ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, January 24, 2021

ሰበር ዜና - በሱዳን ትናንት እና ዛሬ ከፍተኛ ተቃውሞ ሰልፍ ነበር።ሀገሪቱ አዲስ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ያሰጋታል

በካርቱም የእዚህ ሳምንት አመፅ መንገዶች በወጣቶቹ እንዲህ ተዘግቶ ነበር።
Photo = AFP

የጉዳያችን ልዩ ጥንቅር   
======================
በሱዳን ትናንት ቅዳሜ ጥር 15/2013 ዓም ከፍተኛ ተቃውሞ ሰልፍ ነበር።ሰልፈኞቹ በኦምዱርማን አል-አርባይን ጎዳና እና በርካታ ሰፈሮችን በመዘዋወር መንገዶችን ዘግተው ጎማዎችን አቃጥለዋል ፡፡በማዕከላዊ እና ደቡብ ካርቱም ሰሜን አቅራቢያ ባሉ አከባቢዎች ተመሳሳይ ተቃውሞዎች ተካሂደዋል ፡፡ሰልፈኞቹ በሽግግር መንግስቱ ኢኮኖሚያዊ ዕቅዶች ላይ መፈክሮችን በማሰማት በዳቦ እና በነዳጅ እጥረት የተነሳ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።መንግስት የዳቦ ዱቄት ላይ ድጎማ እያደረገ ቢሆንም ቀውሱ ከመባባሱ በላይ በደርዘን የሚቆጠሩ መጋገርያዎች መክሰራቸው እና ከገበያ ውጪ በመሆናቸው ንግዳቸውን ለመዝጋት መወሰናቸው ነው የተሰማው።

በእዚህ መሰረት የዳቦ መጋገሪያዎች ባለቤቶች  በድጎማ የሚገኘውን ዱቄት ተጠቅመው የሚጋግሩት ዳቦ  ከ 2 ፓውንድ በአንድ ዳቦ ወደ 5 ፓውንድ ለማሳደግ ጥያቄ አቅርበው ነበር ፡፡አመፁ በዛሬው ዕለትም የቀጠለ ሲሆን ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ መርጨቱ ለማወቅ ተችሏል።በእዚህ ተቃውሞ የካርቱም ዋና የደም ስር የተሰኘውን 60ኛው ጎዳና ለትራፊክ ዝግ እንዲሆን ተገዶ ነበር።መንግስት በበኩሉ የሽያጭ ዋጋ በኪሎግራም ላይ የተመሠረተ እንዲሆን የሚወስን መስፈርት ለመቀየር መወሰኑ ነው የተሰማው፡፡መንግስት በሌላ በኩል በሬስቶራንቶችና በካፍቴሪያዎች ላይ ከተደረገ ሌላ ዘመቻ በተጨማሪ ክብደቱን በትክክል መያዙን ለማረጋገጥ በመዲናዋ መጋገሪያዎች ላይ የክትትል ዘመቻዎች እንደሚያደረግ አስታውቋል፡፡

በሚያዝያ 2020 (እ.ኤ.አ.) የካርቱም መንግስት  በድጎማ የሚገኘውን የዳቦ ዋጋ ከ 1 ፓውንድ በአንድ ዳቦ ወደ 2 ፓውንድ ከፍ ማድረጉ ይታወሳል ፡፡ምንም እንኳን አንዳንድ ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎች የወሰደ ቢሆንም የአሁኑ የሱዳን የሽግግር መንግስት የግል ዳቦ ጋጋሪዎች የሚጠቀሙባቸውን ዱቄት ለጋጋሪዎች በቅናሽ ዋጋ እንዲደርስ አሁንም ድጎማ እያደረገ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን መንግስት በመሃል የሚገኙ አቀባባዮች የሚሄዱበትን የሙስና መንገድ መዝጋት እንዳልቻለ ነው የሚነገረው።ይህ በእንዲህ እያለ በሱዳን በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት መኖሩ ነው እየተነገረ ያለው። በእዚህ ምክንያት ሀገሪቱ ከውጭ የምታስመጣቸው እቃዎች ላይ የራሱን ተፅኖ ፈጥሯል።አንድ የሁለተኛ ደረጃ ዩኒፎርም የለበሰ ወጣት ለዴይል ሜል በሰጠው ቃል በትምህርት ቤት ለቁርስ የሚሆን ዳቦ ማግኘት አልቻልንም ብሏል።

በ2019 ዓም እኤአ በዳቦ ዋጋ የተነሳው ተቃውሞ ኦማር አልበሽር ከስልጣን እስከመውረድ አድርሶ እንደነበር ይታወሳል።አሁን ደግሞ የኮሮና ቫይረስ ባለበት ረጅም የዳቦ ሰልፍ ለሰዓታት መቆም ከመብራት መቆራረጥ ጋር ተደምሮ ለሕዝቡ ትልቅ የራስ ምታት ሆኗል።60 ቢልዮን ዶላር ዕዳ ያለባት ሀገር ባለፈው ወር ብቻ የዋጋ ግሽበቷ 269 በመቶ በላይ መድረሱ ሀገሪቱ ወደ ከፍተኛ ቀውስ እየመራት ነው።ይህ በእንዲህ እያለ በቅርቡ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ፀሐፊ ስቴቨን ምኑቺን ወደ አንድ ቢልዮን ዶላር ውዝፍ እዳ ከዓለም ባንክ ለማቅለል አንድ ዓይነት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሟ እና ከአሜሪካ አስመጪ እና ላኪ ባንክ ጋር ሌላ የአንድ ቢልዮን ዶላር ስምምነት መፈራረሟ ለማወቅ ተችሏል።በሌላ በኩል የጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ መንግስት አሜሪካ ለረጅም ጊዜ በሱዳን ላይ ጥላው የነበረው ሱዳንን በጥቁር መዝገብ ውስጥ ያስገባው እቀባ መነሳቱ ለሱዳን ምጣኔ ሀብት መነቃቃት ይፈጥራል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

በሌላው የሱዳን ክፍል ዳርፉር በእዚህ ሳምንት ውስጥ በተከሰተ አዲስ ግጭት 10 ሕፃናትን ጨምሮ 250 ሰው መገደሉ ተሰምቷል።በእዚሁ ግጭት 100 ሺህ ሰው ከቤቱ የተፈናቀለ ሲሆን ከ3 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ምስራቃዊ ቻድ መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን መረጃ ያሳያል።የዳርፉር ግጭት በያዝነው አዲስ ሚሊንየም መጀመርያ ዓመቶች ላይ ከተጀመረ ወዲህ ከ300ሺህ በላይ ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን ወደ 2 ነጥብ 5 ሚልዮን ሕዝብ ደግሞ ተፈናቅሏል።

በሱዳን በአሁኑ ጊዜ በተከፋፈለው የጦር ኃይሉ እና በሽግግሩ መንግስት መሃል ያለው ልዩነት ከምንጊዜውም በላይ እያፈጠጠ ነው። የጦር ኃይሉ በራሱ መንገድ የመሄዱ አንዱ ማሳያ የኢትዮጵያን ድንበር መጣሱን የሽግግር መንግስቱ ባለስልጣናት ባይደግፉትም ጦሩ ግን በራሱ መንገድ ሄዷል።አሁን በሱዳን እየሆነ ያለውን አጠቃላይ ሂደት ላይ ሃሳባቸውን እንዲሰጡ ጉዳያችን የጠየቀቻቸው የሱዳን ምሑር ሁለት ስጋት እንዳለባቸው ገልጠዋል።አንደኛው ወገን ለውጡ እራሱ የመጣው አልበሽርን ገለል አድርጎ ሱዳን በአሜሪካ የተጫነበትን ዕቀባ ማስቀረት እና መልሶ የአልበሽር ደጋፊዎች በወታደራዊ መፈንቅል ተመልሰው ወደ ስልጣን እንዲመጡ የማድረግ ዕቅድ ቀድሞውንም ተይዟል የሚሉ ሲሆን።ሌላው ወገን ደግሞ የጦር ኃይሉ መኮንኖች በመካከለኛው ምስራቅ ባላንጣ ሀገሮች አንፃር ስለተቀራመቷቸው በእነኝህ ሀገሮች ሴራም አንፃር በሱዳን አሁን ያለውን የሽግግር መንግስት ለመፈንቀል እንቅስቃሴ እንደሚኖር ጥርጣሬ አላቸው።

ለማጠቃለል ሱዳን በቀውስ ውስጥ የምትንገዳገድ ሀገር ሆናለች።በውስጥ ያለው ቅራኔ በመካከለኛው ምስራቅ የገመድ ጉተታ ውስጥ የጦር ሹማምንቶቿ ገብተዋል።የሽግግር መንግስቱ ደግሞ የምጣኔ ሃብቱን ማረጋጋት አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን የዳርፉር ችግር ከማጡ ወደ ድጡ እየሄደ ነው።ይህ በእንዲህ እያለ ሀገሪቱ አሁን ከሚታየው በላይ በግብፅም ሆነ በሌላ የውጭ ኃይል የበለጠ የምትዘወር ሀገር ሆና መቅረቧ ያልተረጋጋ የውጪ ፖሊሲ መኖር ብቻ ሳይሆን፣ከቀልቧ ጋር ያልሆነች ምድር ብትሆን ሊደንቅ አይገባም። የሱዳን ዓይነት አጀንዳ የተሸከመ ሀገር ጠባይ ከእዚህ ያነሰ ሊሆን አይችልም።ከእዚህ ሁሉ ጋር አሁን ያለው የሽግግር መንግስት እየሰከነ መጥቶ የጦር ኃይሉን ከነውጠኛ መኮንኖች አፅድቶ በእዚህ ዓመት ይደረጋል የሚባለው ምርጫ ከተሰካ ሱዳን ወደ አዲስ ዘመን እየተሸጋገረች ነው ማለት ነው።የሱዳን በእዚህ መልክ መረጋጋት ወጥ የሆነ የውጭ ፖሊሲ በተለይ ከምስራቃዊ ጎረቤቶቿ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጋር የሰከነ ግንኙነት እንዲኖራት ያደርጋታል።ከሁሉም በላይ በዓባይ ግድብ ላይ የምታነሳውን በራሷ ጥቅም ላይ የመቆም አባዜ በተላቀቀች ነበር።ሱዳንን ከመፈንቅለ መንግስት ይሰውራት? ወይንስ አይሰውራት? ጥያቄ ነው።ለኢትዮጵያ የሽግግር መንግስቱ ቢረጋጋ እና የጦር መኮንኖቹን ቢቆጣጠር የተሻለ የሚሆን ይመስላል።አሁን የጦር መሪዎቹ የሽግግር መንግስቱን በመናቅ በራሳቸው የሚቦርቁባት ሀገር ሆናለች።እነኝህ መኮንኖች ወደ ስልጣን ቢመጡ ከጥቅሙ ጉዳቱ ለአፍሪካ ቀንድ አይተርፍም ማለት አይቻልም።ምክንያት - ከአሁኑ በባሰ በውጭ ኃይሎች የምትዘወር ምድር መሆኗ ሊብስ ይችላል።
=================


No comments:

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...