ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, March 18, 2020

በቅርቡ የተመሰረተው እና ከፍተኛ የወጣት ስብስብ እንዳቀፈ የተነገረለት እናት ፓርቲ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ አወጣ ሙሉ መግለጫውን ይዘናል።

Image result for enat party gudayachn
መጋቢት 07/ 2012 ዓ.ም

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የእናት ፓርቲ የአቋም መግለጫ

ተያይዘን እንድንድን እንጂ ተያይዘን እንዳንጠፋ ሁሉም የድርሻውን ይወጣ!

የኖቭል ኮሮና ቫይረስ (COVID-19) በአንድ የውጭ አገር ዜጋ አማካይነት ኢትዮጵያ ውስጥ መግባቱን እና የተጠቂዎችም ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የጤና ሚኒስቴር ባወጣው ይፋዊ መግለጫ አሳውቋል፡፡ ምንም እንኳ መንግሥት የዘገየ ቢሆንም ከዛሬ መጋቢት 07 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለ15 ቀናት በመላ ሀገሪቱ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና ትላልቅ ስብሰባዎች እንዳይካሄዱ መወሰኑ አግባብነት አለው እንላለን። ይህ ወረርሽኝ ለአደጉት ሀገራት እንኳን ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ፣ በሽታውን ይከላከላሉ ተብለው የተቋቋሙ ተቋማት ሓላፊዎችንና ቤተሰቦቻቸውን ጭምር በማይታመን ሁኔታ እየተያዙ እንደሆነ ዐይተናል፣ ሰምተናል፡፡ ይህ ለእንደኛ ዓይነት በምጣኔ ሀብት እድገትና አኗኗር ባህላችን ተጋላጭ ሀገራት ምን ያህል ከባድና ውስብስብ ሊሆን እንደሚችል ማሳያ ነው፡፡ በፖሊሲያችንና ቀረቤታችን ምክንያት “አትምጡ፣ ቅሩብን!” ማለት የሚቻለን ባይሆንም ከመጡ በኋላ ግን አስፈላጊው ክትትል ተደርጓል ብለን አናምንም፡፡ ከጦር መሣሪያ በላይ አውዳሚ የሆነን ችግር እሱን “ተከታተልንበት” ካልነው ጉዞ ያነሰ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡   

የሆነው ሆኖ "ችግር ብልሃትን ይወልዳል" እንዲሉ በእንዲህ ዓይነት ፈታኝ ወቅት ሀገርኛ መፍትሄዎችን እነ አባ መላን ይዞ መሻት፣ በዘርፉ የተማሩ ምኁራንን ወደ መድረክ በማምጣት ቀላል፣ የታሰበባቸውና አዋጭ መፍትሔዎችን እንዲጠቁሙ ማድረግ ይገባል፡፡ በየትኛውም ዓለም ኑሮን ለማሸነፍ የሚኖሩ ጠያቂ የሌላቸው ኢትዮጵያውያንን፣ በተለየ ሁኔታ ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ይበልጥ ጥበቃ እንዲያገኙና ሲጎዱ ፈጥኖ መድረስ ተገቢነቱ ለነገ የሚባል አይደለም፡፡ የማኅበረሰብ አንቂዎችና መገናኛ ብዙኃን ተነሳሽነቱን በመውሰድ የተጠናና በባለሙያ የታገዘ ትንታኔ፣ ማስጠንቀቂያዎችንና የተረጋገጡ ዜናዎችን በማቅረብ የዘመቻ ሥራ መሥራት ለነገ የማይባል ሥራ ነው፡፡ የሃይማኖት አባቶቻችን በእንዲህ ያሉ ፈታኝ ወቅቶች ፈጣሪ ቁጣውን በምኅረት እንዲመልስ፣ ከጭንቁ የመወጫ ጥበቡን እንዲያመላክተን የጋራ ጸሎት በማወጅ የተጀመረው ጥረት በሁሉም ዘንድ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ በየትኛውም ደረጃ የሚጎዱ ሰዎችን ለማገዝ ተከታዮቻችሁን ማነሳሳት ይገባል። 

በሌላ በኩል በእንዲህ ያሉ ጭንቅ ወቅቶች ተጠግተን የምንጸልይባቸው ቤተ እምነቶች ጥቃት አለፍ ሲልም ውድመት ባልተለመደ መልኩ መባባስ እናት ፓርቲን ያሳስባታል፡፡ ልንደኸይ፣ ልንራብ፣ ልንጠማ እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያውያን መንፈሳችን ግን እንዴት ሊወሰድ ይችላል? ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ሀብት ተርፏቸው፣ ሞልቷቸውና ደልቷቸው፣ ካለው ላይ ዘግነው መሣሪያ ገዝተው አይደለም ዘምተው ድል የነሱት፡፡ ይልቅ ተዝቆ የማያልቀውን የአሸናፊነት መንፈሳቸውን መንዝረው ነው ታሪክ ያቆዩልን፡፡ ይህ ከተወሰደብን በእውኑ ምን ይቀረናል? እየጠፋብን አልያም እየተወሰደብን ለመሆኑ ከምልክቶቹ አንዱ የሆነው እየታየ ነውና ያገባኛል በሚል ቁጭ ብለን ብንነጋገር መልካም ነው እንላለን፡፡ ስለሆነም በቅርቡ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ሞረት እና ጅሩ ወረዳ፣ እነዋሪ ከተማ የሙሉ ወንጌል ቤተ ጸሎት ቃጠሎ ከዚህ ለይተን አናየውምና በጥብቅ እናወግዘዋለን፡፡ ቆስቋሽ ምክንያቶች የሚባሉትን የአካባቢው የመንግስት ተሿሚዎች በመነጋገር እንዲፈቱና ጉዳዩ በሕግ አግባብ እንዲዳኝ ማድረግ ሲገባ ዳር ቆሞ በማየት የሆነው እንዲሆን በማድረጋቸው የራሳቸውን አስተዋጽዖ አበርክተዋል ብላ እናት ፓርቲ ታምናለች ፡፡ 
በአጠቃላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ማኅበረሰብ አንቂዎች፣ ሲቪክ ተቋማት፣ ምሁራን፣ የመገናኛ ብዙኃን ሓላፊዎችና ሙያተኞች፣ ይልቁንም መንግስትና የፖለቲካ ፓርቲዎች "ሳይቃጠል በቅጠል" ነውና በእንዲህ ያሉ የፈተና ወቅቶች ልዩነትን ወደጎን በመተው ተያይዘን እንድንድን እንጂ ተያይዘን እንዳንጠፋ በጋራ እንሥራ በማለት ጥሪዋን ታቀርባለች - እናት፡፡   

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን በቸርነቱ ይጠብቅልን!
እናት ፓርቲ

መጋቢት 07/2012 ዓ.ም

ጉዳያችን ሚድያ፣ኮሚኒኬሽን እና ምክር አገልግሎት 
Gudayachn Multimedia, Communication and Consultant

No comments:

ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ታላቅ ተልዕኮ የሚኖረው ሀገራዊ የምምክር ኮሚሽን በተመለከተ ምን ያህል እናውቃለን?

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ኮሚሽን አማካሪ ኮሚቴ አባላትን ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ባካተተ መልኩ አዋቅሯል። በእዚህ ጽሑፍ ስር የሚከተሉት ነጥቦች ምላሽ ያገኛሉ፡  ኮሚሽኑ እንዴት ተመሰረተ?  የኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች እንዴት ተመ...