ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, March 22, 2020

የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች በመላው ዓለም ከሩብ ሚልዮን አልፏል።በሽታው በአስፈሪ ደረጃ እየጨመረ ነው።በኢትዮጵያ ሕዝቡን ከማንቃት ጎን አስገዳጅ ሕግም ያስፈልጋል።የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ላይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች አሉ።



ጉዳያችን ሚድያ፣ኮሚኒኬሽን እና ምክር አገልግሎት 
Gudayachn Multimedia, Communication and Consultant

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን አስመልክቶ የዓለም ጤና ድርጅት በሚያወጣው ወቅታዊ መረጃ መሰረት የተጠቂዎቹ ቁጥር ሩብ ሚልዮን አልፏል።የመጨመሩን ፍጥነት ለመረዳት ባሳለፍነው ሳምንት  በሐሙስ እና በዓርብ መሃል ብቻ 32 ሺህ ሕዝብ አዲስ ተጠቂ ሪፖርት የተደረገ ሲሆን በዓርብ ዕለት ከነበረው ቅዳሜ ዕለት በ26 ሺህ አዲስ ታማሚ ቁጥር ማደጉን ነው የዓለም ጤና ሪፖርት የሚያሳየው።በመሆኑም የዓለም ጤና ድርጅት እስከ ቅዳሜ መጋቢት 12/2020 ዓም ድረስ ወረርሽኙን አስመልክቶ የሚያሳየው ሪፖርት በዓለም ላይ በሽታው እንዳለባቸው የተረጋገጠው 292,142 ሰዎች ሲሆኑ፣ በሞት የተለዩ =12,784 (ከእነኝህ ውስጥ 1600 ያህሉ በአንድ ቀን ብቻ የተመዘገበ የሞት ቁጥር ነው)።

በኢትዮጵያ ሕዝቡን ከማንቃት ጎን አስገዳጅ ሕግም ያስፈልጋል።የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ላይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች አሉ።


በአገር ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ ከተጠቁት ውስጥ ለምሳሌ ጣልያንን ብንመለከት በሰው ልጅ አዕምሮ ከሚታወቁትም ሆነ ከማይታወቁት ምክንያቶች ሌላ በመጀመርያ ደረጃ የበሽታውን አደገኛነት በሚገባ አለመረዳት እና ችላ ማለት አንዱ ምክንያት መሆኑን በጣልያን ያሉ ኢትዮጵያውያን ሳይቀሩ እያስገነዘቡት ያለ ጉዳይ ነው።

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ መንግስት እየወሰዳቸው ያሉ መልካም ርምጃዎች የሚበረታቱ ናቸው።የትምህርት ቤቶች መዘጋት፣የመገናኛ ብዙሃን ትኩረት መስጠት፣የቴሌ እና የእምነት አካላት ውሳኔ ሁሉ ጥሩ ነው።ሆኖም ግን ከአደጋው አንፃር  አሁንም የሚቀሩ ጉዳዮች አሉ።በተለይ በሕዝቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ አሁንም የሚቀር ጉዳይ እንዳለ ለመረዳት በዩንቨርስቲ ደረጃ ያሉ መረጃውን በደንብ ያገኛሉ የተባሉ ሳይቀሩ ቸልተኝነት ሲያሳዩ መስማት ያስደነግጣል።ባሳለፍነው ቅዳሜ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ዜና ላይ በዩንቨርስቲ ዙርያ ያለውን ሁኔታ በዳሰሰ አንድ ዘገባ ላይ የደብረ ታቦር ዩንቨርስቲ መምህር ሲናገሩ ''እኛ ተማሪዎች ሲቀመጡም ሆነ ሲመገቡ ተራርቀው መቀመጥ እንዳለባቸው ስንነግራቸው እኛ ተለያይተን አናውቅም።ስንበላም ብቻችንን በልተን አናውቅም'' የሚል ምላሽ ማግኘታቸው አንዱ ለቸልታው ማስረጃ ነው።

እዚህ ላይ በዩንቨርስቲ ተማሪ ደረጃ ጥንቃቄው በእዚህ ደረጃ ከተገለጠ። በሌላው ሕዝብ ዘንድ በሚድያ ከምናየው በላይ ምን እያለ እንደሆነ ለማወቅ ቀላል ነው። በሌላ በኩል ወረርሽኙ ከውጭ እንደመምጣቱ፣የውጪ አገር ዜጎች የሚያዘወትሩባቸው የቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች እና በእዚያ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች እና የንግድ ቦታዎች ሁሉ ተገቢው ምርመራ ማድረግ እና  ቦታዎቹ ለውጪ ዜጎች ዝግ ማድረግ ተገቢ ነው።

አሁን ባለበት ሁኔታ ግን የማስተማሩን እና ሕዝቡን የማንቃት ሥራ ከመቀጠል ጎን ከጎን አስገዳጅ ሕግም ማውጣት አስፈላጊ ነው። የእዚህ አይነት ሕግ በአውሮፓ፣አሜሪካም ሆነ በራሷ በቻይናም የተተገበረ ነው።ለምሳሌ ወረርሽኙን ተከትሎ  መንግስት ለምያወጣው የመንቀሳቀስ ገደብ፣የጥንቃቄ አወሳሰድ ደንቦች፣የተሳሳቱ መረጃዎች በበሽታው ዙርያ ማሰራጨት እና  የዋጋ መጨመርን በተመለከተ ሁሉ በልዩ ቅጣት ስር ማካተት ካልተቻለ አንዳንዱ ራሱን መጠበቁ ክግዴታ ሳይሆን ከበጎ ፈቃድ  እና የራስ መብት አንፃር እያየው ቸልተኝነቱ እየበዛ ለሌሎች የማስተላለፍ አደጋው እንዳይጨምር ያሰጋል።ይህ ደግሞ አገራችንን ማቅ የሚያለብስ ብሔራዊ ሃዘን እንዳያለብሳት፣የመስርያው እና የመወሰኛው ጊዜ አሁን ነው።  


No comments: