ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, March 16, 2020

ከኢትዮጵያ አንፃር በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሊታዩ የሚገባቸው ሶስቱ የኮሮና ቫይረስ መተላለፍያ መንገዶች (ጉዳያችን ልዩ )


ጉዳያችን ሚድያ፣ኮሚኒኬሽን እና ምክር አገልግሎት 
Gudayachn Multimedia, Communication and Consultant

ዓለማችንን እያናወጠ ያለው የኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያም ስጋት መደቀኑ አይቀርም።ከእዚህም አንፃር የበሽታው አደጋ የሚመጣበትን መንገድ የዓለም ጤና ድርጅት እና የምዕራብ አገሮች በሽታው ይመጣበታል ብለው ከተቆሙባቸው መንገዶች ብቻ የበሽታውን መምጫ መንገዶች መገደብ ስህተት ነው።የዓለም ጤና ድርጅት እና የምዕራብ አገር ሚድያዎች የሚያሰራጩት በሽታውን የምንከላከልባቸው መንገዶች አብዛኛው የዓለም ሕዝብ ከሚኖርበት አኗኗር ዘይቤ ጋር በተለይ ሁኔታዎች ተሟልቶለት ከሚኖረው ሕዝብ አንፃር የምጎድሉትን መንገዶች ብቻ ነው።ስለሆነም እስካሁን ባብዛኛው እየተነገር ያለው እጅ መታጠብ፣ሲያስነጥሱ ወደሌላ ሰው እንዳይተላለፍ የሚደረጉ ጥንቃቄዎች እና በትንፋሽ እንዳይተላለፍ ጥንቃቄ ማድረግ የሚሉት ይጠቀሳሉ።

ሆኖም ግን እነኝህ ምክሮች እና ፖስተሮች እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ጋር ካሉት የባሕል እና የአኗኗር ዘይቤ አንፃር የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቃኝቶ ተጨማሪ እርምጃዎች መውሰድ አለበት።ከእነኝህ እርምጃዎች ውስጥ ሶስቱ ከኢትዮጵያ አንፃር መቃኘት ያለባቸው ይመስሉኛል። እነርሱም -

1) የጥርስ መፋቅያ እንጨት እና የጥርስ ቡርሽ አጠቃቀም 

በኢትዮጵያ በከተማ በአዟሪዎች እየዞሩ የሚሸጡት እና ከፍተኛ የእጅ ንክኪ ያለባቸው፣ቀኑን ሙሉ ለአቧራ ተጋልጠው የሚውሉ የጥርስ መፋቅያ እንጨቶች አሉ።በገጠርም እነኝህን  እንጨቶች የሚጠቀሙ ሁሉ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው።ጥንቃቄው ለምሳሌ በጥቂቱ በሙቅ ውሃ አፅድቶ መጠቀም ሊሆን ይችላል።ሌላው በከተማም ያለው ይህ በውጭ ያሉትም ችግር ሊሆን ይችላል። የጥርስ መፋቅያ ቡርሾች ናቸው።እነኝህ ቡርሾች የሚቀመጡበት አቀማመጥ በተለይ ቫይረሱ ለ12 ሰዓታት ድረስ በውጭ ከመቆየቱ አንፃር ከመጠቀማችን በፊት ማፅዳት ፣ተጠቅመን ስናስቀምጥም በአግባቡ መሆን እንዳለበት መረዳት ይገባል።

2) የጆሮ ኩክ ማፅጃ አጠቃቀም 

በኢትዮጵያ በተለይ በገጠር ፣በከተማም ያለ ችግር ነው የጆሮ ኩክ ለማፅዳት ማናቸውንም ነገር የመጠቀም መጥፎ ልማድ አለ።ተማሪዎች በከተማም ጭምር  ጆሮን ለማፅዳት በእስክርቢቶ ክዳን፣በዶሮ ላባ፣እና በመሳሰለው መጠቀም የተለመደ ነው።ይህ የቫይረሱን ወደ ሰውነት ክፍል የመግባት እድሉን ይጨምረዋል።በተለይ በሽታው ከፍተኛ የሙቀት ሁኔታ ስለማይችል እንደጆሮ፣አፍንጫ እና ጉሮሮ ያሉት አካባቢዎች ተስማሚ የሙቀት ልክ ለቫይረሱ ስለሚሰጡት አመቺ ቦታዎቹ እንደሆኑ ባለሙያዎች ይመክራሉ።ስለሆነም በኢትዮጵያ ከእዚህ ልማድ አንፃር ምክር የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

3) ጫት

በኢትየጵያ እየተስፋፋ የመጣው እና በአረብ እና የአውሮፓ አገራት በአደገኛ ዕፅነት የተመደበው ጫት አንዱ የኮሮና ቫይረስ መተላለፍያ እንደሚሆን መገመት ይቻላል። ጫት በአንድ ቀን ውስጥ ከሚቆረጥበት ማሳ ጀምሮ እስከ ተጠቃሚው ሰው እስከሚደርስ ብዙ ያልታጠቡ እጆች እየነካኩት የሚያልፍ ነው።መጨረሻ ላይ ተጠቃሚዎች አጠብነው ብለው በውሃ ቢይርሱትም የኮሮና ቫይረስን ለማጥፋት እንደማይችል የታወቀ ነው።ስለሆነም በኢትዮጵያ አንዱ እና ዓይነተኛ የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ጫት እንደሚሆን መገመት ቀላል ነው። አንዳንድ አክትቪስቶች እጅ መታጠብ እንዴት እንደሆነ ከሚነግሩን የምያስፋፉትን እና እራሳቸውም እየቃሙ ሲያስተዋውቁት የከረመውን ጫት ጎጂ መሆኑን ለሕዝብ ቢነግሩት ጥሩ ነበር።

ባጠቃላይ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የአንድ በሽታ መከላከያ መንገዶችን ቀጥታ የዓለም ጤና ጥበቃ ወይንም የምዕራብ አገሮች የጤና  ፖስተሮች እንዳለ ከመጠቀም ባለፈ በኢትዮጵያ አንፃር ካለው ልማድ የበለጡ አደገኛ ሁኔታዎች አሉ ወይ? ብሎ ጠይቆ የምክር አሰጣጡን ሁኔታ መቃኘቱ ተገቢ ነው በማለት ጉዳያችን ሃሳቧን ታካፍላለች።

======================/////=============


No comments: