ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, December 11, 2014

ሰበር ዜና -ባለፈው ዓመት ከሳውዲ አረብያ ከተባረሩት ከአንድ መቶ ሰባ ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን 50% (ከ 85ሺህ በላይ የሚሆኑት) ተመልሰው ሳውዲ አረብያ መግባታቸውን አዲስ አበባ ላይ ዛሬ በወጣ አዲስ የዳሰሳ ጥናት ተገለፀ (የጉዳያችን አጭር ጥንቅር)


ፎቶ - የሰማያዊ ፓርቲ  የጠራው በሳውዲ መንግስት በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰውን ግፍ በመቃወም ሰልፍ የወጡ ወጣቶች በኢህአዲግ/ወያኔ ''ፌድራል ፖሊሶች ሲደበደቡ እና ወደ እስር ሲጋዙ  

ኢትዮጵያ ውስጥ የኑሮ መክበድ፣የነፃነት ማጣት እና የስርዓቱን ማዋከብ፣እስር እና ግድያ እየሸሹ የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከእለት ወደ እለት እየጨመረ ነው።ሰሞኑን በየመን የባህር ዳርቻ በቀይ ባሕር ውስጥ ከሰባ በላይ ኢትዮጵያውያን መስመጣቸው ይታወቃል።

ዛሬ የክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ማኅበር  (CRDA) በሳውዲ ተመላሾች አሁን ያሉበት ጉዳይ ላይ የሚወያይ አውደ ጥናት አዲስ አበባ ላይ የቀረበ አንድ ጥናት ባለፈው ዓመት ወደ ኢትዮጵያ ከተባረሩት ከአንድ መቶ ሰባ ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን 50% (ከ 85ሺህ በላይ የሚሆኑት) ተመልሰው ሳውዲ አረብያ መግባታቸውን ይገልፃል።ቪኦኤ የአሜሪካ ራድዮ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ ከአዲስ አበባ አውደ ጥናቱን አስመልክቶ ባቀረበው ዘገባ   የክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ማኅበር  (CRDA) የስትራቴጂክ ቡድን መሪ እና በድርጅቱ ልዩ አማካሪ አቶ ክፍለ ማርያም ገ/ወልድን ባነጋገረበት ወቅት ''ሀቁን እንነጋገር ከተባለ ግማሾቹ ተመልሰው ሄደዋል'' ብለዋል።

በአውደ ጥናቱ ላይ የተገኙ የስደት ተመላሾች ውስጥ ለቪኦኤ ሃሳቧን የሰጠች ወጣት ''ከችግር የተነሳ ነው።እዚህ ሆኘ እራሴን ከማጠፋ ሄጄ ልሙት ከማለት ነው'' ብላለች።ለወገኖቻችን በአራቱም ማዕዘን መውጣት የሀገራችን አጠቃላይ የፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች ከዋና ምክንያትነት አያመልጡም።የችግሩ ዋና መንስኤ እየተተወ ስደቱን ብቻ ብናወጋው መፍትሄ አይሆንም።

የተመላሾቹንም ሆነ የአዲሱን ትውልድ በሀገሩ ተመክቶ እና ተማምኖ እንዲኖር  አልተደረገም።ይልቁንም የኢህአዲግ አባል ካልሆነ  እና ከካድሬዎች እግር ስር ካለወደቀ መኖር አይችልም።በሥራ ዓለም ያለው ባለሙያንም ብንመለከት የነፃነት ማጣቱ እና ሃሳቡን እና ችሎታውን ለሀገሩ ማበርከት አልቻለም።መሃንዲሱ፣የህክምና ዶክተሩ እና የአይሮፕላን አብራሪው በሀገሩ ተስፋ እንዲቆርጥ ተደረገ።ሁሉ ሃገሩን ጥሎ ለመሄድ አኮበኮበ የቀረው ቆርጦ ከኢህአዴግ/ወያኔ ጋር ተጋፈጠ።ለእዚህ አብነት የሚሆኑን የሰማያዊ ፓርቲ እና የዘጠኙ አጋሮቻቸው ድርጊት ተጠቃሽ ነው።

የኢትዮጵያ ጉዳይ በእንዲህ አይነት ሁኔታ እንደሀገር የመቀጠላችን አደጋ በራሱ በግልፅ ይታያል።ጥቂቶች በሙስና እና በጎሳቸው ብቻ በሀብት ሲናጥጡ ሌላው ዜጋ ሃገሩን በረሃ ለበረሃ እየተንከራተተ ሲወጣ አይኖርም።አንድ ቀን እዝያው ሀገር ውስጥ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ የመውጣታቸው አደጋ አይኖርም ማለት አይቻልም።የወገኖቻችን  ሀገር ጥለው የመሄድ ጉዳይ የሚያመለክተው ይህንን ነው።ቁጥር ደግሞ ከሁሉ በላይ የሀገራችንን የፖለቲካ መድረክ መቀየር እንዳለበት አመላካች ነው።''ከሰማንያ ሺህ በላይ የሚሆኑ ወደ ሀገር ቤት የተመለሱ ወገኖቻችን ተመልሰው መከራ ወደ አዩባት ሳውዲ ተመለሱ'' የሚለው ዘገባ በእራሱ መጪውን አመላካች ነው።እናት ልጇ ተመልሳ እቤት ከገባች በኃላ ተመልሳ ስትሰደድ እንዴት ታዝን? ምን ያልደረሰብን አለ? ሱዳን ባቅሟ ኢትዮጵያውያንን አባረረች ስንባል፣የመን ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መንገዶቿን ሞሉ ሲባል፣ጅቡቲ ኢትዮጵያንን ስታስር፣ እራሳችንን መጠየቅ ያሉብን ሶስት ጥያቄዎች አሉ እነሱም -
ኢትዮጵያ ክብሯ እና ማንነቷ አልተዋረደም ወይ?  
ያለውን አስከፊ ሁኔታ ለመቀየር የፖለቲካው ችግር አለመስተካከል ዋነኛው ምክንያት አይደለም ወይ? እና 
ለእዚህም ተጠያቂዎች የእያንዳንዳችን ለስርዓቱ መቀየር የአቅማችንን አለማድረግ አይደለም ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች።
በመሆኑም ሰቆቃ ስንሰማ የምንኖርበት ዘመን እንዲቆም፣ኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካ አራማጅ፣በሙስና የተነከረው እና ክብሯን እና ማንነቷን ከሚመጥናት በታች የሆነ አስተሳስብ ያለው ኢህአዲግ/ወያኔ የበለጠ ሀገራችንን መቀመቅ ሳይከት የእያንዳንዳችንን ኃላፊነት እንወጣ።በዝምታችን ኢትዮጵያን ከሚገድሉ ጋር አንተባበር።

ከእዚህ በታች ያለው ማያያዣ የጀርመን ድምፅ ራድዮ ከጥቂት ወራት በፊት ከሳውዲ የተባረሩ ወገኖቻችን ተመልሰው ወደ ሳውዲ የመመለሳቸውን ሁኔታ አስመልክቶ በድምፅ  ያቀረበው ዘገባ ነው።

http://radio-download.dw.de/Events/dwelle/dira/mp3/amh/1FC0F3BD_2_dwdownload.mp3  

ጉዳያችን 
ታህሳስ 3/2007 (ዴሴምበር 12/2014 ዓም)


No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...