አሁንም ስለ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳይ በጣም በጥልቅ አስባለሁ።የችግሩ ብቻ ሳይሆን የመፍትሄው አካልም እኔ እራሴ እንደሆንኩ አስባለሁ።የብዙዎቻችን ችግር ችግሩን የማንሳት እንጂ የመፍትሄው አካል ለመሆን ምን ላድርግ የሚል ኃላፊነት አለመውሰድ ነው።በእዚች እድሜዬ በቻልኩት ሁሉ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳይ ከመከታተል የቦዘንኩበት ወቅት የለም።መጨረሻ ላይ ግን አንጀቴን የሚባለኝ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው።ሕዝብ ስል በፖለቲካው ዙርያ ተዋናይ የሆኑትን ብቻ አደሉም።ፖለቲካ ውስጥ ገብተው የሚሰሩ ከየትም አቅጣጫ እንበለው እነርሱም ፍቅር የሚሉት የእራሳቸው ነጥብ ይኖራል።ፖለቲካ ላይ ለጥቅም እና ለዝና ከገቡት ውጭ ሌሎች የህዝብ ፍቅር አስገድዷቸው የገቡ ናቸው ብዬ አምናለሁ።ይህንን መካድ አይቻልም።
አሁን በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ የሚታዩኝ አራት ችግሮች በደንብ እይተንፀባረቁ ነው።
1/ የኢትዮጵያ ዘለቄታ የፖለቲካ መፍትሄ ላይ አቅዶ አለመስራት፣
2/ ኢትዮጵያዊነትን ከማጠንከር ይልቅ ኢትዮጵያዊነትን የሚያላሉ ተግባራት ላይ መሰማራት፣
3/ አሁን ያሉት ልዩነቶች አልበቃ ብሎ ለነገ ሌላ፣አዲስ እና ትኩስ ልዩነት ለመፍጠር መሞከር፣
4/ የነገዋ ኢትዮጵያ አሁን ካለባት የአምባገነን እና የጎሳ ፖለቲካ ወጥታ በትክክለኛ ፍትህ፣ዲሞክራሲ እና ሁሉን ያሳተፈ እንድትሆን ከመጣር ይልቅ አሁን ጀምሮ የእራስን ጎሳ እያገነኑ የነገ መሪ እኔ ነኝ ማለት፣
እነኝህ አራት ችግሮች የኢትዮጵያ የወቅቱ ችግሮች ናቸው።ችግሮቹ አሁን በስልጣን ላይ ባለው ስርዓት ብቻ የሚቀነቀኑ ሳይሆኑ በነገዋ ኢትዮጵያ ላይም ተመሳሳይ ችግር እንዲፈጠር ሕልም እና ምኞት እንዳላቸው ከማኅበራዊ ድረ-ገፅ አንስቶ እስከ መድረክ ንግግሮች ድረስ የሚያንፀባርቁ አካላት በትክክል እየታዩ ነው።ከአሁኑ ይልቅ በነገው ላይ የሚሰራው ሥራ ነው አሳሳቢው።¨ከትናንት ብንዘገይ ከነገ እንቀድማለን¨ የምትለው አባባል ልትዘነጋ አይገባም።የኢትዮጵያ ነገር ውስጣችንን የሚያቆስለን በድፍረት ልንጋፈጣቸው የሚገቡ ብዙ ሺህ ጉዳዮች ከፊታችን እንዳሉ መዘንጋት የለብንም። የፌስ ቡክ ንትርኩ አንዳች ጉዳይ አይፈይድም።ይልቁንም ለነገዋ ኢትዮጵያ ሁሉንም ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሳይል የሚበክል የጎሳ ማግነን ሃሳቦች አሁን ያለነውን ብቻ ሳይሆን መጪውን ትውልድ እንዳይበክል መስራቱ ነው ቁም ነገሩ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የነገ መጪ እጣ ግን አንገብጋቢ ነው።መፍትሄ የሌለን ሕዝብ ልንሆን ፈፅሞ አንችልም።ነገን አሻግረን ከተመለከተን የመፍትሄው አካል የሆነው የዛሬ የተግባር ግዴታችን ይገባናል።እውነትን፣ፍቅርን እና ፅናትን አለመያዝ ብቻ ነው የመፍትሄ ድሃ የሚያደርገን።ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ስናወራ የነገውን የሚያስብ እንጂ አሁን ላለው ስሜት ማስታገሻ ብቻ መሆን የለበትም።
አንድ ማወቅ የሚገባን ጉዳይ የሥርዓት ለውጥ አይቀርም።በባሌም በቦሌም ብሎ አይቀርም።ለለውጥ የሚሰራው ይስራ።ለለውጥ የሚሰራው በኃላ ይደርሳል ያላቸው ተግባራት ግን መስራት የሚገባቸው ብዙ ሺዎች ቁጭ ብለው ኢትዮጵያን አይን አይኗን ማየታቸው ነው ጥፋቱ።ለውጥ እንደሚመጣ እያወቅን ከአሁኑ ኢትዮጵያችን ነገ ብቻ ሳይሆን ከእዝያ በኃላም ደምቃ እንድትገኝ በእዚህም ሂደት ሁሉም ኢትዮጵያን ያለ ሁሉ እርስ በርሱ ሳይናከስ እና ማኅበራዊ ሰላሙ ከአሁኑ በባሰ መልኩ ሳይደፈረስ እንደ ሀገር መቀጠሉ ነው ወሳኙ ቁም ነገር። ይህ ደግሞ ከአሁኑ እየተገነባ ካልመጣ እና ሁሉም ወገን በጋራ የሚያምንባቸው ሃሳቦችን እያጎላን ካልመጣን ነገ በይድረስ ይድረስ የሚሰራ አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ በእውነትም ያሳዝናል (ከእራሴ ጨምሮ)። ምሁራኑ አዲስ ሃሳቦች አፍልቆ፣ ከስልጣን ጥማት እና ከማታለል ፈፅሞ በራቀ መልኩ የሕዝቡን ደካማ አስተሳሰቦች እያበረቱ፣እይታውን እያጠነከሩ እና ከክፍለ ዘመን ወደ ክፍለዘመን በቀላሉ የምትሸጋገር ኢትዮጵያን ለማምጣት አሁን ላይ የመፍትሄ ሃሳብ አምጠው መውለድ እና ወደ ሥራ መግባት የምሁራኑ የውዴታ ግዴታ ነው።የኢትዮጵያ ምሁራን ከሀገር ቤት እስከ ባህር ማዶ ያላችሁ ለነገዋ ኢትዮጵያ የሚሰራ የመፍትሄ ሃሳብ በቶሎ ውለዱ እንጂ የእኔ ጎሳ ነገ ኢትዮጵያን ይገዛል ብላችሁ ያለፈ ችግር የሚደገምባት ኢትዮጵያን እንድናይ አታድርጉ።ይህንን ሃሳብ በሚገባ ተንጠርጥሮ መቅረብ እንዳለበት አምናለሁ።ወደፊትም በጊዜው ጊዜ ለማቅረብ እሞክራለሁ።
ኢትዮጵያን መውደድ ማለት፣ህዝብን መውደድ ማለት የእራስን ጎሳ ብቻ ማምለክ አይደለም።የምንኖረው 21ኛው ክ/ዘመን ነው።ይህ የዘመን ቁጥሩ ብቻውን ከጎሳ የፀዳ ዓለም እንደማያሳየን የታወቀ ነው።ዓለም የፈለገውን ሊዘፍን ይችላል።እኛ ኢትዮጵያውያን ግን ከጥንት ጀምሮ አለምን ያስተማርነው ብዙ የፍቅር ታሪኮች አሉን።በወቅቱ የተለየ እምነት ይዘው ከመካ የመጡትን የመሐመድ ቤተሰቦች ጀምሮ እስከ ከዓለም ዳር በክርስትናቸው ምክንያት የተሰደዱትን ዘጠኙን ቅዱሳን የተቀበልን እስከ አሁን ድረስም አሻራቸውን በኢትዮጵያ እንዲያሳርፉ እና አካላችን እንዲሆኑ ያደረግን ድንቅ ህዝቦች ነን።ዓለም በጎሳ ስላበደ አሜሪካን ሀገር የጥቁር እና የነጭ ችግር ስላለ፣በኢትዮጵያ ታሪክ ያልታየ የጎሳ መንግስት አራት ኪሎ ላይ ስልጣን ስለያዘ መሰረታዊ የአስተሳሰባችን መጠን ሊዛነፍ አይገባም።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከትግራይ እስከ ሞያሌ፣ከአኮቦ እስከ ፈርፈር ግራ ተጋብቷል።የሚሰማው ሁሉ ጆሮውን እየጠለዘው ልክ አሁን ያየውን ችግር ያህል ነገም እንዳይደገም የመፍትሄ ሃሳብ የሚሰጠው ወገን እየጠበቀ ነው።አጫጭር ስሜት የሚኮረኩሩ፣ የእኔ ጎሳ የበለጠ ጀግናው የሚሉ ፉከራዎች ለነገ አብሮ የመኖር ሕልውናችን ዋስትናዎች አይደሉም።ዛሬ ኢትዮጵያ የምትሄድበትን መንገድ እያየን የነገ መውጫውን ካሁኑ መተለም የግድ ይላል። ለእዚህም የመፍትሄ ሃሳብ መውለድ ያስፈልጋል ።
ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com