በኢትዮጵያ ኦ/ተ/ ቤ/ክርስቲያን የሰሜን አውሮፓ (ስካንዲንቭያን እና አካባቢው) ሀገረ ስብከት የኦስሎ መካነ ቅዱሳን ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን የስድስት ዓመት ስልታዊ (ስትራቴጂ) ዕቅድ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የኢጣልያን እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ የበላይ ጠባቂ በተገኙበት አቀረበች።ላለፉት ስድስት ወራት ሰባት የኮሚቴ አባላት ያሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ ስልታዊ ዕቅድ አዘጋጅ ኮሚቴ በስልታዊ ዕቅዱ ዝግጅት ላይ ሲሰራ የነበረ ሲሆን ከሁለት ሳምንት በፊት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ልዩ ልዩ የአገልግሎት ክፍሎች ጋር ውይይት አድርጎ ሃሳብ ከተቀበለ በኃላ፣ዛሬ ጥር 2፣2013 ዓም ደግሞ በቀጥታ የዩቱብ ስርጭት ለአጥቢያ ቤተክርስቲያኒቱ ምዕመናን በስልታዊ ዕቅዱ ዙርያ ማብራርያ ሰጥቷል።
በዛሬው የስልታዊ ዕቅድ ዙርያ ማብራርያ ያቀረቡት የአዘጋጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶ/ር ዳዊት ሻወል አስፈላጊነቱን ሲያብራሩ በቀዳሚነት ያስቀመጡት የቤተ ክርስቲያንን ግቦች እና ርዕይ ለማሳካት መሰረት የሚሆን ሰነድ መኖሩ አስፈላጊ በመሆኑ መሆኑን የገለጡ ሲሆን በሌላ በኩል ቤተክርስቲያኒቱ ለምታቅዳቸው ዕቅዶች እና ተግባራት ፍኖተ ካርታ እንዲኖራት እንደሚያደርግ አብራርተዋል።ዶ/ር ዳዊት በመቀጠል የስልታዊ እቅድ ዝግጅቱ የመረጃ ምንጮቹ የተለያዩ ዶክመንቶችን ማለትም የቤተ ክርስቲያኒቱ ዓመታዊ ዕቅዶች እና ሪፖርቶች ከመገምገሙም በላይ በውጭያዊ ተፅኖ ዙርያ የኖርዌይ መንግስት የፖሊሲ ዶክመንቶችን በመመርመር በግብዓትነት መጠቀሙን አብራርተዋል።
በሌላ በኩል የአዘጋጅ ኮሚቴው ጸሃፊ ዶ/ር ታጠቅ ፍቃዱ የስልታዊ እቅዱ ዝግጅት በአገልግሎት ላይ ካሉ የተለያዩ ንዑስ የአገልግሎት ክፍሎች እና ምዕመናን በተሰበሰበ መጠይቅ መሰረት አስፈላጊው ግብዓት መሰብሰቡን፣በአጥብያው የጥንካሬ፣ድክመት፣ዕድል እና ስጋት ትንተና መካሄዱን፣የስልታዊ ዕቅዱ ወሳኝ ጉዳዮች እና በስራቸው ያሉትን ዓላማዎች ላይ በዝርዝር አብራርተዋል።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ኖርዌይ ለተወለዱ ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች የአብነት ትምህርት ሲያስተምሩ
(ኦስሎ መካነ ቅዱሳን ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አዳራሽ)
ይህ ፎቶ ከኮሮና ወረርሽኝ በፊት የተነሳ ሲሆን አሁንም አገልግሎቱ በቪድዮ መገናኛ ቀጥሏል
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የኢጣልያን እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ የበላይ ጠባቂ በመካነ ቅዱሳን የኦስሎ ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ለመጪዎቹ ስድስት ዓመታት ማለትም ከ2013 ዓም እስከ 2018 ዓም የሚተገበረው ስልታዊ ዕቅድ ከያዝነው አዲሱ የአውሮፓውያን ዓመት 2021 ዓም ጀምሮ ቤተክርስቲያኒቱ ሥራ ላይ ከምታውለው ዕቅድ ጋር ተግባራዊነቱ እንደሚጀምር ከገለጡ በኃላ በእዚህ ዓይነቱ አሰራር ቤተክርስቲያን ካልተራመደች በሌሎች እየተቀደመች የመሄድ ዕጣ ስለሚገጥማት ምዕመናን ለስልታዊ ዕቅዱ መሳካት በአገልግሎት በንቃት መሳተፍ እንደሚገባቸው አባታዊ ምክር እና ማሳሰቢያ ሰጥተው መርሃግብሩ ተፈፅሟል።
ይህ የኦስሎ ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ስልታዊ ዕቅድ ለቤተ ክርስቲያን መልካም አርአያነት ያለው እና ሁሉም አጥብያዎች እና ሀገረ ስብከቶች ሊከተሉት የሚገባ ውጤታማ የአሰራር መንገድ ነው።የኦስሎ ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር አስተባባሪነት እና በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የቅርብ ክትትል፣በዓመት ሁለት ጊዜ ማለትም በእየስድስት ወሩ የቤተ ክርስቲያኒቱ አጠቃላይ የአገልግሎት ክፍሎች ሪፖርት ለምእመናን የምታቀርብ እና ሃሳብ የምትቀበል ስትሆን ዓመታዊ ዕቅዶችም በመጀመርያ በአገልግሎት ንዑስ ክፍሎች ደረጃ እንዲታቀድ አድርጋ እና ተወያይታ ለጠቅላላ ምዕመናኑ በማቅረብ በሥርዓት በማስተቸት፣ሃሳብ በመቀበል እና በሃሳቦቹ መሰረት ማሻሻያ በማድረግ ሥራ ላይ የምታውል አጥብያ ቤተ ክርስቲያን ነች።በእዚህም መሰረት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከማዕከላዊ የኦስሎ ከተማ በቅርብ እርቀት የሚገኝ የራሷ ህንፃ ቤተ ክርስቲያን መግዛት፣በአሁኑ ጊዜ በአገልግሎት ላይ ያሉ በኖርዌይ ተወልደው ያደጉ 12 ዲያቆናትን ያፈራች ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው ታዳጊ ሕፃናት የአብነት ትምህርት በመስጠት ላይ ትገኛለች።
===========================
ማስታወቂያ
============
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ?
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ -
No comments:
Post a Comment