ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, November 13, 2015

ኢህአዴግ/ህወሃት የኢትዮጵያን እርሻ የገደለባቸው ሰባቱ ቀስቶች (የጉዳያችን ልዩ ማስታወሻ)ኢትዮጵያ ባለፈው ክ/ዘመን ያስተዳደሯት መንግሥታት በኢትዮጵያ እርሻ ላይ መሰረታዊ የመዋቅር ለውጥ ለመምጣት ስራዎችን ሰርተዋል።ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ በዘመናቸው የኢትዮጵያ ገበሬ በፊውዳል ባላባቶች መከራ የማየቱ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ንጉሡ በሰፊው የሰሩት የነበረው የዘመናዊ እርሻ ልማት ሥራ ነበር።በሰቲት ሁመራ፣በአርሲ ዘመናዊ የእርሻ ልማት ሥራ እና የሲዳሞ ዘመናዊ እርሻ ልማት የሚጠቀሱ ናቸው።ከእዚህ በተጨማሪ የአለማያ እርሻ ዩንቨርስቲ በአሜሪካኖች አማካሪነት እንዲከፈት ሲያደርጉ ለኢትዮጵያ እርሻ ትልቅ መዋቅራዊ ለውጥ ያመጣሉ በሚል ሕልም ነበር።

በደርግ ዘመነ መንግስትም ስርዓቱ ገበሬውን በነበረው ርዕዮት ያመረተውን በፈለገበት ገበያ እንዳይሸጥ ቢከለክለውም  የእርሻውን ክፍለ ኢኮኖሚ ግን ለማልማት ጥሯል።ለእዚህም አብነት የሚሆነው ወደመንግስት ንብረትነት የዞሩት ትላልቅ የእርሻ ልማቶች ደካማ አስተዳደራዊ አቅም ቢኖራቸው ምርት ማምረት ግን አላቆሙም።ለምሳሌ የአዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ፣የጣና በለስ ፕሮጀክት እና ከምሥራቅ ጀርመን ጋር በመተባበር የማረሻ ትራክተር እየገጣጠመ ያመርት የነበረው የናዝሬት ትራክተር ማምረቻ ፋብሪካ ተጠቃሽ ናቸው።ከእዚህ በተጨማሪ በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴም ሆነ በደርግ ዘመን የኢትዮጵያ ገበሬ የመሪዎቹ ቅርብ ጉብኝት እና ክትትል አልተለየውም ነበር። ንጉሱም ሆኑ ኮ/ል መንግስቱ በእየገጠሩ የሚደረጉትን ስራዎች እየዞሩ ይጎበኛሉ።ይህ አይነቱ ሥራ በዘመነ ኢህአዴግ/ህወሃት አልታየም።አንድ ወቅት አቶ መለስ ከገበሬዎች ጋር ሲወያዩ የሚያሳይ ፊልም ያውም ከሞቱ በኃላ ደጋግማ ስትታይ መታየቷ ''አንድ ለእናቱ'' የሆነች ብቸኛ ጉብኝት ሆና ቀርታለች።ከእዚህ ይልቅ ኢህአዴግ/ህወሃት በገበሬው እርሻ እያቆራረጠ አዲስ አበባ እንደመግባቱ የኢትዮጵያ እርሻን ችግር በበለጠ የሚረዱ መሪዎች በኖሩት ነበር።እነርሱ ግን አብዝተው ስለ ገበሬው ያወራሉ እንጂ አዲስ አበባን ከረገጡ በኃላ እረስተውታል።ለእዚህም አይነተኛ ምሳሌ የሚሆነን የሰቆጣ እና የዋግ ገበሬ ነው።የአቶ ዋልዋ አገር ዋግ ከአንድ አመት በፊት ያለበትን ችግር እና አቤቱታ አዛውንቱ እያለቀሱ ሲናገሩ ማየት እጅግ የሚያሳዝን ትዕይንት ነበር።

የኢትዮጵያን እርሻ  ኢህአዴግ/ህወሃት የገደለባቸው ሰባቱ ቀስቶች


ቀስት አንድ :- የተፈጥሮ ማዳበርያ የሚጠቀመውን ገበሬ አማልጋሜትድ ካምፓኒን አፍርሰው ጉናን መትከል ሂደት ላይ በነበሩበት ወቅት ከውጭ የመጣ መሬቱ አንዴ ከለመደ የማይለቅ የኬሚካል ማዳበርያ በግድ እንዲለምድ አደረጉት።በእዚህም ሚልዮን ዶላር ዛቁበት።አቶ መለስ  በኖርዌዩ የማዳበርያ ኩባንያ ለመሸለም ሽር ጉድ አሉ።አሁን ኩባንያው ማዳበርያውን ለመሸጥ አላስፈላጊ ሙስና ከአገራት ጋር መግባቱ ይፋ ሆነ።የእራሱ አገር መንግስት ጉዳዩን መመርመር ያዘ።የኢትዮጵያ ገበሬ ግን በግድ ማዳበርያ መሬቱ ላይ እረጭቶ መሬቱ ሌላ እንዳይለምድ ተደርጎ ቀረ።ይህ ብቻ አይደለም የማዳበርያ ዕዳ የኢህአዴግ/ህወሃት ገበሬውን የሚያስፈራራበት ጅራፍ ሆነ።ገበሬው በገዛ አገሩ የመንግስት ጭሰኛ ሆነ።

ቀስት ሁለት :- በአግባቡ ያላጠኑትን እና በቂ የባለሙያ ምክር የሌለበትን የውሃ ማቆር እያሉ ያዙኝ ልቀቁኝ አሉ።አንድ ወቅት ስለ ውሃ ማቆር ማውራት ልማታዊ መሆን ነው ተባለ።ለውሃ ማቆርያ ነው ብለው የፕላስቲክ ፋብሪካዎቻቸውን  ምርት ቸበቸቡ።ከጥቂት አመታት በኃላ የቆረው ውሃ የወባ ማፍሪያ ሆነ።ገበሬው አለቅን አለ።ቀድሞም አልተጠናም እና አሁን ውሃ ማቆር የሚለው ጉዳይ የት እንደደረሰ ሳይነግሩን እና የባከነው ሀብት ምን እንዳስገኘ ሳይታወቅ አረሳሱን።

ቀስት ሶስት  :- ከፍተኛ አምራች የነበሩ በደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ የሚኖሩ በደርግ ዘመን ትግራይን ጨምሮ ከሰሜን ኢትዮጵያ እና ከሐረር ሰፍረው የነበሩ ገበሬዎች ትውልዳችሁ አይደለም እየተባሉ ሲፈናቀሉ አቶ መለስ ፓርላማ ቀርበው ደን መትከል የሚያስተምረውን ገበሬ ደን ጨፈጨፈ ወዘተ እያሉ ሕዝብ እርስ በርሱ እንዲለያይ ቤንዚን አርከፈከፉ።በከፍተኛ አምራችነታቸው የሚታወቁ ገበሬዎች ከቤንሻንጉል፣ከጉርዳፈርዳ ተፈናቀሉ።በሐረር ደጋማ አካባቢ የሚኖሩ የኦሮምኛ ተናጋሪ ገበሪዎች ከሱማሌ ተናጋሪዎች ጋር በነበሩ ግጭቶች በሱማሌዎች ተገፍተው ስደተኛ ሲሆኑ የሚሰማቸው አልንበረም።ገበሬ በገዛ አገሩ ለማኝ ሆነ።

ቀስት አራት  : - ኢትዮጵያዊ  ኢንቨስተር በእርሻ ሥራ ላይ ገብቶ እንዳይሰራ በየክልሉ አስር አይነት ሕግ አውጥተው የክልሉ ተወላጅ ያልሆነ እንዳይሰራ በውስጥ አሰራራቸው  በተግባር አዋሉት።ከውጭ አገርም ሆነ ከአገር ውስጥ ጥሪታቸውን ሰብስበው ወደ እርሻ የገቡ ኢንቨስተሮች እንዳልሆኑ ሆነው የእርሻ መሳርያቸውን ሳይሰበስቡ ክልሎቹን እየተዉ ወጡ።

ቀስት አምስት  : - ቀድሞ አምራች የነበረው ገበሬ ከእህል ይልቅ በአገሪቱ እንዲስፋፋ ያደረጉት እና የፈቀዱትን ጫት እንዲያመርት ገፋፉት።ጫት በሌሎች አገሮች በአደገኛ እፅነቱ እንደሚመደብ እየታወቀ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ከከተማው አልፎ ገበሬው መሬቱን እየገለበጠ ጫት ሲተክል አበረታቱት።ጫት በቆሎን ተካ፣ጫት ጤፍን ማምረት አስተወ።ቀድሞ የእህል አምራች አካባቢዎች ጫት አምራች ሲሆኑ መንግስት ዝም ብሎ ያያቸው ነበር።አደገኛውን ቅጠል ሻጭ እና አሻሻጭ ከፍተኛ የጦር አዛዦች እና የከፍተኛ ባለስልጣን ሚስቶች ሆኑ።ኢትዮጵያ ጫት የሚቅሙ ገበሬዎች እና ወጣቶች የምንገላወዱባት አገር ሆነች።ቀድሞ የጫት ንግድ ያሳፍር የነበረውን በዘመነ ኢህአዴግ/ህወሃት ጫት ቤቱን ዩንቨርስቲ እና ኮሌጆች ላይ አደረገ።ተማሪዎች በከፍተኛ የጫት ሱስ ወደቁ።

ቀስት ስድስት : - በርካታ የእርሻ ባለሙያ ምሁራን እንዳይሰሩ በካድሬዎች መውጫ መግቢያ አጡ።የእርሻ ምርምር ኢንስቲቱዩት በርካታ በአገር ውስጥ እና በውጭ የሰለጠኑ ምሁራን ቢኖሩበትም የእራሳቸውን የምርምር ፅሁፍ ከመፃፍ እና ትንሽ ሰርተው አገር ጥለው በመሄድ ለሌሎች የአፍሪካ እና አውሮፓ አገራት ሲሳይ ከመሆን ያለፈ ምንም ማድረግ አልቻሉም።የሚገርመው ነገር የእርሻ ምርምር ኢንስቲቱዩት በመጀመርያ በክልል ከተሰነጣጠቁት መስሪያቤቶች ውስጥ አንዱ ነው።መስሪያቤቱ  ከሥራው ባህሪ አንፃር የፌድራል  መስርያቤት ብቻ ነው መሆን ያለበት እንጂ በክልል መደራጀት የለበትም በመላ አገሪቱ ላይ እንደ አየር ንብረት ፀባይ ነው ምርምሮቹ የሚሰሩት በመሆኑም መከፋፈል የለበትም ብለው ኃላፊዎቹ ከአቶ መለስ ጋር ጨምሮ ተከራክረው ነበር።ሆኖም ግን መከፋፈል ስራው የሆነው መንግስት የደቡብ፣አማራ፣ትግራይ፣ወዘተ እያለ ገነጣጠለው።አዲስ አበባ ያለው አስተባባሪ ቢሮ በየክሉሉ ያሉት የእርሻ ምርምር መስርያቤቶችን ማማከር የማይችልበት ደረጃ ደረሰ። ምክንያቱም ክልሎቹ ተጠሪነታቸው ለክልሉ መንግስት ስለሆነ የክልሉ መንግስት ደግሞ በካድሬዎች የተሞላ ስለሆነ በዶክትሬት ደረጃ ያሉት ተመራማሪዎች የጥናት ፅሁፍን በዲፕሎማ ደረጃ ያሉ የክልሉ ተወላጅ በመሆናቸው ብቻ በአለቅነት የተመደቡ ሃሳብ እንዲሰጡበት የተደረገበት ደረጃ ተደርሶ ነበር።የእዚህ ፅሁፍ ፀሐፊ አንድ ወቅት ከአንድ ባለሙያ እንደተረዳው ሐዋሳ ላይ ይሰረ የነበረ ባለሙያው በማስተርስ ደረጃ ቢሆንም የክልሉ ተወላጅ በመሆኑ ብቻ በዲፕሎማ ደረጃ ያለ ምንም አይነት ምርምር አድርጎ የማያውቅ የጥናት ፅሁፎች ላይ ሃሳብ እንዲሰጥ እና ፈርሞ እንዲያሳልፍ ተደርጎ የነበረበትን ሁኔታ ነበር። ይህንን በተመለከተ አዲስ አበባ የሚገኘው የእርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ተመሳሳይ ችግር በተለያዩ ክልሎች በማየቱ አቤቱታ አሰምቶ ሰሚ አላገኘም።አንድ ወቅት እንዲያውም የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ  በተደጋጋሚ ያሰሙት ቅሬታን ሰሚ በማጣታቸው ስራቸውን ለቀው ሌላ አፍሪካ አገር ሄደው ተቀጥረዋል።


ቀስት ሰባት : - ገበሬው የነበረውን ማኅበራዊ መስተጋብር አፈረሱት።ገበሬው የእራሱ የሆነ የኖረ ባህል አለው።ከሁሉም በላይ እርስ በርስ መደጋገፍ አንዱ መገለጫው ነው።ኢህአዴግ/ህወሃት ግን አንዱን ታጣቂ፣ሌላውን ፀረ ሕዝብ።አንዱን ሰላም አስከባሪ ሌላውን ፀረ ሰላም እያለ እርስ በርሱ እንዲጠላለፍ አንድ ለአምስት እያደራጀ አንዱ የአንዱ ጆሮ ጠቢ አደረገው።ይህ ማኅበራዊ ሰላምን የሚያናጋ ዘመዳሞች እርስ በርስ እንዲጣሉ አንዱ ባለ ጊዜ ሌላው ጊዜ የጣለው እያደረገ የተገፋው ቀየውን ጥሎ ወደ ሱዳን እና ሌሎች ቦታዎች እንዲሰደድ የቀረውም ተስፋ ቆርጦ እርስ በርሱ የጎሪጥ እየተያየ እንዲኖር ማድረግ ስራው ሆነ።ይህ በከተማ የኢንዱስትሪ ሰላምን እንደሚነሳ ሁሉ በገጠር ትልቅ ቀውስ አስከትሏል።ሌላው ቀርቶ ትርፍ አምራች የተባሉ ገበሬዎችን እሸልማለሁ እያለ ሲመርጥ አንዱ መስፈርቱ ለስርዓቱ ታዛዥ መሆን በውስጥ ታዋቂነት መለያ ሆነ።ለመስኖ አመቺ የሆነ መሬት የሚወስዱት የስርዓቱ ታዛዦች ሆኑ።እውነት መናገር ባህሉ የንበረውን ገበሬ ልቡን አሳዘኑት።የደረሰበትን ዘመን እያማረረ መኖር እጣው ሆነ።

ለማጠቃለል የኢትዮጵያን እርሻ ከነበረበት አሳደግነው ሲሉት የነበረው ሁሉ ሐሰት እንደሆነ ገሃዱ ወጣ።እርሻው አድጎ ቢሆን ኖሮ ከገበሬው አልፎ የከተማው ሰው ምርት እንደልቡ በቀረበለት ነበር።ገበሬውም እንደ ፈለገ በልቶ ባደረ ነበር።የገበሬው ሴት ልጆች ወደ አረብ አገር የሚልኩ ደላሎች እጅ ወድቀው በእየአረብ አገሩ ፍዳቸውን ባላዩ ነበር።እርሻው አድጎ ቢሆን ኖሮ ወጣት የገበሬው ልጆች በእየከተማው ሥራ ፍለጋ ባልተንከራተቱ ነበር።እርሻው አድጎ ቢሆን ኖሮ ኢንዱስትሪው በቂ ግብአት አግኝቶ ባደገ ነበር።እርሻው አድጎ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ ዛሬ 15 ሚልዮን ዜጋዋ በአንድ ክረምት ዝናብ ማጣት ብቻ የሚላስ የሚቀመስ ባላጣ ነበር።እርሻው አድጎ ቢሆን ኖሮ አሜሪካ እና ቻይና ለኢትዮጵያ የምግብ እርዳታ ሰጡ የሚል ዜና እየሰማን አንሳቀቅም ነበር።እርሻውን ገድላችሁታል።የእርሻ ምሁራን እንዳይሰሩ እግር ከወርች አስራችሁ መላወሻ አሳጥታችሁ አሰደዳችሁ።ዛሬ ኢትዮጵያ ተርባም ራበኝ ማለት ፖለቲካ ነው ብላችሁ ለማሳቀቅ በቃችሁ።ለመሆኑ እሩብ ክ/ዘመን (24 አመታት)  የአንድን አገር እርሻ ለማሳደግ ከበቂ በላይ አይደለም? ያውም በእዚህ ቴክኖሎጂ በፍጥነት በሚያድግበት ዘመን።ሃያ አራት ዓመት ውሸት አይሰለችም? አያሳፍርም? ግብርናን መግደል ወጭትን መስበር በወንጀለኝነት አያስቆምም? የኢትዮጵያ እርሻ ላይ 24 ብኩን አመታት በአናቱ ላይ በረው አልፈውበታል።ይልቁን ስለመጪው ዘመን እናውራ።ኢትዮጵያን እንዴት መልሰን እናንሳት? እንነጋገር።በሕይወት እያለን ቤተ መንግስቷንም፣ቤተ እርሻዋን እና ቤተ ኢንዱስትሪውን እንዴት ዘመን ተሻጋሪ ትውልድን አኩሪ አለምን የሚያስደምም እናድርገው? እኛ ከተነሳን እንችላለን።ቁጭት በውስጣችን እና በሌሎች ላይ መፍጠር መቻል አለብን።


ጉዳያችን GUDAYACHN   www.gudayachn.com 

ህዳር 4/2008 ዓም (November 14/2015)

No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...