትሰሩ ሁሉ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይን ጨምሮ ለማመስገን እፈልጋለሁ። ለትውልድ የሚሆን ቅርስ እየሰራችሁ ነው።አመስጋኙ ደግሞ የዛሬው ትውልድ ብቻ አይሆንም መጪውም እንጂ።
========================
***************************
ማስታወቂያ /Advertisement
====================
Click the link below to Top-up your friends or family's mobile air time.
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ?
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ -
No comments:
Post a Comment