ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, March 2, 2020

ትውልዱ በፍጥነት ተደራጅቶ የሰለጠነ ፖለቲካ አካል መሆን ይገባዋል።ጊዜ የለም!

ጉዳያችን ሚድያ፣ኮሚኒኬሽን እና ምክር አገልግሎት 
Gudayachn Multimedia, Communication and Consultant
ወቅታዊው አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ 

ኢትዮጵያ በወሳኝ ፖለቲካዊ፣ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ የአቅጣጫ ለውጥ ዳር ላይ ትገኛለች።ይህ ጊዜ አገሪቱ በ21ኛው ክ/ዘመን የሚኖራት መልክ የሚወስን ወሳኝ ጊዜ ነው።የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ቀንድም፣የመካከለኛው ምሥራቅም ሆነ የመላው ዓለም ፖለቲካ የሆነ የለውጥ አፋፍ ላይ ያለ ይመስላል።የአፍሪካ ቀንድን ብቻ ብንመለከት የሩቅም ሆኑ የቅርብ አገሮች ወታደራዊ ሰፈሮቻቸውን ከኤርትራ እስከ ሱማልያ እየኮለኮሉ ነው።ቱርክ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በሱማሌ ውስጥ እየገነባች ነው።የመካከለኛ ምስራቅ የኩአታር እና የኢራን ባንድ በኩል በሌላ መስመር የሳውዲ ቡድን ተፋጠዋል።የመረጃ መመነታተፋቸው ከረቀቀው የሳይበር ጦርነት እስከ አደባባይ ደርሷል።

የኔቶ አባል ቱርክ በሶርያ ከሰሞኑ በተለየ መልክ የያዘችው ዘመቻ ከሩስያ ጋር ሳይቀር አፋጧታል።በሌላ በኩል የቱርክ ለአውሮፓ ያላት ስልታዊ አቀማመጥ እና ለምዕራቡ ዓለምም አለመታመን እንዲሁም በአልታሰበ ጊዜ የሩስያ እና ኢራን ስልታዊ ጥምረት የመፍጠር አደጋ ለአውሮፓ ስጋት እንደሆነ ነው።ባሳለፍነው ሳምንት የቱርክ መንግስት ከፍተኛ አማካሪ ለቢቢሲ ሲናገሩ ቱርክ በቅርቡ በእርሷ ጋር የሚገኙትን ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡ ስደተኞች ወደ ምዕራብ አውሮፓ እንዲሄዱ እንደምትፈቅድ ሲያብራሩ  ''እኛ ድሮም የስደተኞች ፖሊሲ ለውጥ አላደረግንም።ድንበሩን እንከፍትላቸዋለን'' ነበር ያሉት። ቱርክ ምዕራቡን የምታስፈራራው በስደተኛ ጎርፍ የመምታት አቅሟን በማሳየት ነው።የአውሮፓ ህብረት ከእዚህ በፊት  ቱርክ ስደተኞቹን እንዳታሳልፍ በገንዘብ እየደጎመ አስታግሷት ነበር።ከሰሞኑ ግን እኝሁ ከፍተኛ አማካሪ ሲናገሩ ''ስደተኞቹ  የምዕራባውያን የክፋት ሰለባዎች ናቸው።ምዕራባውያን ክፉ ስራቸው  ውጤቶች ናቸው'' በሚል ቃላት መናገራቸው  የቱርክ አካሄድ ወዴት እንደሆነ ለማወቅ አዳጋች አድርጎታል።

በሌላ በኩል የዓለም ምጣኔ ሀብት በከፍተኛ ሁኔታ አደጋ አንዣቦበታል።ለእዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ የትራምፕ የንግድ ጦርነት ከሜክሲኮ እስከ ቻይና መዝለቁ ብቻ ሳይሆን የቻይናው ኮሮና ቫይረስ ጉዳይም ጭምር ነው።ቻይና የዓለማችን ግዙፍ ምጣኔ ሀብት አንቀሳቃሽ ነች።የአውሮፓ አገሮች ሳይቀሩ የቻይና ዕዳ አለባቸው።እዳው ደግሞ በንግድ ግንኙነት የሚጣጣ ተደርጎ የታሰበ ነበር። አሁን በኮሮና ቫይረስ ሳብያ የቻይና ተፅኖ ቀላል አይደለም።በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ኢኮኖሚ ተፅኖ ይኖረዋል።አፍሪካውያን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2002 ዓም ከቻይና የነበረባቸው ዕዳ 1ቢልዮን ዶላር ብቻ የነበረ ሲሆን በ2019 ዓም ወደ 142 ቢልዮን ዶላር አሻቅቧል።ከእዚህ ውስጥ 42 ቢልዮኑ የአንጎላ ዕዳ ብቻ ነው።ስለሆነም የቻይና ጉዳይ በተለይ በኮሮና ቫይረስ ሳብያ ቀውሱ ከተባባሰ የአፍሪካ ምጣኔ ሀብት አደጋ ይዳረግበታል።የኢትዮጵያም እንዲሁ።

ትውልዱ አባቶቹ በሙቱላት አገር እንደ ፍልስጤማውያን 'የአገር ስጡኝ' ልመና ላለመግባት፣ በፍጥነት ተደራጅቶ የሰለጠነ ፖለቲካ አካል መሆን ይገባዋል።

ከላይ ለማንሳት እንደተሞከረው አገራዊ፣አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች የሚያሳዩት ሊመጡ ከሚችሉ ፖለቲካዊ፣ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶች  ለመውጣት ትውልዱ ከፖለቲካው ዓለም በመራቅ የተጣለበትን የተረት ቡልኮ አውልቆ በአዲስ መልክ እና የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል ስሜት ተደራጅቶ የዘመናዊው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት አካል መሆንን የሚጠይቅ ጊዜ ላይ መሆናችንን ነው። ዘመናዊ ፖለቲካ ዘመኑ የሚጠይቀው ፖለቲካ በሚለው ይወሰድልኝ።በዓለም ላይም ሆነ በአካባቢያችን የሚከሰቱት ክስተቶች ለቀረው ዓለም ቀውስም ሆነ ዕድል ቢሆኑ ይህ ትውልድ ግን ያለበት ኃላፊነት የራሱን ድርሻ ለመወጣት ተደራጅቶ የፖለቲካው አካል በመሆን የፖሊሲ አውጪነቱን እና በራሱ ዕድል ላይ ሌሎች እንዲወስኑ ተቀምጦ መጠበቅ ሳይሆን የእርሱ ድምፅ እንዲሰማ ተደራጅቶ የፖሊሲ አውጪው አካል መሆን ነው።


ስለሆነም በመጪው ነሐሴ ይደረጋል ለተባለው ምርጫ የዳር ተመልካች በመሆን እና የፖለቲካውን ሜዳ ለፅንፍ የጎሳ እና አክራሪ ኃይሎች በመልቀቅ ኢትዮጵያ አገሩን እንዳያጣ መጠንቀቅ ይገባዋል።በኢትዮጵያ ካሉት የፖለቲካ ድርጅቶች ቁጥራቸው በመቶዎች ይቆጠሩ እንጂ ኢትዮጵያን እንደኢትዮጵያ ለማሻገር  የሚመኙት እና በአንፃራዊ መልኩም ቢሆን አቅም አላቸው የሚባሉት  አራት አይሆኑም።ይህ ማለት አሁንም ኢትዮጵያ ቃላት ከመቶ ሚልዮን በላይ ሕዝብ ውስጥ ድምፁ ያልተሰማ እና ኢትዮጵያ እንዴት መቀጠል እንዳለባት የራሱ ሃሳብ፣ሕልም እና አቅም ያለው ትውልድ አለ ማለት ነው። ይህ ትውልድ ደግሞ መደራጀት የወቅቱ ጥይቄ መሆኑን ማመን አለበት።ኢትዮጵያውያን በጋራ አሳባቸው ሲደራጁ ደቂቃ አይፈጅባቸውም። የሰለጠኑ፣የሚሰሩትን የሚያውቁ እና ስረ መሰረታቸው በማይበጠስ ሕብረት የተሳሰረ ነው።ጥምቀት ሲደርስ ማንም ጡሩንባ አይነፋላቸውም፣ ለመውሊድ ሲሰበሰቡ ደውል አይጠብቁም፣ለደመራ ከዓመት ወር እና ሰዓት ሳያዛንፉ ሲገኙ መካሪ አይፈልጉም።የሚያደርጉትን ያውቃሉ።

ለማጠቃለል ይህ ትውልድ ኢትዮጵያን የማስቀጠል እና ክብሯን በ21ኛው ክ/ዘመን ፈተና አሻግሮ፣ ጠብቆ ማስቀጠል እና ለልጆቹ ማውረስ አለበት። ይህንን ለማድረግ ደግሞ መደራጀቱ ወሳኝ ነው።ለመደራጀቱ ከዘገየ ግን ነገ እንደ ፍልስጤማውያን 'አገር ስጡኝ' ብሎ የሚለምን እንዳይሆን የዛሬ ሥራ ዛሬ መሰራት አለበት።ከጎሳ ክፍፍል በራቀ መልኩ፣ኢትዮጵያዊ ሕብረ ብሔርነቱን አክብሮ እና ማንነት መሰረቱን ሳይነቅል ለሚሰራው ሥራ ሁሉ ደግሞ ሕዝብም እግዚአብሔርም አብረውት ናቸው።ጉዳያችን GUDAYACHN

No comments: