ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, November 9, 2015

''7-ኪሎ'' የተሰኘች በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ምጣኔ ሃብታዊ እና ባህላዊ ጉዳዮች ላይ የምታተኩር አዲስ አለም አቀፍ መፅሄት ተመረቀች

የ7-ኪሎ የመጀመርያ እትም የፍት ሽፋን  (ከ7-ኪሎ ማኅበራዊ ድረ-ገፅ የተወሰደ)

''7-ኪሎ'' የተሰኘች በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ምጣኔ ሃብታዊ እና ባህላዊ ጉዳዮች ላይ የምታተኩር  አዲስ አለም አቀፍ መፅሄት ትናንት ጥቅምት 28/2008 ዓም በአሜሪካ፣ሲልቨር ስፕሪንግ ተመርቃለች።የመፅሄቱ ይዘት የቀድሞ አዲስ ነገር ጋዜጣ  አዘጋጆች እና ሌሎች ምሁራን የሚሳተፉባቸው ትንተናዊ ፅሁፎች የያዘ ሆኖ ለንባብ እንደሚበቃ ተገልጧል ።አዲስ ነገር ጋዜጣ ሕትመቷ እስከ ቆመበት ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ በተለይ በከተማ ነዋሪው ዘንድ የጋዜጣ አቀራረብ፣አፃፃፍ እና በፖለቲካዊ፣ማህበራዊ ጉዳይዮች ላይ ትልቅ፣ግልፅ እና አሳማኝ ትንተናዎችን በመስጠቷ ትልቅ ዝናን አትርፋ እንደነበር ይታወቃል።

በእዚህም ሳቢያ የማንበብ ባህል እየቆረቆዘባት ለመጣው ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋን የፈነጠቀ የአጭር ጊዜ መልካም ብልጭታ ሆኖ አልፏል።ይህ ሁኔታ በተለይ አዲሱ ትውልድ የአዲስ ነገር ጋዜጣ በእለተ ቅዳሜ መውጣት ዕለቱን በእጅጉ እንዲናፈቅ አድርጎት  ነበር።የኢህአዴግ/ህወሃት ጨካኝ የአፈና ስርዓት የኢትዮጵያን አንድ ሙሉ ትውልድ ለስደት እንደዳረገ የታወቀ ነው።ከፓይለት እስከ ገበሬ፣ከሕክምና ዶክተር እስከ ጋዜጠኛ ለስደት ተዳረገ።የአዲስ ነገር ጋዜጠኞችም ''አዲስ ነገርንም አዲስ ዘመንንም አላነብም'' ብለው በአንድ ወቅት በተመፃደቁት አቶ መለስ ዜናዊ የስልጣን ዘመን አረመኔያዊ ''የሽብርተኝነት'' ወንጀል እየተለጠፈባቸው ተሰደዱ።ሆኖም ግን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሥራ እና በትምህርት የሚገኙት የአዲስ ነገር አዘጋጆች ስራዎቻቸውን እየያዙ ብቅ እያሉ ነው።

በአሁኑ ወቅት የአዲስ ነገር ጋዜጣ መንፈሶችን በሁለት ሚድያዎች ሲንፀባረቁ ማየት ይቻላል።የመጀመርያው ቀደም ብሎ በተመሰረተው ዋዜማ ቦድካስት የራድዮ ዘገባዎች ሲሆን  ሁለተኛው በ7-ኪሎ የድረ-ገፅ እና የሕትመት መፅሄት ይሆናል ማለት ነው። 

በጉዳያችን ድረ-ገፅ ከአመት በፊት ስለ ዋዜማ ቦድካስት ራድዮ መጀመር አጭር ዘገባ ቀርቦ ነበር (http://www.gudayachn.com/2014/06/blog-post.html)። ዛሬ ደግሞ ስለ 7-ኪሎ የድረ-ገፅ እና የሕትመት መፅሄት ከ7-ኪሎ ማኅበራዊ ድረ-ገፅ ላይ የተገኘው ፅሁፍ ይበልጥ ገላጭ በመሆኑ ከእዚህ በታች እንዳለ እንደሚከተለው ቀርቧል።የአዲስ ነገር ቤተሰቦች በርቱልን!
=============/////================////===========///==

ከእዚህ በታች ያለው ፅሁፍ  በመጋቢት ወር ላይ በ7-ኪሎ ማኅበራዊ ድረ-ገፅ (https://www.facebook.com/7kilo/) ላይ ወጥቶ የነበረ ነው።

ሰባት ኪሎ ምንድነው? 

ሰባት ኪሎ ሚዲያ የኢትዮጵያን ፖለቲካ፥ ኢኮኖሚ፥ እና ባህል በጥልቅ የሚዳስስ እና የሚመረምር ተቋም ነው። በተቋሙ የተሰናዱት ሞያዊ ጽሑፎች በመጽሔት፥ በድረገጽ፥ እና በማኅበራዊ ሚዲያ ኔትወርኮች ይሰራጫሉ። የሞያዊ ጽሑፎቹ ይዘት ሽንጠ-ሰፊ ዘገባን እና የትንተና ጋዜጠኝነት ከሽኖ የሚቀላቅል ይኾናል።

ሽንጠ- ሰፊ ዘገባ ምንድነው?

መጽሔታችን (ኦንላይንም ኾነ የኅትመት) በጥልቅ እና በጥዑም ሽንጠ-ሰፊ ፊቸሮች እና ጽሑፎች የታጨቀ በመኾኑ ለቅዳሜ እና እሁድ ግሩም መዝናኛ እና መማሪያ፥ ለቀሪዎቹ የሥራ ቀናትም የቡና እና የሻይ ሰዓት ማረፊያ የተመቹ ናቸው። በአንባቢዎች ዘንድ በሚገባ የተጠኑ እና የተተነተኑ ፥ ሰፋ ያለ የማሰላሰያ ጊዜ የሚሹ ዘገባዎች እና የቃለምልልስ ፊቸሮች ጽኑ ረሃብ አለ ብለን እናምናለን።

የትንተና ጋዜጠኝነት ምንድነው?

መልካም ጋዜጠኝነት ኹሉ የሰላ እና በሚገባ የተብራራ ነው። ጋዜጠኞች ብዙውን ጊዜ ( ይኾነኝ ብለውም ኾነ በደመነፍስ) ለሚዘግቡት ታሪክ ምክንያተ-ጽሕፈት ያሰፍራሉ፤ ሞዴል ይሾማሉ፤ የትንቢታቸውን አንደምታ እና የትንተናቸውን ውጤት ይዘረዝራሉ። ዓላማችን መልካም ጋዜጠኝነት የመጽሔታችን ብሉይ ገዢ መርኾ ማድረግ ነው። ብሔራዊ ዜናዎቻችንን እና ጉዳዮቻችንን ተረድቶ ለማስረዳት ዳታዎችን እና ማኅበራዊ ሳይንስ ያጎለበታቸው ሜቶዶሎጂዎችን እና ሐለዮቶችን በሚገባ እንጠቀማለን። ሥራዎቻችንንም ለአንባቢዎቻችን በተዋበ ቋንቋ እና በሚያስደስት ዘዬ እናቀርባለን።

ከዚህ በላይ ያላችሁትን እንዴት ታሳኩታላችሁ?

ሥራችንን የምንጀምረው በዐሥር ጸሐፊዎች ( ሁለት ኢኮኖሚስት፥ ሦስት ፖለቲካል ሳይንቲስት፥ አንድ ሶስዮሎጂስት፥ የፍልስፍና የዶክትሬት ተማሪ፥ ሁለት የሕግ ምሁራን፥ አንድ ጋዜጠኛ) ነው። ጸሐፊዎቻችን እና ብሎገሮቻችን አስልቶ ለማሰብ በማኅበራዊ ሳይንስ ሜቶዶሎጂዎች በሚገባ የሠለጠኑ ከመኾናቸው ባሻገር መጽሔታችን ኤክስፐርቶች ጽሑፎቻቸውን እና ምልከታዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ስለሚጋብዝ ከዚህ በላይ ያልነውን እናሳካዋለን።

ሰባት ኪሎ መቼ ወደቡን ይለቃል?

በበራፍ ነን። የሰባት ኪሎ መርከብ በዚህ ሳምንት የፕሮጄክቱን ጉዞ ቀዳሚ ምዕራፍ በይፋ ያበስራል። የሰባት ኪሎ መጽሔት ማኅበራዊ ሚዲያ ክንፍ የሽንጠ-ሰፊ ዘገባዎቹን አጫጭር ጨመቆች ፥ የትዊተር መጣጥፎች፥ እና አጫጭር የፌስ ቡክ ጡመራዎችን በመልቀቅ ይጀመራል። በቀጣይም የሰባት ኪሎ ድረገጽ ይከተላል።የፕሮጀክቱ መደምደሚያ የኾነው የኅትመት መጽሔት በሰኔ ወር ይሰራጫል።

እንዴት ልሳተፍ?

እባካችሁ የሰባት ኪሎን የፌስ ቡክ እና የትዊተር ገጾችን ላይክ አድርጉ፥ተከታተሉ። በፕሮጀክታችን እና በመጣጥፎቻቸን ላይ የሚኖራችሁን ስል እና በሳል አስተያየት በናፍቆት እንጠብቃለን። በየዕለቱ ቀስ በቀስ የምንለቃቸውን አጫጭር ጨመቆች ተከታተሉ።ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
ቅጥምት 29/2008 ዓም (Nov.09/2015)

No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...