በኢትዮጵያ የተከሰተው ርኀብ እንደ ተባበሩት መንግሥታት ዘገባ ከሆነ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ያልታየ ነው።ዓለም አቀፍ የዜና ወኪሎች፣የተባበሩት መንስታት የምግብና እርሻ ድርጅት፣ከርኀቡ ስፍራ በስልክ ቃላቸውን ለኢሣት ራድዮ እና ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛው አገልግሎት የሰጡ የችግሩ ተጠቂዎች ሁሉ ያረጋገጡት የሰው ልጅ መሞት እንደጀመረ ነው።
በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በአንድ በኩል ከገዢው ፓርቲ የሚሰጠው ርኀቡን ተቆጣጥረነዋል የሚለው ዲስኩር እና በሌላ በኩል ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የሚቀርበው የልመና ጥሪ እየሰማ በከፍተኛ ቁጭት ላይ ነው።በአገር ቤት የሚኖረውም በተመሳሳይ ስሜት እና ይብሱን ነገ ይዞ የሚመጣውን ባለማወቅ በስጋት ላይ ይገኛል።ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ስርዓቱ ዛሬም ከፍተኛ ገንዘብ እያወጣ ለቀጣይ የጎጥ ድርጅቶች በመቶ ሚልዮን ብሮች እያወጣ ድግስ እያሳመረ ነው።
በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ችግሩን ከመስማት እና ከመቆጨት ባለፈ ለወገኖቹ የሚደርስበትን አንድ አይነት መንገድ ማመቻቸት አለበት። በተለይ በተበጣጠሰ መልክ በየቦታው የማሰባሰብ ሥራ እንዳይሰራ መጠንቀቅ እና ለአንዳንድ በወገናቸው ስም ለሚነግዱ ስርዓት አልበኞች እንዳይጋለጥ በህብረት አንድ ዓለማቀፋዊ በሆነ መልክ ማስተባበር ተገቢ ነው።ለምሳሌ በሳውዲ፣በየመን፣በሊብያ እና በደቡብ አፍሪካ ወገኖቻችን ላይ ችግር ሲደርስ የአቅሙን ጥረት ያደረገው በአክትቪስት ታማኝ እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን የሚስተባበረው ''ግሎባል አልያንስ'' ትልቅ ሥራ መስራት ይችላል።ይህ ተግባር በእራሱ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ለወገኖቹ ከመድረሱ በላይ ህብረቱን የሚያጠነክር አንዱ አይነተኛ አጋጣሚ ነው።ለወደፊቱም እንደ አገር ለሚገጥሙን ችግሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ አቅማችንን የምናዳብርበት ሌላው መንገድም ነው። ለኢትዮጵያ ማንም ከየትም አይመጣላትም እኛው ኃላፊነት ያለብን።በአገር ቤት በሕዝብ ንብረት እና ሀብት ላይ የሚቀልደው ስርዓት የተዋጣውን ገንዘብ ወይንም የተገዛውን እህል በትክክል ለወገኖቻችን መድረሱን የማረጋገጥ እና ሂደቱን በዓለም አቀፍ ድርጅቶች በኩል ማድረግ አሁንም የዓለም አቀፍ እንቅስቃሴው ኃላፊነት ይሆናል።
ምክንያቱም የብዙዎች ስጋት በስልጣን ላይ ያለው ስርዓት በኩል መላክ ያለው አሉታዊ ማለትም ለፖለቲካ ጥቅም ሊጠቀመበት ይቻላል የሚል ነው።ይህ ደግሞ የማይካድ ሀቅ ነው።ሆኖም ግን ኢትዮጵያውያን በአንድነት ግልፅነት ባለው መልክ እርዳታውን ያሰባስቡ እንጂ የሚላክበትን መንገድ በሥርዓት እና በመልኩ እንዲሆን የማድረግ እንዲሁም የማስገደድ አቅም ይኖራል። ገንዘብ ሲያዝ የመደመጥም ሆነ ተፅኖ የመፍጠር አቅሙም በእዛው መጠን ይጨምራል።አሁን ጥያቄው በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በርኀብ የተጎዱትን ወገኖቹን ከቁጭት ባለፈ እንዴት ይርዳ? የሚለው ነው። ቁጭት፣ሃዘን እና ብስጭት የሰሞኑ ከራሞታችን ሆኗል።ቀጥሎስ? በእዚህን ያህል ደረጃ ኢትዮጵያ ተርባ ዝም እንበል? ይህ ፈፅሞ ሊሆን አይችልም።በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ የገንዘብ አቅሙን ማሳየቱ ለወገኖቹ ፈጥኖ ከመድረሱ ባለፈ አምባገነኑን ስርዓት የመገዳደር አቅሙንም ማሳያ አንዱ መንገድም ነው እና ችላ አይባል።
የኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ''እረኛው'' የተሰኘው ክላሲካል ሙዚቃ Ethiopian Music Composer Prof.Ashenafi Kebede classical music
ጉዳያችን Gudayacn
ህዳር 8/2008 ዓም (Nov.18/2015)
No comments:
Post a Comment