ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, December 6, 2014

አሁንስ ሰዎቹ ጫካ የነበሩም አልመስልህ አለኝ።ጫካ የነበረ እኮ ከአራዊቱም ከእፅዋቱም ሕግ ይማራል



ሕግ ሕግ ሕግ!!! ቅንጣት ታክል ሕግ የማያከብሩ ለማክበርም ፍላጎት የሌላቸው ሰዎች ተሰብስበው መንግስት መሆናቸው እየቆየ ይብሱን የሚያንገበግብ ጉዳይ እየሆነ ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢህአዴግ/ወያኔዎች የዛሬ 20 ዓመት አፀደቅነው ያሉትን ሕግ እየጠቀሰ ሲሞግታቸው እና ሕግ አክብሩ ሲላቸው ዓመታትን አስቆጠረ።በሕግ ስልጣን ባትይዙም በሕግ ስልጣን  ለሕዝብ አስረክቡ ቢባሉም አልሰሙም።ከሽግግሩ ጊዜ ጀምሮ ብዙዎች ብዙ ሊመክሩ ሞክረዋል። በ''ዞን 9'' ጦማርያን፣በፖለቲከኞቹ አንዱዓለም አራጌ፣በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ቀደም ብሎም በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ዳኛ ብርቱካን ደሜቅሳ እና ሌሎችም ስማቸውን ያልተጠቀሰው ሁሉ ሕግ የማክበርን 'ሀሁ' ለማስተማር ቢጥሩም ሰሚ አጡ።ሁሉም ስለ የሕግ የበላይነት ተናግረዋል፣ፅፈዋል።ሰሚ የለም።ይብሱኑ ከአመት ዓመት ትዕቢት ቤቷን እየሰራች በልቦናቸው ላይ እንደ ሸረሪት ድር እያደራች የሚናገሩት እሬት እሬት የሚል የሚሰሩት የውድቀታቸውን ጥልቀት የሚያሳይ ሆነ።

ሕግን ከመከራ  

ሰሞኑን በያዝነው በኅዳር ወር መጨረሻ ''የሕገ መንግስቱ ሰነድ የፀደቀበት'' እያሉ በሚወተውቱን ሰሞን የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 30 ''የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት'' በሚለው ርዕስ ስር ቁጥር 1 ስር ''ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሣሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና፣ አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው'' የሚለውን መሰረት አድርገው ሃሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ ሊገልጡ የተነሱትን የሰማያዊ ፓርቲን ጨምሮ 'የዘጠኙ ጥምረት' በመባል የሚታወቁት ዛሬ ህዳር 27/2007 ዓም ሰልፍ መውጣታቸው እና ከፍተኛ ድብደባ እና እስር እንደተፈፀመባቸው ይታወቃል።ፓርቲዎቹለሰልፉ  ያነሳሳቸው ዋናው ጉዳይ ሕግ የማያውቀውን ግን የህገ መንግስቱን  ሃያኛ  ዓመት ''ልደት'' ለማክበር ሽር ጉድ እያልኩ ነው የሚለውን ስርዓት ሕግ ለማስተማር ነበር።መማር አንድ ከማስተዋል አልያም ከመከራ ነው እና ኢህአዲግ/ወያኔ ከማስተዋል ሕግ እንደማይማር በተግባር አሳይቷል።ከመከራ ግን እንደሚማር ለማወቅ ግን ነቢይ መሆን አይጠይቅም።  


ሕግ ካላወቅህ ለምን እንደመለስከውም አትናገርም
 


ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ሐሙስ ህዳር 25/2007 ዓም ወደ አውሮፓ የነበረው ጉዞ እገዳ ምክንያት እስካሁን አልታወቀም።
ዛሬ ቅዳሜ ህዳር 27/2007 ዓም  በሸገር ''ታድያስ አዲስ'' ፕሮግራም ላይም የቴዲ ጉዞ ለምን እንደታገደ አለመታወቁን ተወስቷል።
ተመልከቱ! አንድ ኢትዮጵያዊ ያውም በሕዝብ የሚታወቅ ከያኒ አየር መንገድ ደርሶ ''ተመለስ መውጣት አትችልም'' ሲባል ለምን እንደሆነ አይነገረውም።''ለምን?'' ብሎ መጠየቅም አይችልም።ሕዝብም  አንድ ታዋቂ የኪነት ሰው ለምን ከሀገር መውጣት አትችልም እንደተባለ የማወቅ መብት የለውም።ምን ሕዝቡ ብቻ ጉዳዩ ስለ ኪነት ሰው ቢሆንም ጋዜጠኞችም ስለጉዳዩ መጠየቅ አይችሉም።ተመልከቱ! የትዕቢትን መጠን።ተመልከቱ የመጥገብን ልክ።ሌላው ቢቀር የአንድ አየር መንገድ ኢሚግሬሽን ሰራተኛ ሊሰጠው ከሚገባው አገልግሎት አንፃር ትንሹ አንድን ተገልጋይ እንደ ሰው ቆጥሮ ''እንዳትሄድ የተደረገው በእዚህ ምክንያት ነው'' ብሎ መናገር የአገልግሎት አሰጣጡ የሚጠይቀው ትንሹ የደንበኛ የማስተናገድ ክህሎት ነው።ለእዚህም ግን ትዕቢታቸው 'ስቅ ስቅ' እያለች ወጣጠረቻቸው።''ወደ ቤት ሂድ'' አሉት።ሃገሩ የግላቸው ነዋ! ሕግ አይገዛቸውም።ጥቂቶች ተጠራርተው በአንድ ወቅት ግንባራቸውን ለሞት በሰጡ ኢትዮጵያውያን አጥንት ተረማምደው ስልጣን ይዘዋላ! ማን ይናገራቸው? ሕዝብ ሕግ ምን እንደሆነ የሚያስተምርበት ቀን እሩቅ አይሆንም።


አዲስ ዘመን እና የፀጥታው መስርያ ቤት 

ሰሞኑን ''ዋዜማ'' የተሰኘው የድረ-ገፅ ራድዮ ነፍሱን ይማረውና በቅርቡ ለረጅም አመታት በስደት በኖረባት ስዊድን  ሀገር ህይወቱ ያለፈው  የታዋቂው ገጣሚ በብዕር ስሙ ገሞራው ከዛሬ 40 ዓመት በፊት በንጉሡ ዘመን ደርሶበት የነበረውን እንዲህ ይገልፀዋል።
''ገሞራው በ1966 ዓም በወቅቱ የኢትዮጵያ የፀጥታ መስርያ ቤት በመባል የሚታወቀው የደህንነት መስርያቤት በርካታ የድርሰት ፅሁፎቹ ይወሰዱበታል።ገሞራው ዝም አላለም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ለፀጥታ መስርያ ቤቱ ፃፈ።የደብዳቤው ይዘት ፅሁፎቹ በመስርያ ቤቱ መወሰዱን እና በፍጥነት ይመለስለት ዘንድ ይጠይቃል።አዲስ ዘመን ጋዜጣ በወቅቱ የንጉሡ ተቃዋሚ እና በተማሪዎች እንቅስቃሴ ንቁ ተሳታፊ የነበረው ገሞራው የወቅቱን የደህንነት መስርያቤት ወቅሶ ለፃፈው ደብዳቤ በሚዛናዊነት አትሞ አወጣው።''

አስገራሚው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የአንድ ተበዳይን ደብዳቤ ማተምን  ዛሬ ቢሆን  አዲስ ዘመን ጋዜጣ  ያደርገዋል ወይ? ብለን ጠይቀን ምን ያህል ወደኃላ እንደሄድን ማሰብ ሳንጨርስ ራድዮኑ የወቅቱ የፀጥታ መስርያቤት ''ስማቸውን ገሞራው ብለው ለጠሩት ግለሰብ'' ብሎ የመስርያቤቱን ሕግ አክባሪነት፣ የተወሰዱት ፅሁፎች በመስርያ ቤቱ ውስጥ እንደሚገኙ እና እየተመረመሩ መሆናቸውን እና መስርያ ቤቱ ከሌሎች በሕግ ከተመሰረቱ መስርያ ቤቶች አለመለየቱን የሚገልፅ ሰፋ ያለ ምላሽ መፃፉን እና ፅሁፉን አሁንም አዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳተመው ያብራራል።

ይህ ከአርባ ዓመታት በፊት የነበርንበት ዛሬ የኃልዮሽ ጉዞ ስናጤን የደህንነት መስርያ ቤት ለአንድ ግለሰብ ምላሽ ሊሰጥ ቀርቶ በንቀት ዜጋውን ቁልቁል የሚያይ የማን አለብኝ ባዮች መጠራቀምያ መሆኑ ነው አሳዛኝነቱ።ሕግ ማረፍያ አጣች።ኢትዮጵያውያን ፍትህ አጡ።ለቅሶ በየቦታው ተሰማ።ጥቂቶች በሕግ ላይ የሚረማመዱ ልዩ የዜግነት መብት ያላቸው ሆኑ።ለእዚህም ነው  ሰዎቹ ጫካ የነበሩም አልመስልህ አለኝ።ጫካ የነበረ እኮ ከአራዊቱም ከእፅዋቱም ሕግ ይማራል የሚያስብለኝ።

ጉዳያችን
ህዳር 28/2007 ዓም (ደሴምበር 7/2014)

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...