ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, March 20, 2020

በኮሮና ቫይረስ ሳብያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት እንዳይታጎል ቴክኖሎጂ መጠቀም!


የጉዳያችን ወቅታዊ መልዕክት! ንቁ! ትጉ!

በእዚህ ጽሁፍ ስር -

+ የኦስሎ መ/ቅ/ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን የቀጥታ ስርጭት አገልግሎት የሚያገኙበት ሊንክ ያገኛሉ።
+ ምዕመናን የቀጥታ ስርጭት በቤታቸው ሲከታተሉ እንዴት ሆነው መሆን አለበት? የሚል አጭር መረጃ ያገኛሉ።

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳብያ  ከህዝብ ንክኪ ለመታደግ እና የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በውጪ አገራት የሚገኙ የዕምነት ቦታዎች በሙሉ ምዕመናን እንዳይገኙ መደረጉ ይታወቃል።ይህ ማለት ግን ለአገልግሎቱ ሌላ አማራጭ የለም ማለት አይደለም።ከችግሩ አንፃር የቤተ ክርስቲያን አባቶች እና አገልጋይ ምዕመናን ከመቼውም ጊዜ በላይ በተቻለ መጠን ለምዕመናን አገልግሎት ለማድረስ መጣር ያለባቸው ጊዜ አሁን ነው።ይህ ካልሆነ ትልቅ አደጋ በምዕመናን ሕይወት ላይ እንደሚደቀን በጥብቅ ሊያስቡት ይገባል።ምዕመናን ከልጆቻቸው ጋር ከቤት ሲውሉ ከመንፈሳዊው ጉዳይ ይልቅ አልባሌ ነገሮች እየተመለከቱ እንዲውሉ የሚያደርግ ከባድ የመንፈስ ዝለት እንዳይደርስባቸው እና በስጋም ሆነ በመንፈስ እንዳይጎዱ አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎቱን በቀጥታ ስርጭት እንዲደርሳቸው ማድረግ አለባቸው።

ምዕመናን የቀጥታ ስርጭት እንዴት መከታተል አለባቸው?


ማሳሰቢያ = ከእዚህ በታች ያለው የጉዳያችን የግል ሃሳብ እንጂ የቤተ ክርስቲያን ስርዓት አንቀፅ እየተጠቀሰ የተፃፈ አይደለም።ነገር ግን የእንዲህ አይነት አዲስ ነገር ሲገጥም ቀድሞ መንገዱን ከማመልከት አንፃር ብቻ የተጠቆመ ነው።


ምዕመናን በቤታቸው የቀጥታ የቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት  ስርጭት ሲከታተሉ የሚከተሉትን ነጥቦች መዘንጋት የለባቸውም።እነርሱም -


1) ተግተው እና ነቅተው መከታተል 

የቀጥታ ስርጭቱ ለምሳሌ ትምህርት፣ምህላ፣ወይንም ቅዳሴ ሲሰራጭ ቤታቸው ያሉ ሌሎች ሚድያዎች ማለትም ቴሌቭዥን፣ስልክ እና የመሳሰሉትን አጥፍቶ በህሊና ቤተ ክርስቲያን እንዳሉ አድርጎ መከታተል።ቅዳሴው እና ምህላውን ቢችሉ ከቤተሰብዎ ጋር ጫማ አውልቆ ስዕለ መድኃኔዓለም ወይንም ቅዱሳን ፊት ቆሞ በአንቃዕዶ ህሊና ልክ ቤተ ክርስቲያን እንዳሉ አድርጎ መከታተል።

2) ከቤተሰብ ጋር ቀድሞ መወያየት

የቀጥታ ስርጭቱ ሲደረግ ቤት ውስጥ እንዴት መሆን እንዳለበት ቀድሞ ከቤተሰብ ጋር መምከር።ለምሳሌ ከእዚህ በፊት ከቤተሰብ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን አዘውትሮ መሄድ ልማድ የሌለው ሰው ዛሬ ቆመህ አስቀድስ ወይንም ምህላ ቁም ማለት ሊከብደው ይችላል።ስለሆነም  በበጎ ህሊና ቀድሞ መነጋገር ካልቻለ አጭሩን የቀጥታ ስርጭት ጊዜ ቴሌቭዥን በማጮህ ወይንም በሌላ እንዳይረብሽ መነጋገር፣መቆም ካልቻለ ተቀምጦ እንዲከታተል መምከር ይህም ካልተቻለ ልጆች እና ከቤተሰቡ ፈቃደኛ የሆኑት በሚከታተሉበት ጊዜ ቢቻል ሌላውን የቤት ሥራ እያገዘ እንዲቆይ  ወይንም ሌላ አማራጭ ላይ  መመካከር።ሁሉ በፍቅር መሆን ስላለበት እንጂ በተቻለ ከቤተሰቡ ማንም ሳይነጠል በኅብረት አገልግሎቱን መካፈል በረከት  ስላለው  በተቻለ መድከም የሚገባው በህበረት መሳተፉ ነው።

ለማጠቃለል፣ይህ የፈተና ጊዜ ነው።ስለሆነም በፈተና ጊዜ የበለጠ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እና ያሉትን  አማራጮች ሁሉ ተጠቅሞ መትጋት ይገባል።ይህ ካልሆነ ሰይጣን የበለጠ የምያሰንፍበትን መንገድ እንደሚያስብ አውቀን ለእያንዳንዱ የቀጥታ ስርጭት ህሊናችንን ሰብስበን መከታተል፣ቤተሰባችንንም ሆነ ልጆቻችንን ከመንፈሳዊው አገልግሎት እንዳይርቁ ልንጠነቀቅ ይገባል። በሌላ በኩል ከእዚህ በፊት ቤተ ክርስቲያን ሄደን ለመገልገል ዕድሉን በተለያየ ምክንያት ያላገኘን፣ እግዚአብሔር እቤታችን ድረስ መጥቶ ሲፈልገን እኛ ኮምፑተር ከፍተን ለመገልገል ሰንፈን ከተኛን የራሳችን ስህተት መሆኑን ልንረዳ ይገባል።

በኦስሎ መካነ ቅዱሳን ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን የቀጥታ ስርጭት የሚኖርባቸው ሰዓታት እና ቀን ከእዚህ በታች ይመልከቱ።

1) በዓቢይ ፆም ወቅት ዘወትር ረቡዕ እና ዓርብ በኦስሎ ሰዓት ከ17 ሰዓት (5pm) ጀምሮ የምሕላ ጸሎት
2) ዘወትር ዕሁድ ማለዳ  በኦስሎ ሰዓት አቆጣጠር ከ7 ሰዓት (7am) ጀምሮ የቅዳሴ ስነ ስርዓት የሚተላለፍ ሲሆን
ሁሉንም ለመከታተል በእዚህ ድረገጽ ከፍተው መከታተል ይችላሉ።

ድረ ገፁ http://www.eotcnor.no/  ወይንም 
http://www.eotcnor.no/live   የሚለውን ቢጫኑ መክፈት ይችላሉ።



ጉዳያችን ሚድያ፣ኮሚኒኬሽን እና ምክር አገልግሎት 
Gudayachn Multimedia, Communication and Consultant

No comments:

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...