ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, March 16, 2020

የግብፅ ፓርላማ ዛሬ ማክሰኞ በዓባይ ግድብ ዙርያ ለመነጋገር ድንገተኛ ስብሰባ ጠርቷል።

በእዚህ ዜና ውስጥ በተጨማሪ እነኝህ ሦስት ነጥቦች ላይ መረጃ ያገኛሉ።
  • የግብፅ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሳማህ ሐሰን ሽክሪ ማን ናቸው? 
  • የአረብ ሊግ ተከፋፍሏል 
  • ዲፕሎማሲው ያልሰራላት ግብፅ ቀጣይ ስልቷ ምንድነው?
=================
በግብፅ ፓርላማ የውጪ ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ ካሪም ሐሰን የግብፅ ፓርላማ ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 8/2012ዓም ስብሰባ እንደጠራ ለግብፅ መገናኛ ብዙሃን ገልጠዋል። የፓርላማው ዋና የውይይት ጉዳይ በግድቡ ዙርያ  መሆኑን እና በተለይ ግድቡን በመገንባት ላይ ያሉ የውጪ ኩባንያዎች ላይ ቀጥተኛ እቀባ ለማድረግ መሆኑን እኚሁ የፓርላማ የውጪ ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ አብራርተዋል።በእዚህ መሰረት በኢትዮጵያ በዓባይ ግድብ ላይ የተሳተፉ ኩባንያዎቹ ግብፅ ውስጥ የስራ ውል ካላቸው  መንግስታቸው  እንዲያቆሙ እንዲያደርግ  እና ወደፊትም ሌላ የስራ ውል ግብፅ ውስጥ እንዳይሰጣቸው ለማድረግ ያለመ ስብሰባ ነው።

ስብሰባው እንዲጠራ ያደረጉት የፓርላማ አባላት ናቸው ያሉት የውጪ ኮሚቴው ሰብሳቢ ስብሰባው በተጨማሪ የዓለም ባንክ እና ሌሎች አበዳሪ አገሮች  ኢትዮጵያ በአሜሪካ የቀርበላትን ሰነድ እስካልፈረመች ድረስ ለኢትዮጵያ የሚሰጡትን ብድር እንዲያቆሙ የመጠየቅ ዓላማ እንዳለው ገልጠዋል።ይህ ስብሰባ የግብፁ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰሞኑን ከላይ ታች የሮጡበትን የዲፕሎማሲ ሩጫ ጉዳይም ይገመግማል።ግብፅ ከእዚህ በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዘመንም ለኢትዮጵያ ብድር እንዳይሰጡ የዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን እንዲሁም መንግስታትን ስትወተውት እንደነበር እና ልፋቷ ሁሉ መና እንደቀረ ይታወቃል።በእዚህ ወቅት ይህንን ማንሳቷም ፍሬ የሚያፈራ አይደለም።ምክንያቱም ኢትዮጵያን የአፍሪካ መግብያ በር በማድረግ አዳዲስ ኢንቨስትመንት ለመጀመር እቅድ የያዙ የምዕራብ አገሮች ኢትዮጵያን በእዚህ ወቅት ብድር በመንፈግ በጥቅማቸው ላይ ይቆማሉ ብሎ ማሰብ አይቻልም።በዛሬው እለት ሳይቀር ፋይናንሻል ታይምስ አሜሪካ በኢትዮጵያ የስኩዋር ኢንዱስትሪ ውስጥ በመግባት የቻይና ሚናን መጋፋት እንዳሰበች ፅፏል።ይህ ማለት ቻይናን ከገበያ ለማስወጣት የምዕራቡ ዓለም ሩጫ ላይ ባለበት ወቅት የግብፅ ፓርላማ ውሳኔ ውሃ የሚያነሳ አይሆንም። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የግብፅ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሳማህ ሐሰን ሽክሪ  ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ ፈረንሳይ ድረስ የኢትዮጵያን ግድብ እንዳይደግፉ ሰፊ የዲፕሎማሲ ሥራ ላይ ተሰማርተው ሰንብተዋል።ሚኒስትሩ ካደረጉት ጥረት አንፃር ያገኙት ውጤት ምንድንነው? ተብሎ ቢገመገም ግን ከአረብ ሊግ ''የወረቀት ነብር'' የሆነ የተለመደ ያልሰለጠነ መግለጫ ባለፈ የረባ ምላሽ ከአገራቱ አላገኙም። 

የግብፅ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሳማህ ሐሰን ሽክሪ ማን ናቸው? 



የግብፅ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሳማህ ሐሰን ሽክሪ  በዲፕሎማሲ ዘርፍ ልምድ እንዳላቸው ይነገራል።እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ጥቅምት 20/1952 ዓም እንደተወለዱ የሚነግርላቸው  የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሳማህ ሐሰን ሽክሪ በግብፅ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ሥራ የጀመሩት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1976 ዓም  እንደነበር ጉዳያችን ባደረገችው አጭር ዳሰሳ ለመረዳት ችላለች።ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ በግብፅ ውጭጉዳይ ሚኒስቴር  ለሁለት ዓመት ከሰሩ በኃላ በለንደን የግብፅ ኢምባሲ ሶስተኛ ፀሐፊ ሆነው ተመደቡ።በመቀጠል በ1984 ዓም በአርጀንቲና የግብፅ ኤምባሲ አንደኛ ፀሐፊ ሆነው አገልገዋል።በቀጣይ ዓመታት በኒውዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ኮንሱላር፣ በቅርቡ ያረፉት የቀድሞው የግብፅ ፕሬዝዳንት ሙባርክ የመረጃ እና ክትትል ፀሐፊ፣በኦስትሪያ የግብፅ አምባሳደር፣ በጀነቭ የግብፅ አምባሳደር፣እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2008 እስከ 2012 ዓም በአሜሪካ የግብፅ አምባሳደር እና በ2014 ዓም ጀምሮ እስካሁን የግብፅ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር  ሆነዋል። እዚህ ላይ የግለሰቡ የዲፕሎማሲ ልምድ ማስተባበል አይቻልም።ከእዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ብዙ ልትማር ይገባታል።በተለይ በዘመነ ህወሓት የሳሳው የዲፕሎማሲ የሰው ኃይሏን አሁን በተገቢው መንገድ መልሳ ማጠናከር ይገባታል።እዚህ ላይ የረጅም ጊዜ የዲፕሎማሲ ልምድ ያላቸው ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ያለውን ክፍተት ለመሙላት የሚያሳዩት ተግባር አገር አኩሪ ነው።በቅርቡ በአፍሪካ አገሮች አንፃር በኬንያ እና ዑጋንዳ ያደረጉት ጉብኝት ተጠቃሽ ነው።

ለግብፁ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህ ሁሉ የስራ  ልምድ ግን በኢትዮጵያ ላይ ያለሙትን ለመፈፀም የሚፈልጉትን ውጤት አላመጣላቸውም።የሚንስትሩም ሆነ የመንግስታቸው ዋና ዓላማ በዲፕሎማሲው  ረገድ ግብፅ አጋር እንዲበዛላት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን የማስፈራራት ዓላማም ነበረው።ሆኖም  የዘመኑ ተለዋዋጭ የዓለም ሁኔታ እና ኢትዮጵያ እያሳየች ያለው ውስጣዊ አንድነት እንዲሁም ብዙ አገሮች በእዚህ ጊዜ ከኢትዮጵያ ጋር ለመጣላት ዝግጁ ያልሆኑበት በርካታ ምክንያቶች እና አፍሪካ ላይ ያላቸው ፍላጎት በኢትዮጵያ ተፅኖ ውጪ እንደማይሆን መረዳታቸው የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው ዲፕሎማት ጉዳዩ ቀላል እንዳልሆነ ሳይገባቸው አልቀረም።የዩጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ከግብፅ ጋዜጠኛ ጋር በቅርብ ባደረጉት ቃለ ምልልስ  ''የአባይ ውሃ ምንጭ ያለው  እዚህ  አፍሪካ  ነው፣ ግብፅ ግን የምትዞረው መካከለኛው ምስራቅ እና ሌሎች አገሮች ነው።ከእዚህ ይልቅ ግብፅ ብዙ ጊዜዋን ውሃው ከሚመነጭበት ከኢትየጵያ እና አፍሪካ አገሮች ጋር ጊዜ ብታጠፋ ይሻላት ነበር'' እንዳሉት ግብፅ ጊዜዋን እያጠፋች ያለችው መካከለኛው ምስራቅ እና አሜሪካ ላይ ነው።

ግብፅ የዓባይ ምንጭ የምገኝባትን አፍሪካ ትታ የማይመለከታቸውን የመካከለኛው ምስራቅ እና አሜሪካንን ስትማፀን መቅረሟ ፍሬ እንዳላመጣ ዘግይተውም ቢሆን በማውቅ ይመስላል ግብፅ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ ሱዳንን ማባባል የያዘችው እና አዲስ የውይይት ጥረት እንዲጀመር፣ሱዳን የማደራደር ጥረት እንድታደርግ በሹክሹክታ መጠየቅ የያዘችው።ሱዳን አሁን ባለባት የውጪ ምንዛሪ እጥረት እና የሽግግር መንግስቱ ካሉበት በርካታ አጣዳፊ ስራዎች አንፃር ጉዳዩ እንዲረግብ መፈለግዋ  አልቀረም።በሌላ በኩል የሱዳን በአረብ ሊግ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያን የሚያወግዝ ሰነድ ላይ አልፈርምም በማለቱ ሳውዲ አረብያ ለሱዳን ልትሰጥ ያሰበችውን ገንዘብ እንደያዘችባት ነው የተሰማው።ገንዘቡ እንዲለቀቅ ደግሞ ግብፅ ሳውዲን ለማግባባት ለሱዳን ቃል በመግባት ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር እንድታደራድራት ግብፅ አልጠየቀችም ለማለት አይቻልም።በአረብ ሊግ አንፃር ሱዳን የወሰደችው ውሳኔ ግን ትክክለኛ እና ሳይንሳዊ ውሳኔ ነው።ሱዳን ያለችው ቃል በቃል ''አፍሮ አረብ በኢትዮጵያ እና በግብፅ የግድብ ጉዳይ ፈፅሞ መግባት የለበትም።ከገባም ገለልተኛ መስመር ይዞ የማስማማት ሚና ብቻ ነው።ይህ ካልሆነ ከፍተኛ ቀውስ ከመፍጠሩ በላይ ራሱ የአረቡ ዓለምን የሚከፋፍል አደገኛ ሁኔታ ይፈጥራል።የሌሎች ኃይሎችንም ይጋብዛል'' ነበር ያለችው። ይህ አባባል በረጅሙ ብተነተን ለሱዳን ትክክለኛ አባባል ራሱን የቻለ መፅሐፍ ይወጣዋል። ረጅም ልምድ አላቸው የተባሉት የግብፁ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን እያወቁ ልሞክረው ዓይነት ሩጫ ሱዳን እንዳለችው ያመጣላቸው ለውጥ የለም። ሌላው ቀርቶ ሞቅ ባለ መንገድ የተቀበሏቸው የተባበሩት ዓረብ ኢምረቶች ባለስልጣናት የግብፁ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደ አየር መንገድ ሲያመሩ ለኢትዮጵያ ሊሰጡ የነበረውን ለአነስተኛ እና ጥቃቅን ንግድ መርጃ የሚሆነውን የአንድ መቶ ሚልዮን ዶላር ገንዘብ ጉዳይ እስካሁን አልሰረዙም ይልቁንም ከኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እና ገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመፈራረም አፀኑት።  

የአረብ ሊግ ተከፋፍሏል 

ግብፅ ድምጿን አጥፍታ ኢትዮጵያን ልታስፈርም የፈለገችው ሰነድ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ከተነቃባት በኃላ በቀጥታ ፊቷን ያዞረችው ወደ አረብ ሊግ ነበር።አረብ ሊግ መፎከር እና ምክንያት እና ሞራል ያለሽ  የዲፕሎማሲ አካሄዱ የታወቀ ስለሆነ እና በ21ኛው ክፍለ ዘመንም ልክ የአረብ እስራኤል ጦርነት ዘመን የሚያስብ ስለሆነ የአረብ ሊግን ውሳኔ ተከትሎ የዲፕሎማሲ ዕይታውን የሚቀይር አገርም ሆነ አህጉራዊ ድርጅት የለም።ምክንያቱም የአረብ ሊግ በራሱ ሌላው ቀርቶ የልብያና የሶርያን ጉዳይ በአግባቡ ይዞ ከኃያላን አገሮች ጣልቃ ገብነት ማዳን ያቃተው ደካማ አስተሳሰብ የተሞላ ድርጅት መሆኑ ፀሐይ የሞቀው ነው። 

ግብፅ የአረብ ሊግ መግለጫ ከአጋርነት ያለፈ ሥራ እንደማይሰራ ምናልባት ከኢትዮጵያ ጋር የሚነሳ ግጭት ካለ ብቻ ከጎኗ እንደሚቆም ከማሰብ ባለፈ አሁን ለምትፈልገው ሥራ እንደማይደርስ ገብቷቷል። በሌላ በኩል ራሱ የአረብ ሊግ ውስጡ የተከፋፈለ ለመሆኑ ከግብፅ የበለጠ የሚያውቀው የለም። ለመከፋፈሉ ሁለት ማስረጃዎች መጥቀስ ይቻላል።አንዱ በሶርያ፣በሊብያ እና በየመን ጉዳዮች የአረብ ሊግ አባላት ወጥ የሆነ ዕይታ የሌላቸው መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በቅርቡ በደማስቆ የአረብ ሊግ  ቢሮ ለመክፈት ጉዳይ ላይ ሳይቀር ዱላ ቀረሽ ፀብ ተነስቷል።ሌላው የመክፋፈሉ ምልክት ደግሞ የግብፁ ውጪ ጉዳይ  ሚኒስትር የመካከለኛ ምስራቅ የሰሞኑ ጉዞ ነው።

 የአረብ ሊግ በሰሞኑ መግለጫ እንዲሁም ቀደም ባሉት ወራት የአረብ ሊግ ፓርላማ ኢትዮጵያን ለማስፈራራት የሞከረባቸው መግለጫዎች እያሉ፣የግብፁ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን ደብዳቤ ይዘው በሊጉ አባል አገሮች ዋና ከተሞች ሲዞሩ ነው የከረሙት።ይህ ማለት የአረብ ሊግ የሚያወጣው መግለጫ የመካከለኛው አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና መንግስታትን ሙሉ የተስማማ ሃሳብ እንዳልሆነ ያሳያል።ለእዚህ ነው የግብፁ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአረብ ሊግ መግለጫም በኃላ በየአገራቱ እየዞሩ  መንግስታቱን መማፀን የያዙት።ይህ ማለት ግን ከመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያን እንደ ስጋት የሚያዩ የዘመናት የኢትዮጵያ ባላንጣዎች የሉም ማለት አይደለም።እነኝህ አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ዱላ የምያስነሳ ማናቸውም ምክንያት ካገኙ ምንም ከማድረግ የሚመለሱ አይደሉም።

ኢትዮጵያን በተመለከተ የግብፅ ቀጣይ ስልት ምንድነው?

ግብፅ ሰሞኑን የዞረችበት የዲፕሎማሲ ጥረት ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ ፈረንሳይ የዘለቀ ቢሆንም ከአገራቱ የቀዘቀዘ ስሜት፣በውስጣቸው ትኩረት የሚሰጡት በርካታ ውስጣዊ ጉዳይ መኖር፣ሰሞኑን የተነሳው የኮሮና ቫይረስ ብሔራዊ አደጋ ከመሆኑ አንፃር እና የነዳጅ ዋጋ እጅግ በመውረዱ ሳብያ (ዛሬ በበርሜል እስከ 20 ዶላር) መውረድ ሳብያ የግድቡ ጉዳይ ግብፅ የፈለገችውን  ያህል ትኩረት ሊስብላት አልቻለም።ጉዳዩ ትኩረት አለመሳቡ በራሱ ደግሞ ለኢትዮጵያ የሚያመጣው ጥቅም አለ። ይሄውም በእዚህ ወቅት በፍጥነት ግድቡን የመገንባቱን ሂደት ማፋጠን እና በቶሎ መጨረስ ነው። ይህ በእንዲህ እያለ የግብፅ ቀጣይ ስልት ሊሆን የሚችለው በኢትዮጵያ የውስጥ ክፍተቶች ውስጥ መስራት እና ኢትዮጵያን ከውስጥ ለማተራመስ መስራት ነው።

እዚህ ላይ የወታደራዊ እርምጃው ግብፆች ሊሞክሩት አይችሉም።ምንያቱም አንዳች አይነት የወታደራዊ ሙከራ ቢደረግ 85% የዓባይ ወንዝ የሚመነጭባት አገር ኢትዮጵያ በውሃው ላይ ሌላ የፈለገችውን አማራጭ የአፀፋ እርምጃ የማትወስድበት ምንም ምክንያት የለም። ይህ ደግሞ ከረጅም ጊዜ አንፃር ለግብፅ የሚያዋጣ አይደለም። ስለሆነም የግብፅ ዋነኛ ሥራ የሚሆነው በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ገብቶ በእጅ አዙር መፈትፈት ነው። ይህንን ደግሞ እየሄደችበት ለመሆኑ በአሜሪካን አገር መሰረቱን ያደረገው ዘሀበሻ በዛሬ ዜናው  የሱዳኑ የቀድሞ የስለላ ከፍተኛ ባለስልጣን  እና ከቀድሞው የኢትዮጵያ ደህንነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ ጋር የቅርብ ወዳጅ ነበሩ የተባሉት ሰው ሜጀር ጀነራል ሳላህ አብደላ ጎሽ  ግብፅ መግባታቸው መረጃው እንደደረሰው ዘግቧል። ባለሥልጣኑ  በዋናኝነት ከግብፅ የደህንነት መስርያቤት ጋር በጋራ የሚሰሩት ኢትዮጵያን የማተራመስ ሥራ ለመስራት መሆኑን ዜናው አክሎ ዘግቧል።

ይህ የግብፅ ተግባር ደግሞ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ እጃቸውን ማስገባታቸው እና ኢትዮጵያ አንገቷን ቀና አድርጋ እንዳትሄድ ለማድረግ የሙሉ ጊዜ ሥራ ካደረገችው ሰንብታለች።ስለሆነም የግብፅ ቀጣዩ ስልት ከዲፕሎማሲው ጎን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ገብቶ ኢትዮጵያን መረበሽ  መሆኑን መረዳት ይገባል። 

ባጠቃላይ ግብፅ እንደምንም አግባብታ ኢትዮጵያን በግድቡ ዙርያ ልታስፈርም የፈለገችው ሰነድን ኢትዮጵያ ባትፈርምስ የሚል አማራጭ ሃሳብ ሳትይዝ ኢትዮጵያ አዘናግታ ከመጨረሻው ስምምነት መቅረቷ በግብፅ መንግስት ውስጥ መደናበር አልፈጠረም ለማለት አይቻልም።ይህ መደናበር ደግሞ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ ይዘው ከአገር አገር እንዲዞሩ ማድረጉ ጥሩ ማሳያ ነው።ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከዙረቱ በኃላ የኢትዮጵያን ቦታ በሚገባ የለኩት ይመስላል።ኢትዮጵያን በአሁኑ ጊዜ መንካት እስራኤልንም ሆነ ሩስያ የሚይዙትን መስመር ለማወቅ አስቸጋሪ መሆኑ ለግብፅ መንግስት ግልጥ ሆኗል። ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የአፍሮ-ዓረብ ዲፕሎማሲ ሚዛን መሆኗን ያለማወቅ ችግር በግብፆች ውስጥ ነበር። በተለይ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ሰላም መሆኗ በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ የሚረማመድ አገር ቶሎ ለማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል ለግብፆቹ።ስለሆነም አሁን ግብፅ ትንሽ ጊዜ መግዛት እና ኢትዮጵያን ሊያጠቃ የሚችል ሁነኛ ጠላት ማፈላለግ  እንዳለባት ገብቷታል።ለእዚህ ደግሞ የውስጥ ውጥረቶች እና ቅራኔዎችን በደንብ መተንተን እና ማጥናት እንዳለባት ገብቷታል። ለእዚህም ልምድ አላቸው የተባሉትን የቀድሞ የሱዳን የደህንነት ከፍተኛ ባለስልጣን ወደ አገሯ ተርታ ለመመካከር ወስናለች። ይህ በእንዲህ እያለ ግን ግብፅ በአርባ ዓመት ታሪኬ አይቼ አላውቀውም ያለችው የጎርፍ እና የመብረቅ አደጋ ሃያ ሰው እንደገደለባት ገልጣለች።ግብፅ ውሃው ከላይ ነው የሚመጣው።የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ መንግስት የግብፅን ሕዝብ የመጉዳት ዓላማ እንደሌለው ይልቁንም ግድቡ መሰራቱ ለግብፅም ጥቅም እንደሆነ እንዲያውቁት ደግሞ ማን በነገራቸው?

ጉዳያችን ሚድያ፣ኮሚኒኬሽን እና ምክር አገልግሎት 
Gudayachn Multimedia, Communication and Consultant


No comments: