- ይህ ጉዳይ ኢትዮጵያውያን የበለጠ እንዲነጋገሩበት ሁኔታው መንገድ ከፍቷል።
- የክልል ባለስልጣናት፣የዞን ኃላፊዎች፣የወረዳ ባለስልጣናት፣ሚኒስትሮች፣ኮሚሽነሮች፣የመምሪያ ኃላፊዎች ሲሾሙ መስፈርቱ ምን ነበር?
- በኢትዮጵያ አንድ ሰው ምን ያህል ዕውቀት፣ልምድ እና ችሎታ ቢኖረውም የኦሮቶዶክስ ክርስቲያን አማኝ በመሆኑ ብቻ ከስልጣን እየተገፋ ነው?
- ጉዳዩ ጠለቅ ላለ ምርምር ይጋብዛል።የዛሬው የፓርላማው ውሎ አንድ ደውል በኢትዮጵያውያን ጆሮ አቃጭሏል
- ኢትዮጵያ የአንዱ ወገን ወይም የሌላው አይደለችም።ሁሉም እኩል መብት አለው።ትውልዱ አገር በጣሳ እየሰፈረ የሚሰጠው ወይንም የሚነፍገው ፓርላማ አይፈልግም።
- በልበሙሉነት አገሩን መረከብ እንዳለበት ይህ ትውልድ ከምንጊዜውም በላይ ከገባው ዛሬ ነው።
===================
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት የቦርድ አባላት ሹመትን አጽድቋል።በእዚህ መሰረትም ምክር ቤቱ ከቀረቡለት ዘጠኝ ግለሰቦች ውስጥ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ እና ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ይገኙበታል።የምክር ቤቱ አባላት ውስጥ የተወሰኑቱ የሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን ሹመት ሲቃወሙ ታይተዋል።ሆኖም ግን አብላጫው በድምፅ ብልጫ በመደገፉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ባቀረቡት መሰረት የሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ሹመት አልፏል።
የተወሰኑ የፓርላማው አባላት የተቃወሙበት ምክንያት ግን የሚጠቁማቸው ሁለት ግልጥ ጉዳዮች አሉ። እነርሱም -
1ኛ) ፓርላማው በፅንፈኛ አክቲቪስቶች ማኅበራዊ ሚድያ ከማየት ያለፈ ብዙም ብስለት የሌላቸው ሰዎች በውስጡ መያዙን
በፓርላማው ውስጥ የሙሐዘ ጥበባት ዲ/ን ዳንኤልን ሹመት የተቃወሙት የፓርላማው አባላት፣ የዲያቆን ዳንኤል ክብረትን ለፕሬስ ድርጅት የሚመጥን ፣ከሃያ ዓመታት በፊት የስነፅሁፍ ምሩቅ መሆኑን አላነሱም። የፓርላማው አባላት ዳንኤል የፕሬስ ስራን የሚያውቀው እና በስራው ውስጥ ከሃያ አምስት ዓመታት በላይ የስራ ልምድ እንዳለው አላነሱም። የፓርላማው አባላት ዳንኤል ከደርዘን በላይ መፃሕፍ ማሳተሙ ከፕሬስ ድርጅት ሥራ ጋር በቀጥታ የተቆራኘ የአሰራር ልምድ እንዳለው አላነሱም።ዳንኤል በኢትዮጵያ በመንግስት ያልተሞከረውን ለኢትዮጵያ የለፉ ሰዎች የሚሸለሙበት በጎ ሰው የተሰኘ የሽልማት ድርጅት እንዲመሰረት ሃሳብ ከማመንጨት እስከ ተግባራዊ ሥራ ድረስ እየሰራ መሆኑን አላነሱም።የፓርላማው አባላት ዳንኤል በመላው ዓለም ከአንድ መቶ አገሮች በላይ ተዘዋውሮ ከፍተኛ የፖለቲካ ፣የማኅበራዊ እና የባሕል ልምዶች ማግኘቱን አልተነፈሱም።
በእርግጥ የእዚህ ዓይነቱ የሙያ ጥያቄ ሊነሳ የሚችለው የሚያነብ እና የሚያገናዝብ የፓርላማ አባል ሲኖር ነው።በአክቲቪስት ፌስ ቡክ ላይ ከጧት እስከ ማታ ተጥዶ ውሎ ለሚያድር እና እውቀት ማለት የማኅበራዊ ሚድያ ብጥቅጣቂ ፅሁፍ እንደ የዕውቀት ምንጭ አድርጎ ለሚወስድ የፓርላማ አባል የእዚህ ዓይነቱ ማገናዘብ ፈፅሞ አይጠበቅም።
2ኛ) እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው የሚፈሩ የፓርላማ አባላት
በፓርላማው ውስጥ በሙሐዘ ጥበባት ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ላይ ሹመቱን ተቃውሞ ያነሱት የዳንኤል እግዚአብሔርን መፍራቱን ነው።በእነርሱ አገላለጥ የሃይማኖት ሰው ስለሆነ የፕሬስ ድርጅቱ ለኢትዮጵያ ለሁሉም የሚያገለግል ስለሆነ ...የሚል አነጋገር የተጠቀሙ የፓርላማው አባል ነበሩ።ይህ በራሱ አስቂኝ፣ሞራላዊነት የጎደለው እና አድልዎ እና መገለሉ ከጎሳዊ መልክ ይልቅ በኃይማኖትም መሆኑን ያመላክታል።
በመጀመርያ ደረጃ ለኃላፊነት የሚሾም ሰው ሃይማኖትን አክባሪ፣አገሩን ወዳጅ መሆኑ ዋና መስፈርት መሆን የለበትም ወይ? የተወሰኑት የፓርላማ አባላት ሃይማኖቱን መከተሉ እንደሚያዳላ ሊናገሩ ሞክረዋል።እዚህ ላይ ሃይማኖት ያለው ነው ወይንስ የሌለው አድልዎ የሚያውቀው? ሃይማኖትህን ስታከብር ሳዳላ ሰው ባያየኝ እግዚአብሔር ያየኛል ትላለህ።ሃይማኖትህን ሳታከበር እና እግዚአብሔርን ሳትፈራ ሰውንም አታፍርም።ስለሆነም ''ሆዴ ይሙላ፣ደረቴ ይቅላ'' ብለህ በአድሎ የተሞላ ሥራ ላይ ትጠመዳለህ። ኢትዮጵያስ ላለፈው ግማሽ ክ/ዘመን ጠፍቶባት የኖረችው እና ለእዚህ ሁሉ ቀውስ የተዳረገችው እግዚአብሔርን የማይፈሩ ወደ ቤተ መንግስቱ መግባታቸው አይደለም እንዴ? ደግሞስ አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ጀምሮ ያሉት ባለስልጣናት በክርስትና ወይንም በእስልምና እምነት ውስጥ የጠለቁ እና ባመኑበት እምነታቸው ያጠበቁ አይደሉም ወይ? ይህ በራሱ ክፋቱ ምንድነው?
ባጠቃላይ ሃይማኖት ያለው ሰው እግዚአብሔርን ይፈራል።እግዚአብሔርን የሚፈራ ደግሞ አድልዎ አያውቅም።የእዚህ ዓይነት ሰው ከአገሩ አልፎ ስለሰው ልጆች የሚጨነቅ ነው የሚሆነው።አሁን ያለው የኢትዮጵያ ፓርላማ ላለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ የነበረው የለውጥ ሂደት ላይ በጎ ተፅኖ በመፍጠሩ እናመሰግነዋለን።የዛሬው የተወሰኑ (ሁሉም አይደሉም) በሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ላይ በሃይማኖቱ ምክንያት ብቻ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡትን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባልነት ሊያስቆሙ የመሞከራቸው ጉዳይ ግን አንድ ጉዳይ ግልጥ ማድረጉን ሕዝብ እየተነጋገረበት ነው።ይሄውም አድልዎ እና መገለሉ ከጎሳዊ መልክ ይልቅ በኃይማኖትም መሆኑን።ይህ ጉዳይ ኢትዮጵያውያን የበለጠ ሊነጋገሩበት ሁኔታው መንገድ ከፍቷል።የክልል ባለስልጣናት፣የዞን ኃላፊዎች፣የወረዳ ባለስልጣናት፣ሚኒስትሮች፣ኮሚሽነሮች፣የመምሪያ ኃላፊዎች ሲሾሙ መስፈርቱ ምን ነበር? በኢትዮጵያ አንድ ሰው ምን ያህል ዕውቀት፣ልምድ እና ችሎታ ቢኖረውም የኦሮቶዶክስ ክርስቲያን አማኝ በመሆኑ ብቻ ከስልጣን እየተገፋ ነው? ጉዳዩ ጠለቅ ላለ ምርምር ይጋብዛል።የዛሬው የፓርላማው ውሎ አንድ ደውል በኢትዮጵያውያን ጆሮ አቃጭሏል? ኢትዮጵያ የአንዱ ወገን ወይም የሌላው አይደለችም።ሁሉም እኩል መብት አለው።ትውልዱ አገር በጣሳ እየሰፈረ የሚሰጠው ወይንም የሚነፍገው ፓርላማ አይፈልግም።በልበሙሉነት አገሩን መረከብ እንዳለበት ይህ ትውልድ ከምንጊዜውም በላይ ከገባው ዛሬ ነው።
ጉዳያችን ሚድያ፣ኮሚኒኬሽን እና ምክር አገልግሎት
Gudayachn Multimedia, Communication and Consultant
No comments:
Post a Comment