ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, November 5, 2015

መንግስት ''ለውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያቱ እድገቱ ነው'' በሚል አዲስ የማምለጫ ምክንያት እየደረደረ ነው። እውን እድገት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያመጣል?

ዶ/ር አብርሃም ተከስተ 


  • ''ወደ አስር አመት ለሚጠጋ አመታት በውጭ ምንዛሪ እጥረት ስንሰቃይ ነበር'' የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ ዶ/ር  አብርሃም ተከስተ የተናገሩትን ዛሬ የኬንያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እንደዘገበው።

  • ''በዕድገታችን ሳቢያ የውጭ ምንዛሪ ክምችታችን አስተማማኝ ነው'' ቀድሞ አቶ መለስ በመቀጠል አቶ ሃይለማርያም ለምክር ቤት አባላት ባለፉት 10 አመታት ሲነግሩን የነበረው። 
መንግስት ''ለውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያቱ እድገቱ  ነው'' በሚል አዲስ የማምለጫ ምክንያት እየደረደረ ነው።የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ ''የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ምክንያት እድገታችን ነው'' ብለዋል።ቀጥለው ''ችግሩ (የውጭ ምንዛሪ ችግር) በርካታ የመንግስት እና የግል ፕሮጀክቶች ከመኖራቸው ጋር ይያያዛል'' አሉ ይለናል  የኬንያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዛሬ የለቀቀው ዜና።

ጉዳዩ ከእውነታው ጋር ይቃረናል።የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ ለውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያቱ የመንግሥታችን የተሳሳተ ፖሊሲ እና አሳታፊ አለመሆኑ ነው ከማለት ይልቅ በድፍኑ ''እድገቱ''ነው ካሉ በኃላ በማስከተል የፕሮጀክቶች መብዛት ነው ብለዋል።እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን ቀላቅለዋል።እድገትን እንደ አንድ ተጠያቂ ማድረግ እና የፕሮጀክቶች መለጠጥን ምክንያት ማድረግ የተለያየ ነው።ፕሮጀክቶች ስለተደረደሩ እና ሥራ ስለጀመሩ ብቻ እድገት አለ ማለት አይደለም።ፕሮጀክቶቹ አዋጪነት፣ለአገር የሚያመጡት ስልታዊ ጥቅም እና የእርሻውንም ሆነ የኢንዱስትሪውን ክፍል የማንቀሳቀስ አቅማቸው ሁሉ መፈተሽ አለበት።አቶ አብርሃም ግን በድፍኑ እድገቱ ነው በሚል ሊያልፉት ሞከሩ።

ለውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ምክንያት የፕሮጀክቶች መብዛት ብቻ ሊሆን አይችልም።እርግጥ ነው የፕሮጀክቶች መብዛት የውጭ ምንዛሪ ጥያቄን ያንረዋል።ሆኖም ግን  የፕሮጀክት መብዛት ነው ብለን ብንነሳ ይህ በእራሱ የስርዓቱን ስህተት የሚያሳይ ነው።ምክንያቱም የአለም ባንክን ጨምሮ ፕሮጀክቶች በአገሪቱ አቅም እና ቅድምያ የሚሰጣቸው አንገብጋቢ ፕሮጀክቶች ላይ ብቻ መሆን አለበት እንጂ ለምርጫ ፕሮፓጋንዳ ተብሎ ''አስር ወጥ አትጣዱ አንዱንም ሳታማስሉት እንዳያር'' የሚል መሰል ምክር ሲሰጥ ነበር።ይህንኑ የተሳሳተ ተግባር በውጭ የሚኖሩ ምሁራንም በተለያየ ጊዜ ደግመውታል።በመሆኑም የፕሮጀክት መብዛት ነው ቢባልም አሁንም ስህተቱ ወደ እራሱ የስርዓቱ የተሳሳተ ፖሊሲን አመላካች መሆኑ  አይቀርም።

ለውጭ ምንዛሪ እጥረቱ የዓለም አቀፉ ኦርቢት ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ ሲሳይ አሁንም ለኬንያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሰጡት መልስ ግን እውነቱም አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል።''የአገሪቱ ወደ ውጭ ሸቀጦችን የመላክ አቅም (ኤክስፖርት ሴክተር) ደካማ መሆን ነው ለውጭ ምንዛሪ እጥረት ዋናው ምክንያት'' ነበር ያሉት አቶ አለማየሁ።

የአቶ አለማየሁ ምክንያት እንዳለ ሆኖ ሌሎች የተረሱ ግን ዋነኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያቶች አሉ። ከአገሪቱ በሕገ ወጥ መንገድ በሙስና በተዘፈቁ ባለስልጣናት እና አቀባባይ ነጋዴዎችየሚሸሸው ገንዘብ ጉዳይ ምነው ተረሳ? ከአራት አመታት በፊት ከኢትዮጵያ 'ግሎባል ፋይናንስ ኢንተግሪቲ'' የተሰኘው ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም ባወጣው ዘገባ ከኢትዮጵያ በአስር ዓመታት ውስጥ ብቻ በሕገ ወጥ መንገድ 16.5 ቢልዮን ዶላር ከአገር መውጣቱን መገለፁ ይታወቃል።

ከእዚህ በተጨማሪ ስርዓቱ ስልጣኑን ለመጠበቅ የሚያወጣው ወጪ ለምሳሌ የተቃዋሚዎችን የመረጃ መረብ ለመስበር በሚልዮን የሚቆጠር ዶላር ለአንድ የጣልያን ኩባንያ መከፈሉን ከሰማን ገና ወራት ማስቆጠራችን ይታወሳል።ከእዚህ በተጨማሪ ለጎጥ ድርጅቶች አመታዊ በዓል እየተባለ የሚደገሰው ድግስ በሚልዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ የሚያወጣ ውስኪ እና ሌሎች የቅንጦት እቃዎች ግዥዎች መፈፀማቸውን አንርሳ።ከእዚህ በፊት ለህወሃት፣ለኦሕደድ ሰሞኑን ደግሞ ለብአዴን ተብሎ የወጣው ገንዘብ በእራሱ ስንት ሆስፒታሎችን፣ለስንት ዜጎቻችንን የስራ ዕድል በፈጠረ እና ይልቁንስ በአሁኑ ጊዜ በረሃብ የሚሰቃዩትን ስንት ወገኖቻችንን በታደገ ነበር።

ስለሆነም ለውጭ ምንዛሪው እጥረት ዋነኛ ምክንያቱ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ እንደሚሉት አይደለም።የዶ/ር አብርሀምን ንግግር ነገ አቶ ሃይለማርያም ሲደግሙት ለመስማት ተዘጋጅተናል።እውነታውን ግን ከመናገር እና ለኢትዮጵያ ህዝብም ከመግለፅ ወደኃላ ማለት የለብንም።ምክንያት ያለፈ ስህተትን አይሸፍንምና። 

የአቶ አብርሃም ተከስተን ገለጣ ኬንያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ድረ-ገፅ ላይ ለማንበብ ይህንን በመጫን ይመልከቱ።

ጉዳያችን GUDAYACHN
ጥቅምት 25/2008 ዓም (November 5/2015)
www.gudayachn.com


No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...