ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, December 19, 2016

የአንካራው የሩስያው አምባሳደር ግድያ ምን አዲስ የፖለቲካ ትኩሳት ሊያስነሳ ይችላል? (የጉዳያችን ልዩ ዘገባ)

በቱርክ የሩስያ አምባሳደር አንድሬ ካርሎቭ ከመገደላቸው ጥቂት ደቂቃዎች በፊት ንግግር ሲያደርጉ  (photo: Reuters)

ጉዳያችን /Gudayachn

ታህሳስ 11፣2009 ዓም  (ዴሴምበር 19፣2016)



የሰኞው ምሽት ግድያ 


ሰኞ ምሽት በቱርክ ዋና ከተማ አንካራ የሚገኘውን የስዕል ኤግዚብሽን መክፈቻ ላይ የተገኙት ሩስያን እኤአ 2013 ዓም ጀምሮ በቱርክ የወከሏት አምባሳደር  አንድሬይ ካርሎቭ (Andrey Karlov) ከጀርባቸው በተተኮሰ የሽጉጥ ጥይት ተገደሉ።ግድያው በቀጣዩ ቀን የሶርያን ጉዳይ በተለይ ሩስያ፣ኢራን እና ቱርክ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው ደረጃ ውይይት ለማድረግ ሞስኮ ላይ ቀጠሮ ነበራቸው። ግድያውን ተከትሎ ከተሰጡት ሁለት መላ ምቶች ውስጥ አንዱ የሩስያ እና የቱርክ ግንኙነት ይሻክራል የሚለው ሲሆን ሌላው ደግሞ በሶስቱ ሀገሮች ማለትም በሩስያ፣ቱርክ እና ኢራን መካከል  ሶርያን አስመልክቶ የሚደረገውን ውይይት ለማደናቀፍ የታሰበ ነው የሚል ነው። ሆኖም ግን የሩስያው ፕሬዝዳንት ፑቲንም ሆኑ አደጋውን ወደ ሞስኮ እየበረሩ ሳለ አይሮፕላን ውስጥ የተነገራቸው የሩስያው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርገይ ላቭሮቭ (Sergey Lavrov) አደጋው በቱርክ እና በሩስያ መካከል ያለውን ግጭት የሚያባብስ አይሆንም ብለዋል።እንደ እውነቱም ከሆነ ቱርክ ከወራት በፊት የሩስያ አይሮፕላንን መትታ ከጣለችበት እና ግንኙነቷ ከሩስያ ጋር ከሻከረ ወዲህ ባሉት ጊዚያት ከሩስያ ጋር በሶርያ ጉዳይ እየተቀራረበች እና ሞስኮ ላይ ጉባኤ ለመቀመጥ ቀጠሮ እስከመያዝ መድረሷ በሁለቱ ሃገራት መካከል የከፋ ግንኙነት ተፈጥሯል ለማለት አያስደፍርም።ሆኖም ግን በሶርያ ጉዳይ ሩስያ እና ቱርክ የጋራ መስመር ለመያዝ አልተቸገሩም ማለት አይቻልም።ቱርክ የኩርድ ተገንጣይ እንቅስቃሴ በሶርያ መሰረት እንዳያገኙ ታስባለች።ከእዚህ በተለየ የቱርክ ከሩስያ ጋር መቀራረብ ጉዳዩን የምያወሳስበት መንገድ የቱርክ የናቶ ጦር ቃል ኪዳን ሀገሮች አባል መሆኗ ነው።ናቶ ደግሞ ከምሥራቅ በኩል ቀዳሚ ስጋቴ የሚላት ሩስያ ነች።ሩስያ እና ቱርክ ደግሞ የሶርያ ጉዳይ አገናኛቸው።ይህ ሁኔታ ምዕራባውያንን ያስደስታል ብሎ ማሰብ አይቻልም። 

ፑቲን ቅጭም ባለ ፊት 


የሩስያው ፕሬዝዳንት ፕሬዝዳንት ፑቲን ፊታቸውን ቅጭም አድርገው በ¨ሩስያ ቱዴይ¨ ቴሌቭዥን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሟቹን አምባሳደር አንድሬይ ካርሎቭን በቅርብ እንደሚያውቁ እና ትጉህ፣ታታሪ አምባሳደር መሆናቸውን ከገለፁ በኃላ ልዩ መታሰቢያ እንደሚደረግላቸው ገልፀዋል።ፑቲን ስሜታዊ ላለመሆን በሞከረ መልኩ በሰጡት በእዚሁ መግለጫ ላይ  በተለይ ጉዳዩን አስመልክተው ሲናገሩ የሶርያ ሰላም እየተሻሻለ መምጣት ያሳሰባቸው ወገኖች ድርጊቱን የፈፀሙ መሆናቸውን እንደሚገመት እና ልዩ የምርመራ ቡድን ወደ ቱርክ መላኩን ገልፀዋል። የቱርክ እንግሊዝኛ ጋዜጣ ¨ደይሊ ሳባህ¨በበኩሉ  በሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የአደጋ ኮሚቴ ከግድያው ጋር በተያያዘ መመስረቱን ከመግለፁም በላይ የሩስያ ፓርላማ (ዱማ) የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀመንበር ሌኦንድ ስሉትስኪ (Leonid Slutsky)
     ¨ በአንካራ እና በምዕራብ ያሉ ስልታዊ ጠላቶቻችን በአንካራ እና በሞስኮ መካከል አዲስ የግንኙነት መቀዛቀዝ  እንዲኖር እንደሚሰሩ ብናውቅም   ምንም አይነት አዲስ ውጥረት ግን አይኖርም¨ ማለታቸውን ጠቅሷል።

መንገዶች ሁሉ ወደ ሳውዲ አረብያ ያመራሉ 


በግንቦት ወር 2016 እኤአ  ¨ናሽናል ኢንተረስት ዶት ኦርግ¨  ¨ሩስያ እና ሳውዲ አረብያ ወደ ለየለት ፀብ እያመሩ ነው¨ (Russia and Saudi Arabia Are Headed for a Showdown) በሚል ርዕስ በወጣ ዘገባ ላይ በሩስያ እና ሳውዲ አረብያ መካከል ያለው ውጥረት በነዳጅ ገበያ ዙርያ የማይታጠፍ ነው ካለ በኃላ።ሳውዲ አረብያ በርካታ ነዳጅ ከአጋሮቿ ጋር ወደገበያ በመልቀቅ ተዋዳዳርዎቿን ለመጉዳት እንደምትሞክር ያትታል።ሩስያ በአንፃሩ የነዳጅ አምራች ሀገሮች ማህበር በምህፃሩ ¨ኦፔክ¨ በመባል የሚታወቀውን ድርጅት በተለየ ¨የጋዝ ላኪ ሀገሮች ፎረም¨ የሚል መስርታ ውጤታማ የሆነ ሥራ ላለፉት አስር አመታት መስራቷን ይገልፃል። የሩስያ እና የሳውዲ ችግር የቅርብ ጊዜ ክስተት ብቻ አይደለም። ሩስያ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ወታደሮቿ አፍጋኒስታን ዘምተው በነበረበት ወቅት ከፕሮፓጋንዳ እስከ ቀጥታ እርዳታ ከአሜሪካ ጋር ሆና ሩስያን ያጠቃች ሳውዲ አረብያ ነበረች። ¨አል ሞኒተር ¨  ¨What Russia's Syria shift means for Moscow-Riyadh ties¨ በሚል ርዕስ እኤአ መጋቢት 18፣2016 ዓም ባሰፈረው ፅሁፍ ላይ ይህንኑ የቆየ የሩስያ እና የሳውዲ አረብያ ፀብ እንዲህ በማለት ገልፆታል።
  ¨የሩስያ እና የሳውዲ ግንኙነት አሁን የተጀመረ ሳይሆን በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ሳውዲ አረብያ ፀረ-ሶቪየት ድጋፍ በአፍጋኒስታን በማድረግ ይገለፃል።በተጨማሪም የሩስያ መሪዎች በቼቼንያ ተገንጣዮች እንቅስቃሴ ሳውዲ አረብያን ይጠረጥራሉ¨ ይላል።

በሌላ በኩል ሩስያ በሳውዲ አረብያ ድርጊት ከተበሳጨችበት ጉዳይ አንዱ ሳውዲ አረብያ በየመን ላይ ከመጋቢት ወር 2015 እኤአ ጀምሮ የከፈተችው የአየር ጥቃት ጉዳይ ነው። ሳውዲ አረብያ በእዚህ ድርጊት በዓለም አቀፍ ወንጀል መጠየቅ እንደሚገባት ሩስያ ደጋግማ ተናግራለች።በእዚህ ድርጊትም ተባባሪ በመሆን መሳርያ ለሳውዲ አረብያ በመሸጥ የሚታወቁት እና የየመኑን እልቂት ሳውዲ አረብያን ከመውቀስ የታቀቡት ምዕራባውያንን ሩስያ ኮንናለች።ከእዚህ አልፋ የሩስያ መገናኛ ብዙሃን ሳውዲ አረብያ በየመን ፈፀመችው ያሉትን የህዝብ ፍጅት በቀጥታ በቴሌቭዥን በማስተላለፍ ከምዕራብ ዜና አውታሮች በተሻለ መንገድ ተቀምጣለች። 

¨የገዳዩን እጅ የዘወረው ማን እንደሆነ ማግኘት አለብን¨ ፕሬዝዳንት ፑቲን 
“We must know who directed the killer’s hand.” President Putin 

ይህ ሁሉ ጉዳይ በሩስያ እና ሳውዲ አረብያ መካከል እያለ ነው እንግዲህ የሶርያው የእርስ በርስ ጦርነት ሲነሳ ሩስያ በፕሬዝዳንት በሺር አል-አሳድ  የሚመራውን የሶርያን መንግስት ደግፋ ስትቆም ምዕራባውያን፣ሳውዲ አረብያ እና ኩአታር ከሶርያ አማፅያን ጎን የቆሙት።

ጦርነቱ እንደተጀመረ ሰሞን ፕሬዝዳንት ፑቲን በተለይ ፕሬዝዳንት ኦባማን የሶርያ አማፅያን የአሸባሪው ¨አይኤስ ኤስ¨ ውላጅ እና አካል መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ጠንቅ መሆናቸውን ባስረዱበት የቡድን ስምንት ስብሰባ ላይ አማፅያኑ የሰው ስጋ ሲበሉ የሚያሳይ ቪድዮ እስከማሳየት ደርሰዋል።በወቅቱ ፑቲን ሰሚ አላገኙም።ጦርነቱ በተለይ ሳውዲ አረብያ እና ኩአታር በአንድ በኩል በኢራን የሚደገፈው ¨ሄዝቦላ¨ እና የሶርያ መንግስት በሌላ በኩል ሆነው ሩስያ የሶርያን መንግስት በመደገፍ ጦርነቱ ቀጠለ።ጦርነቱ በያዝነው ወር ግን አዲስ ቅርፅ ያዘ።የሶርያ መንግስት ወታደሮች ቁልፍ በአማፅያን የተያዙ ከተሞችን ያዙ።አማፅያኑ የመውጫ ኮሪደር እንዲሰጣቸው ሩስያን እና የሶርያን መንግስት መማፀን ከጀመሩ ገና ሳምንታት መሆኑ ነው።የሶርያ ጦርነት በሶርያ መንግስት ሲጠናቀቅ የሳውዲ አረብያ እና ኩአታር እንዲሁም የምዕራባውያን እጅ አዙር እርጥባን የሚደርሳቸው አማፅያን ከገበያው መውጣት ደጋፊ አገሮችን ከሶርያ ጉዳይ የሚያሽቀነጥር ሆነ።የሶርያን ጉዳይ የሚወስኑት ባለጉዳዮቹ አሸናፊዎቹ ሊሆኑ ሳምንታት ቀሩት። ሩስያ ሞስኮ ላይ በመጭዋ የሶርያ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር ዛሬ ታህሳስ 11፣2009 ዓም ከቱርክ እና ኢራን ጋር ቀጠሮ ያዘች። 

ይህ በእንዲህ እያለ ነው የሩስያው አምባሳደር በአንካራ የስዕል ኤግዚቢሽን ላይ የተገኙት እና የቱርክ ፖሊስ ባልደረባ መሆኑ  በተነገረው ሰው ከጀርባቸው ተተኩሶ የተገደሉት።ግድያውን ማን ፈፀመው? ፕሬዝዳንት ፑቲን እንዳሉት የገዳዩን እጅ የዘወረው ማን እንደሆነ ያገኙት ይሆን? የጉዳያችን ስጋት ግን ገዳዩ ማንም ሆነ ማን ሩስያ በሳውዲ አረብያ ላይ የአየር ጥቃት ለመፈፀም ከእዚህ ጊዜ የተሻለ የማታገኝ መሆኑን ልታስብ ብትችል እና  ብታደርገውስ የሚል ነው።አንድ ቀን ማለዳ ስንነሳ በጭስ የታፈኑ የሳውዲ ሰማዮችን ከማየት ይሰውረን።በእዚህ ማን ያተርፋል? ማን ይጎዳል? ወደፊት የምናየው ይሆናል።ዓለማችንን ሰላም ያድርግልን።  


ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com